
የፎቶው ባለመብት, Iran's Presidential website/WANA/Reuters
የአሜሪካ ጦር፣ የኢራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦች የማጥቃት አቅም "ይበልጥ
ለማዳከም" ያለመ ነው ያለውን ጥቃት ለ10ኛ ተከታታይ ቀን ፈጽሟል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው፤ አገራቸው
በአሁኑ ሰዓት ከአሜሪካ ጋር "ሙሉ ጦርነት" ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል።
“እውነታው ዛሬ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሙሉ
የሆነ ጦርነት ውስጥ መሆኗ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ “እውነታውን መገንዘብ እና የዚህን ተጋድሎ ተፈጥሯዊ መዘዞች መቀበል ይኖርብናል”
ሲሉ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።
የሰኞ ሌሊቱ የዋሽንግተን ጥቃት የተፈጸመው ፕሬዝዳንት ዶናልድ
ትራምፕ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወታደሮችን የገደለችው ኢራንን እንደሚቀጡ ከተገዘቱ በኋላ ነው።
ባለፉት ቀናት በደረሱ ጥቃቶች ዮርዳኖስ ውስጥ
ሁለት፣ በኢራቅ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል።
ኢራን ከትናንቱ ጥቃት በኋላ በወሰደቸው የአጸፋ
እርምጃ፤ በሆርሙዝ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንዲሁም ባህሬን እና ኩዌት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎችን
መምታቷን ‘ኢርና’ የተሰኘው የመንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።
በተመሳሳይ ሰዓት፣ ከዚህ ቀደም የተፈራረሙት
የመግባቢያ ስምምነት የከሸፈባቸው አሜሪካ እና ኢራን በአሸማጋዮች አማካኝነት ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት እየተለዋወጡ መሆኑን ቴህራን
አስታውቃለች።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገጹ ባወጣው
መግለጫ፤ በትናንቱ ጥቃት የኢራን "ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላት፣ የባህር ኃይል አቅሞች፣ የሚሳዔል እና የድሮን ማስወንጨፊያ
ስፍራዎች እንዲሁም የአየር መከላከያ ሥርዓቶች"መምታታቸውን ገልጿል።
የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያደርጉትን
ጉዞ እንደቀጠሉም በመግለጫው ጠቅሷል።
ኢራን በበኩሉ ጥቃት በፈጸመችባቸው ሁለት ነዳጅ
ጫኝ መርከቦች ውስጥ የነበሩ ባሕርተኞችን ለማውጣት የነፍስ አድን ቡድን መሰማራቱን አስታውቃለች። መርከቦቹ የተመቱት በወሽመጡ በኩል
ለማለፍ በመሞከራቸው መሆኑን ኢርና ዘግቧል።
የዮርዳኖስ መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ከኢራን
የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን መትቶ መጣሉን ገልጿል። የኩዌት ጦርም
ኢራን ድሮኖችን እንደጠለፈ አስታውቋል።
ባሕሬን ደግሞ ከኢራን የተነሳ ድሮን የአየር
መቆጣጠሪያ ስርዓቶቿን ዒላማ ቢያደርጉም በረራዎች አለመስተጓጎላቸውን ጠቅሳለች።
የአሜሪካ ጦር በፈጸማቸው ጥቃቶች ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣
ኮናራክ፣ ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማም ኾሜኒን ጨምሮ በርካታ ከተሞች መመታታቸውን ከፊል ይፋዊ የዜና ወኪል የሆነው ታስኒም
ዘግቧል።
በኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት፣
ሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ፍንዳታ ተከስቷል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ፤
መርከቦቹ "ደኅንነቱ ባልተጠበቀው እና በአደገኛው ደቡባዊ መስመር" እየተጓዙ ስለነበረ፤ “ፍንዳታ እንደተከሰተባቸው
እና ጉዟቸው እንዲቋረጥ መደረጉን” አስታውቋል። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ይህንን ገለጻ አስተባብሏል።