የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግጭት ቀስቅሰዋል ሲሉ ወቀሱ

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተናገሩት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ "አንዳንዶቹ የተገደሉት ሰብአዊ ባልሆነ፣ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ነው" ብለዋል። ለሰዎቹ ሞት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

    እስራኤል ሐሙስ ዕለት በጋዛ ሰርጥ ዴይር አል ባላህ የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Palestinian News Agency

    እስራኤል ሐሙስ ዕለት በጋዛ ሰርጥ ዴይር አል ባላህ በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መገደላቸውን ሐማስ አስታወቀ።

    ሐማስ አክሎም እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን እየጣሰች ነው ሲል ወንጅሏል።

    በእስራኤል ጥቃት ተጨማሪ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

    እስራኤል ስለ አየር ጥቃቱ እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።

    መቀመጫቸውን በሊባኖስ ያደረጉ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የአልቃሰም ብርጌዶች አዛዥ ሙሐመድ አል ሐዋሊ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ተናግረዋል።

    አክለውም “እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጣስ ያላትን ፍላጎት ያሳያል’ ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።

    በተጨማሪም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ልየ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እስራኤል ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

    “ኳሱ ያለው በትራምፐ እና በዊትኮፍ ሜዳ ነው፤ ዋሽንግተን እስራኤል ለተኩስ አቁሙ ስምምነት ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው” ብለዋል።

    የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የጋዛ ጦርነትን ለመቋጨት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ግዛቱን የሚያስተዳድር በባለሙያዎች የሚመራ መንግሥት ወደሚቋቋምበት ሁለተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩ ከተገለፀ በኋላ ነው።

    የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ምሽት በሐዋሊ ቤተሰብ መኖሪያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአልቃሰም ብርጌዶች ኮማንደር አል ሐዋሊ ባለቤት እና ሴት ልጅ እንዲሁም ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

    የሕክምና ባለሙያዎች ከተገደሉት ሰዎች መካከል የ16 ዓመት ልጅ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

  2. የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት በአገሪቱ ላይ ወታደራዊ አገዛዝን ለመጫን በመሞከራቸው የአምስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው

    የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ ፍትህን በማደናቀፍ እና ሰነዶችን በማጭበርበር የአምስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው።

    የቀድሞው ፕሬዚዳንት እአአ በ2024 ከከሸፈው የወታደራዊ አገዛዝ ሕግ በኋላ ከተመሰረቱባቸው አራት ክሶች ጋር በተያያዘ የተሰጠ የመጀመርያው ፍርድ ነው።

    ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝን ለማስፈን ያደረጉት ሙከራ አጭር ጊዜ ብቻ የቆየ ቢሆንም በመላው አገሪቱ ነውጥ ፈጥሮ ነበር።

    የቀድሞው ፕሬዚዳንት በዚህ ውሳኔያቸውም ለስድስት ሰዓታት ያህል ወታደራዊ አገዛዝን በአገሪቱ ላይ እንዲሰፍን አድርገዋል።

    ይህንን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያውያን ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣታቸው የሕዝብ እንደራሴዎች ዮንን ለማውረድ ብሔራዊ ጉባዔ እንዲጠሩ አስገድዷቸዋል።

    አርብ ዕለት ጉዳዮን የሚመለከቱት ዳኛ የዮን ድርጊት “አገሪቱን ወደ ፖለቲካ ቀውስ ከቷታል” በማለት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በጥፋታቸው “ምንም ዓይነት መጸጸት አላሳዩም” ብለዋል።

    አርብ ዕለት የተሰጠው ውሳኔ ዮን ላይ የተመሠረቱት ሌሎች ክሶች ላይ የሚሰጠው ፍርድ ምን ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል።

    ከቀረበባቸው ክሶች መካከል ከባዱ መንግሥት ላይ ማመጽ የሚል ሲሆን በዚህም አቃቤ ሕግ የሞት ቅጣት አንዲጣል ጠይቋል።

    ውሳኔው በየካቲት ወር ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

  3. የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ባካሄደው ዘመቻ ከ30 በላይ የአል ሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ

    የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም)

    የፎቶው ባለመብት, SONNA

    የአፍሪካ ኅብረት በደቡብ ሶማሊያ ሐሙስ ዕለት ባካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ከ30 በላይ የአልሸባብ ተዋጊዎች መገደላቸው ተገለፀ።

    በታችኛው ሸበሌ ክልል የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻው በአየር ኃይል የታገዘ እንደነበር የገለፀው ኅብረቱ፣ የሶማሊያ ጦር እና የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች በጋራ መሳተፋቸውን ገልጿል።

    አፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ በቅርቡ ከጌንዴርሼ እና ጂሊብ ማርካ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ተገፍተው እንዲወጡ የተደረጉ ታጣቂዎች በወታደሮቹ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ እርምጃ መወሰዱን ተናግሯል።

    “በምድር እና በአየር በጥምረት በተፈጸመ ዘመቻ ከ30 በላይ የአልሸባብ ወታደሮች ሲደመሰሱ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።”

    በዘመቻው የሶማሊያ መከላከያ ወታደሮች፣ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም)፣ የቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲሁም የኡጋንዳ ጦር ተሳትፈዋል።

    አፍሪካ ኅብረት አክሎም ለጸጥታ አካላት እና ለሰላማዊ ዜጎች ስጋት የሆኑትን ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ መውሰዱን ገልጾ ተልዕኮው ሰላማዊ ዜጎችን መከላከል እና የሰብዓዊ ድጋፍ ደህንነቱ በተጠበቁ መንገድ እንዲደርስ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።

    አልሸባብ የሶማሊያ መንግሥትን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲዋጋ የነበረ ሲሆን አፍሪካ ኅብረት ወሰድኩት ባለው እርምጃ ላይ ያለው ነገር የለም።

    አፍሪካ ኅብርት የአልሸባብን እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት እንዲኖር ለማድረግ በጋራ የሚሠራቸውን ሥራዎች እንደሚቀጥል ገልጿል።

  4. የታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ደራሲ ቺማማንዳ ልጅ ሞትን ተከትሎ በናይጄሪያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ቀረበ

    ታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ደራሲ ቺማማንዳ ንጎዚ ልጇ ኦክስጅን እንዳያገኝ በመደረጉ እና በከፍተኛ የሕመም ማስታገሻ ስለተሰጠው መሞቱን ትናገራለች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ደራሲ ቺማማንዳ ንጎዚ ልጅ በሕክምና ቸልተኝነት ምክንያት መሞቱ ከተገለፀ በኋላ በናይጄሪያ ከፍተኛ ውዝግብ ተነሳ።

    የደራሲዋ ልጅ በሕክምና ቸልተኝነት ምክንያት መሞቱ ከተገለፀ በኋላ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው በርካታ ውንጀላዎች በናይጄሪያ የሕክምና ስርዓት ላይ ቀርበዋል።

    ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘችው ቺማማንዳ የ21 ወር ልጇ የሞተው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    የደራሲዋ ልጅ በሌጎስ በሚገኝ የግል ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያገኘ እንደነበር ተገልጿል።

    ልጇ ኦክስጅን እንዳያገኝ በመደረጉ እና ከመጠን በላይ የሕመም ማስታገሻ ስለተሰጠው የልብ ድካም አጋጥሞት ሕይወቱ ሊያልፍ ቸሏል ተብሏል።

    ሆስፒታሉ በልጁ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ ምንም ዓይነት የሕክምና ስህተት አለመፈጸሙን በመግለጽ ተከራክሯል።

    የሌጎስ ከተማ አስተዳዳሪዎች በሕክምና ቸልተኝነት የተነሳ በሚከሰቱ ሞቶች የተቀሰቀሰውን የሕዝበ ቁጣ ተከትሎ በሟች ላይ ተጨማሪ ምርምራ እንዲደረግ አዝዘዋል።

  5. የኢራን የጸጥታ አካላት የተቃዋሚ ሠልፈኞችን አስከሬን ለመስጠት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃሉ ተባለ

    በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ ወቅት ጫማቸውን የጣሉ ሠዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ ወቅት የተገደሉ ሠዎችን አስከሬን ወስዶ ለመቅበር የጠየቁ የቤተሰብ አባላት ከፍተኛ ገንዘብ በባለሥልጣናት መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ቢቢሲ ፐርዢያ ያነጋገራቸው በርካታ ሰዎች ከሆስፒታሎች የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ለመውሰድ የሚፈልጉ የቤተሰብ አባላት ገንዘብ ካልከፈሉ በስተቀር መውሰድ እንደማይችሉ በጸጥታ አካላት መከላከላቸውን ገልጸዋል።

    ከሁለት ሳምንት በላይ በመላ አገሪቱ በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ቢያንስ 2,435 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።

    በራሻት የሚኖር አንድ ኢራናዊ የቤተሰቡን አስከሬን ለመውሰድ 5,000 ዶላር (700 ሚሊዮን ቶማን) እንዲከፍል እንደተጠየቀ ለቢቢሲ ተናግሯል።

    የቤተሰቡ አስከሬን በፖርሲና ሆስፒታል እንደሚገኝ የተናገረው ይህ ግለሰብ የሌሎች 70 ተቃዋሚ ሠልፈኞችንም አስከሬን በዚሁ እንዳለ ገልጿል።

    በግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና አስከሬኖችን ለመውሰድ የጠየቁ ኩርዶች 7000 ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ቤተሰቡ የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ስላልቻለ አስከሬኑ በማቆያ ውስጥ እንደተቀመጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። በኢራን የግንባታ ሠራተኞች በወር የሚያገኙት ከ100 ዶላር በታች ነው።

    አንዳንድ አካባቢዎች የሆስፒታል ሠራተኞች ለሟች ቤተሰቦች በመደወል የደህንነት አባላት የልጃቸውን አስከሬን ይዘው ገንዘብ ከመጠየቃቸው በፊት በፍጥነት መጥተው እንደሚወስዱ እንደሚያስጠነቅቅቁ ቢቢሲ ሰምቷል።

    በቴህራን ምንጮች ለቢቢሲ ፐርዢያ እንደተናገሩት ባለሥልጣናት የልጆቻቸውን አስከሬን ለመውሰድ ገንዘብ ይጠይቁናል ብለው የፈሩ የቤተሰብ አባላት የአስከሬን ማቆያ ክፍል ሰብረው የወዳጅ ዘመዶቻቸውን አስከሬን መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

    የልጆቻቸውን አስከሬን ያገኙ ቤተሰቦች የግል አምቡላንስ መጥቶ እስኪወስድላቸው ድረስ በሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ አስከሬኑን አስቀምጠው ሲጠብቁ መታየታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

    በኢራን የተቃውሚ ሠልፍ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት አስቸጋሪ አድርጎታል።

    ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ቡድኖች እንዲሁም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያላቸው ግንኙነት መቋረጡን ተናግረዋል።

    ቢቢሲ ኢራን ውስጥ ገብቶ እንዲዘግብ አልተፈቀደለትም።

  6. ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ላይፈጽሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ

    የነዳጅ በርሜሎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ላይፈጽሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ቅናሽ አሳየ።

    የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 64 ዶላር ዝቅ በማለት የአራት በመቶ ቅናሽ አስመዝግቧል።

    ባለፉት ቀናት የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 67 ዶላር ነበር።

    በሌላ በኩል ረቡዕ ዕለት የወርቅ ዋጋ ወደ 4ሺህ 600 ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም ማክሰኞ ከነበረው በ0.4 በመቶ ከፍ ያለ ሆኗል።

    ትራምፕ በጽህፈት ቤታቸው ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች "ኢራን ዜጎቿን በሞት መቅጣት ማቆሟን ሰምተናል። . . . .በሞት የመቅጣት ዕቅድ የለም” ብለው ነበር።

    ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ “በጣም ጠንከር ያለ እርምጃ” እንደሚወስዱ ዝተው ነበር።

    የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ1 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም የትራምፕን አስተያየት ተከትሎ ወዲያውኑ ቅናሽ ተመዝግቧል።

    ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዳቸውን ትተውት እንደሆን ሲጠየቁ ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።

  7. የዴንማርክ የአውሮፓ አጋሮች በግሪንላንድ ወታደራዊ ተልዕኳቸውን ጀመሩ

    የአውሮፓ የኔቶ አጋሮች ለጋራ ልምምድ ወደ ዋና ከተማዋ ኑክ ሲያቀኑ የዴንማርክ የአየር ኃይል ማመላለሻ አውሮፕላን ግሪንላንድ ደርሷል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ የኔቶ አጋሮች ለጋራ ልምምድ ወደ ዋና ከተማዋ ኑክ ሲያቀኑ የዴንማርክ የአየር ኃይል ማመላለሻ አውሮፕላን ግሪንላንድ ደርሷል

    አስራ አምስት የፈረንሳይ ጦር አባላት ግሪንላንድ ዋና ከተማ ኑክ መድረሳቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በርካታ የአውሮፓ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ግሪንላንድ ለቅኝት ተልዕኮ አሰማርተዋል።

    ጀርመን፣ ስዊዲን፣ ኖርዌይ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ወታደሮቻቸውን የላኩ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክ ራስ ገዝ የሆነችው ግሪንላንድ ትገባኛለች ማለታቸውን ቀጥለውበታል።

    የኔቶ የአውሮፓ አጋሮች ወታደሮቻቸውን ወደ ግሪንላንድ መላካቸው ያልተጠበቀ እርምጃ ነው ተብሏል።

    የፈረንሳይ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊቪር ዲ አርቮር ጠንካራ የፖለቲካ መልዕክት ያስተላልፋል ሲሉ ተናግረዋል።

    “ይህ የመጀመሪያው ልምምድ ነው. . . ለአሜሪካ ኔቶ መኖሩን እናሳያታለን።”

    የወታደሮች የጋራ ልምምድ የተሰማው የዴንማርክ እና የግሪንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ዋሺንግተን አቅንተው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ካገኙ በኋላ ነው።

    ከስብሰባው በኋላ የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላርስ ሎኬ ራስሙሰን እንደተናገሩት ውይይቱ ገንቢ ቢሆንም፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል "መሠረታዊ አለመግባባት" እንዳለ ጠቀወሰው ትራምፕ ግሪንላንድን ለመግዛት ያቀረቡትን ጥያቄ ተችተዋል።

  8. ሩሲያ በሰላይነት የወነጀለችውን የብሪታንያ ዲፕሎማት አባረረች

    ሞስኮ የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ መግቢያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    ሩሲያ ሞስኮ በሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲው ውስጥ በድብቅ የሚሠራ ሰላይ ነው የሚል የወነጀለችው የብሪታኒያ ዲፕሎማት አገሪቱን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዘች።

    የዲፕሎማቲክ እውቅናው የተሰረዘው ይህ ማንነቱ ያልተገለጸው ግለሰብ፤ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቆ መውጣት እንዳለበት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፤ በሩሲያ የሚገኙት የብሪታንያ ጉዳይ ፈጻሚ ዳኔ ዶላኪያ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጥራቱንም ገልጿል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እስካሁን ውንጀላውን በተመለከተ አስተያየት አልሰጠም።

    ሞስኮ ወደ ግዛቷ የሚገቡ "በይፋ የማይታወቁ የብሪታንያ የደኅንነት መኮንኖችን" እንደማትታገስ ገጻለች። ዩናይትድ ኪንግደም ሁኔታውን የምታባብሰው ከሆነም ተጨማሪ እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቃለች።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዩናይትድ ኪንግደም እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል። በሩሲያ በ2022 ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ ሁለቱም አገራት በግዛቶቻቸው ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዲፕሎማቶችን አባርረዋል።

    ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ሩሲያ ሰላይ ናቸው በሚል የወነጀለቻቸውን ሁለት የብሪታንያ ባለሥልጣናትን አባርራ ነበር። የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በወቅቱ በሰጠው ምላሽ፤ ሞስኮ በሠራተኞቹ ላይ "ተንኮል ያዘለ እና መሠረተ ቢስ ክስ" አቅርባለች በማለት ወቅሶ ነበር።

    "በብሪታንያ ኤምባሲ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደረግ ማስፈራራትን አንታገስም" ያለችው ዩናይትድ ኪንግደም በምላሹ የአንድ ሩሲያዊ ዲፕሎማት እና ባለቤቱን እውቅና ሰርዛለች።

  9. የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በድጋሚ በኢራን ጉዳይ ሊሰበሰብ ነው

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት

    የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢራን የተከሰተውን ተቃውሞ እና የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ሐሙስ ስብሰባ ያካሂዳል።

    በአሜሪካ ጠያቂነት ይካሄዳል በተባለው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ከሁለት ሺህ በላይ ተቃዋሚዎች ተገድለውበታል ስለተባለው የኢራናውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና በአገሪቱ ስላለው ሁኔታ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።

    ሦስተኛ ሳምንቱን እያጠናቀቀ ያለው የኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ አብዛኛውን የአገሪቱ ከተሞች ያዳረሰ ሲሆን፣ መንግሥትም ተቃውሞውን ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰደ ነው።

    እስካሁን ከ2,500 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር ጥቂት የማይባሉ የመንግሥት ፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸው ተዘግቧል።

    የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ከሳምንት በፊት በኢራን ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የአሁኑ ደግሞ በአገሪቱ ስላለው ሁኔታ ማብራሪያ እንደሚቀርብበት ተገልጿል።

    ረቡዕ ዕለት የመብት ተከራካሪው አምነስቲ ኢንተር ናሽናል የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት "ኢራን ውስጥ ተጨማሪ ግድያዎችን ለማስቆም" አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል።

    አምነስቲ ዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የኢራን ባለሥልጣናት የሕጋዊ ጥበቃ መብታቸው ማብቃቱን እንዲያውቁ ማድረግ አለበት ሲል ጥሪ አቅርቧል።

    ድርጅቱ ጨምሮም ኢራን ውስጥ መጠነ ሰፊ ከሕግ ውጪ ግድያ መፈጸሙን ከቪዲዮዎች እና ከታማኝ የዓይን ምስክሮች እንዳረጋገጠ በሪፖርቱ ገልጿል።

  10. ስታርሊንክ ኢራናውያን በነጻ ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ፈቀደ

    የስታርሊንክ ኢንተርኔት መቀበያ ሳህን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታም ኢላን መስክ ንብረት የሆነው የሳተላይት ኢንተርኔት አቅራቢው ስታርሊንክ፤ ኢራን ውስጥ ከክፍያ ነጻ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት አቀረበ።

    የኢራን መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት አቅርቦት በማቋረጡ ምክንያት በሳተላይት የሚሠራው ለስታርሊንክ ወርሃዊ ክፍያ እየፈጸሙ ይጠቀሙ የነበሩ ኢራናውያን አገልግሎቱን በነጻ እንዲያገኙ ፈቅዷል።

    ምንም እንኳን ስታርሊንክ በኢራን ውስጥ ሕገወጥ ቢሆንም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በድብቅ አገልግሎቱን ይጠቀማሉ።

    የኢራን መንግሥት ከሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ውጪ ቁጥጥር የሚያደርግበትን ስታርሊንክን ሲጠቀሙ የሚገኙ ሰዎች እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

    ሦስት ሳምንት የሞላውን ተቃውሞ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በመላው ኢራን ኢንተርኔት የተዘጋ ሲሆን፣ ባለሥልጣናትም ዜጎች ኢንተርኔት እንዳይጠቀሙ ለማገድ የስታርሊንክ ማገናኛ የሳተላይት ሳህኖችን እያሰሱ ነው።

    ኢራን ውስጥ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ግንኙነት ከመስተጓጎሉም በላይ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ያለው የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እርምጃ በቀሪው ዓለም እንዳይታወቅ አድርጓል።

  11. ግሪንላንድ፣ ዴንማርክ እና አሜሪካ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተጠናቀቀ

    ግሪንላንድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከአሜሪካ አቻቸው ጋር የተወያዩት የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግሪንላንድ ጉዳይ “ከአሜሪካ ጋር መሠረታዊ ልዩነት” እንዳላቸው ተናገሩ።

    ላርስ ሎክ ራስሙሰን ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ጋር በዋይት ሐውስ ተወያይተዋል።

    “ውይይታችን ግልፅ እና ገንቢ ነው” ያሉት ላርስ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን “እንጠቀልላታለን” ማለታቸው “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

    አሜሪካ፣ ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ያደረጉት አንድ ሰዓት የወሰደ ውይይት ያለስምምነት ተጠናቋል። ነገር ግን የግሪንላንድ ዕጣ ፈንታን ለመወሰን በከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘንድ ንግግር ሊኖር እንደሚገባ እንደተስማሙ ተዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት በተደጋጋሚ ግሪንላንድን መቆጣጠር ለብሔራዊ ደኅንነት ወሳኝ ነው ሲሉ ይሰማል።

    ይህ የትራምፕ አቋም የኔቶ አባል የሆነችውን ዴንማርክ ያስቆጣ ነው።

    ከመሬት ስፋቷ አንፃር እጅግ ትንሽ ሰው የሚኖርባት ግሪንላንድ በሰሜን አሜሪካ እና አርክቲክ መካከል መገኘቷ የሚሳዔል ጥቃት ቢመጣ ቀድሞ ለማሳወቅ እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ለመቆጣጠር ወሳኝ ሥፍራ ያደርጋታል።

    አሜሪካ ሰሜን ምዕራብ ግሪንላንድ በሚገኘው ፒቱፊክ የጦር ካምፕ 100 ያክል ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ይህ ካምፕ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ጀምሮ በአሜሪካ ሲመራ ቆይቷል።

    አሜሪካ ከዴንማርክ ጋር ባላት ስምምነት መሠረት የፈለገችውን ያህል የወታደር ቁጥር ወደ ግሪንላንድ መላክ ትችላለች።

  12. ትራምፕ ኢራን ተቃዋሚዎችን መግደል “እያቆመች ነው” አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን ተጨማሪ ተቃዋሚዎችን የመግደል “እቅድ የላትም” ቢሉም ቴህራን በመንግሥት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ላይ የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎ አሜሪካ ለመውሰድ የዛተችው እርምጃ ስለመቅረቱ ግን አልገለጹም።

    ረቡዕ ዕለት በዋይት ሀውስ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ፤ “በኢራን ግድያው እየቆመ መሆኑ እና ግድያ ለመፈጸም እቅድ እንደሌለ”፤ አስተዳደራቸው በአንድ “ጥሩ ባለሥልጣን” እንደተነገረው ገልጸዋል።

    ትራምፕ ጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ ይህንን መረጃ የሰጣቸው “በሌላው ወገን ያለ በጣም ጠቃሚ ምንጭ” እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ መረጃ እውነት ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

    ታህሳስ ላይ የጀመረው የኢራን ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የአገሪቱ ገንዘብ አቅም በከፍተኛ ደረጃ መውደቁን ተከትሎ ነበር። ይሁን እንጂ በተለያዩ ግዛቶች በፍጥነት የተስፋፋው ተቃውሞ፤ የኢራን ሃይማኖታዊ አገዛዝ ላይ የቅቡልነት ቀውስ ፈጥሯል።

    ትራምፕ፤ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎችን የሚገድል ከሆነ “እጅግ ጠንካራ እርምጃ” እንደሚወስዱ ዝተው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት፤ በተቃውሞው ወቅት የተያዘ ኤፍራን ሶልታኒ የተባለ የ26 ዓመት ሰልፈኛ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት መገለጹን ተከትሎ ነው።

    ተቃዋሚው ረቡዕ ዕለት የሞት ቅጣት ሊፈጸምበት ቀጠሮ ተይዞ እንደነበር ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። ኋላ ላይ ግን ቅጣቱ ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን እንደተራዘመ በኖርዌይ ለሚገኝ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ገልጸዋል።

    መንግሥት ሊፈጽመው ስለሚችል የሞት ቅጣት ጥያቄ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ “ስቅላት ከጥያቄ ውጪ ነው” ብለዋል። “ዛሬ ወይም ነገ ምንም ስቅላት አይኖርም” ሲሉም ተናግረዋል።

  13. አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የተወሰኑ ወታደሮቻቸውን ከኳታር ማስወጣት ጀመሩ

    አል-ኡዴይድ በመካከለኛ ምስራቅ ትልቁ የአሜሪካ የጦር ካምፕ

    የፎቶው ባለመብት, TSGT Scott Reed, USAF

    የምስሉ መግለጫ, አል-ኡዴይድ በመካከለኛ ምስራቅ ትልቁ የአሜሪካ የጦር ካምፕ ነው

    ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኳታር አል-ኡዴይድ ከሚገኘው የአየር ኃይል ካምፕ የተወሰኑ ወታደሮቻቸውን ማስወጣት ጀመሩ። በተያያዘ ዜና ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ኢራን ላይ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንደተናገሩት የተወሰኑ ወታደሮች እንዲወጡ የተደረገው “ለቅድመ ጥንቃቄ” በሚል ነው። ቢቢሲ በበኩሉ የተወሰኑ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ከኳታር እየወጡ እንደሆነ መረዳት ችሏል።

    የኳታር መንግሥት መግለጫ እርምጃው “በቀጣናው የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ የተወሰደ ነው” ይላል።

    ቴህራን የሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ ለጊዜው የተዘጋ ሲሆን ዶሀ የሚገኘው ኤምባሲ ደግሞ ሠራተኞቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

    የአሜሪካ ፌዴራል አቪየሽን ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው ኢራን ከሐሙስ ንጋት ጀምሮ ማንኛውም አውሮፕላን በአየር ክልሏ እንዳይንቀሳቀስ አግዳለች። ኤር ኢንዲያ እና የጀርመኑ ሉፍታንዛ የበረራ አቅጣጫ ለውጥ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    በኢራን የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ እስካሁን 2400 ሰዎች እንደተገደሉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች አስታውቀዋል።

  14. የኢራን ጥቃት ያሰጋት ኳታር የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ መውሰዷን አረጋገጠች

    ኳታር በግዛቷ ባለው የአሜሪካ አል ኡዴይድ አየር ኃይል ሰፈር ለሚገኙ ዜጎቿ ደኅንነት ስትል አንዳንዶቹን ወደ ሌሎች ቦታዎች ማዘዋወርን ጨምሮ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ መውሰዷን አረጋገጠች።

    የኳታር ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ማዕከል እንዳለው የተወሰደው እርምጃ መንግሥት ዜጎቹን እና ነዋሪዎችን፣ ቁልፍ ወታደራዊ ተቋማትን ደኅነንት ለመጠበቅ ከሚወስዳቸወቅ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው። ለውጦች የሚኖሩ ከሆነ በይፋዊ መንገዶች በኩል እንደሚገለጽም አመልክቷል።

    ከዚህ የኳታው ውሳኔ ከሰዓታት ቀደም ብሎ ኳታር ውስጥ በሚገኘው የአየር ኃይል ሰፈር ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወደታሮች ለቅቀው እንዲወጡ እንደተናገራቸው ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

    ኳታር ውስጥ ያለው አል ኡዴይድ የአየር ኃይል ሰፈር አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ካሏት ወታደራዊ ሰፈሮች ሁሉ ትልቁ ሲሆን፣ 10 ሺህ የሚደርሱ የአሜሪካ ወታደሮች ሰፍረውበታል።

    ባለፈው ዓመት ሰኔ እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ኢራን የጦር ሰፈሩን ዒላማ ደያረገ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።

    አሁንም አሜሪካ እየዛተችው እንዳለው በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በዚህ ለኢራን ቅርብ በሆነው የአሜሪካ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ የአጸፋ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች ተብሎ ተሰግቷል።

  15. ኢራን ጎረቤቶቿን ስታስጠነቅቅ፤ አሜሪካ ለወታደሮቿ መመሪያ ሰጠች

    የኢራን ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ወታደሮች

    አሜሪካ በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ በመቃወም ኢራን ላይ እርምጃ እንደምትወስድ እየገለጸች ባለበት በአሁኑ ሰዓት፤ ኢራን ጎረቤቶቿን አስጠነቀቀች።

    አሜሪካ ደግሞ በኢራን ዙሪያ ባሉ አገራት ለሚገኙ ወታደሮቿ የጥንቃቄ መመሪያ ማስተላለፏን ምንጮች አስታውቀዋል።

    አሜሪካ ጥቃት የምትፈጽምባት ከሆነ ኢራን በጎረቤት አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን እንደምትመታ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ዋነኛ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ውስጥ ያሉ ወታደሮች ለቅቀው እንዲወጡ እንደተመከሩ ሦስት ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ባለፈው ዓመት አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ኢራን ኳታር በሚገኘው አል ኡዴይዳ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ ጥቃት ከመፈጸሟ በከሰዓታት በፊት ወታደሮቿ ከጦር ሰፈሩ እንዲወጡ አድርጋ እንደነበር ይታወሳል።

    በኢራን እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ምክንያት ከሁለት ሺህ በላይ ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በተደጋጋሚ ሲዝቱ ቆይተዋል።

    ኢራንም በበኩሏ ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ አጸፋውን እንደምትፈጽም ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች።

  16. በተቃውሞ የተሳተፉትን በሞት መቅጣት

    በ2022 ተቃውሞ የተገደለችው ወጣት ፎቶን የያዙ ተቃዋሚዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በ2022 ተቃውሞ የተገደለችው ወጣት ፎቶን የያዙ ተቃዋሚዎች

    ኢራንን እያናወጠ ካለው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ መንግሥት ኢርፋን ሶልታኒ የተባለውን ተቃዋሚ ዛሬ ረቡዕ በሞት ይቀጣል ተብሎ እየተዘገበ ነው።

    ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ተቃውሞ ሰበብ ቢያንስ 12 ወንዶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ሞት ተፈርዶባቸው ተገድለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2022 ማህሳ አሚኒ የተባለች ወጣት ሂጃብ በአግባቡ አልለበሰችም በሚል በሞራል ፖሊሶች ተይዛ በተፈጸመባት ድብደባ መሞቷን በመቃወም ነበር ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።

    ሰኞ ዕለት የኢራን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጎላምሆሴን ሞህሴኒ-ኤጄ በተቃውሞ ወቅት ጥቃት የተፈጸመው "የጦር መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች" ነው በማለት ተቃዋሚዎችን ከስሰዋል።

    በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ተቃዋሚዎቹ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ "ግልጽ ድጋፍ" እንደተደረገላቸው በመጥቀስ፣ የኢራን መንግሥት "ካለምንም ርህራሄ" እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

    የሰብአዊ መብት ቡድኖች እንደሚሉት በተቃውሞ ሰበብ የሞት ቅጣት የተፈጸመው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ኢስፋህን ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ነው።

    ግለሰቡ ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው ተቃውሞ ወቅት ፈጣሪን በመቃወም እና የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባልን ገድሏል በሚል ተከስሶ ነው በሞት የተቀጣው።

  17. ቻይና በኢራን የሚኖር የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደማይኖረው ገለፀች

    በኢራን ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዛታቸውን ተከትሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በኢራን የውስጥ ጉዳይ የሚኖር የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም” አለ።

    ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን በቁጥጥር ሥር ያዋለቻቸውን ተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ ግድያ የምትፈጽም ከሆነ “በጣም ከባድ እርምጃ” እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ “ድጋፍ እየመጣላችሁ ነው” በማለት ሠልፈኞቹ ተቃውሟቸውን እንዲቀጥሉ አበረታትተዋል።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በመግለጫቸው ላይ “ቻይና በዓለም አቀፍ ግንኙነቷ ማስፈራሪያን ወይንም ኃይልን መጠቀምን አትደግፍም” ብለዋል።

    ቻይና ከዚህ ቀደምም በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ትቃወማለች።

    በኢራን የኑሮ ውድነት ምክንያት የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሠልፍ ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን እስካሁን ድረስ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከ2400 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል።

    በኢራን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ኢንተርኔት ከተቋረጠ ከ132 ሰዓት በላይ እንደሆነ ኔትብሎክስ ይፋ አድርጓል።

  18. 2976 ዓመትን እያከበሩ የሚገኙት የሰሜን አፍሪካ ሕዝቦች

    ባለፉት አስርት ዓመታት የአማዚጋ ባሕል እና ቋንቋ ከፍተኛ ዕውቅና አግኝቷል

    የፎቶው ባለመብት, APP/NurPhoto via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ባለፉት አስርት ዓመታት የአማዚጋ ባሕል እና ቋንቋ ከፍተኛ ዕውቅና አግኝቷል

    ከአብዛኛው የዓለም ሕዘብ 1000 ዓመት ይቀድማሉ። 2976 ዓመትን እያከበሩ የሚገኙት የአማዚግ ሕዝቦች መኖሪያቸውን በሰሜን አፍሪካ ነው።

    የቀን አቆጠጣራቸው የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ950 የግብፁ ንጉሥ ሼሾንቅ ዙፋኑን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

    የአማዚግ (Amazigh) አዲስ ዓመት ዬናይር (Yennayer) በመባል የሚታወቅ ሲሆን የሚከበረውም በጥር 4 እና 6 መካከል ነው

    ይህ ደግሞ የሚወሰነው የአማዚግ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ መሠረት ነው።

    በአልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ሊቢያ የሚኖሩት አማዚጎች አዲስ ዓመታቸውን ቤተሰብ ተሰባስቦ፣ ችቦ ለኩሰው፣ ባሕላዊ ሙዚቃቸውን እየዘፈኑ እና እየጨፈሩ ያከብሩታል።

    መልካም አዲስ ዓመት ወይም “አሴጋስ አሜጋስ” የሚሉ ደውሎች በመንደሮቻቸው እና ከተሞቻቸው ይሰማሉ።

    በዓሉን በባሕል አልባሳት ደምቀው ያሳልፉታል።

    ዬናይር በሞሮኮ እና አልጄሪያ ሕዝባዊ በዓል ነው

    የፎቶው ባለመብት, APP/NurPhoto via Getty Images

    አማዚጋ ማለት “ነጻ ሕዝብ" ወይም “የተከበረ ሕዘብ” ማለት ነው።

    የሰሜን አፍሪካ ቀደምት ሕዝቦች እነደሆኑ የሚታመነው አማዚጋዎች ምን ያህል እንደሆኑ ይፋዊ የሆነ የሕዝብ ቁጥር መረጃ ስለሌለ አይታወቅም።

    ነገር ግን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት በሰሜን አፍሪካ እንደሚኖሩ ይታመናል።

    አልጄሪያ እና ሞሮኮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማዚግ ሕዝቦች ይኖራሉ።

    በሞሮኮ ብቻ 40 በመቶ የሚሆኑት የአማዚግ ሕዝቦች ይገኛሉ።

    የዚህ ሕዘብ አዲስ ዓመት ወይም ዬናይር የቤተሰብ መሰባሰቢያ፣ አማዚጋዎች ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ጥልቅ መስተጋብር ማጠናከሪያ ተደርጎ ይከበራል።

    በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የአማዚግ ሕዝቦች የሚመገቧቸው ባሕlኣዊ ምግቦች እንደሚኖሩበት አካባቢ ይለያያሉ።

    በ7ኛው ክፍለ ዘመን በመላው ሰሜን አፍሪካ አረቦች ወረራ ሲፈጽሙ የአማዚግ ቋንቋ እና ባሕል አደጋ ላይ ወደቀ።

    በሊቢያ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ ቋንቋው በትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ አገደው የነበረ ሲሆን ከፍተኛ ጥረቶች ተደርጎ እገዳው ተነስቷል።

    እአአ በ2011 ደግሞ በሞሮኮ ቋንቋው እውቅና አግኝቷል።

  19. የፈረንጆቹ 2025 ለዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች የከፋ ዓመት ነበር ተባለ

    ሩሲያ በዩክሬን በፈጸመችው ጥቃት ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት የፈረንጆቹ 2025 ለዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች አስከፊው ዓመት እንደነበር ገለፀ።

    በ2025 በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት 2,514 ሰዎች መገደላቸውን በዩክሬን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪ አስታውቋል።

    እአአ በ2023 ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1,974 ነበር።

    በየዓመቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው አካላዊ ጉዳት እየጨመረ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ጨምሮ አስታውቋል።

    ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በምዕራብ ቴርኖፒል ግዛት በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሕጻናትን ጨምሮ 38 ሰዎች የሞቱበት ጥቃት አስከፊ ከነበሩት መካከል አንዱ ነበር ተብሏል።

    ሐሙስ ዕለት ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በካርኪዝ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

    አክለውም ጥቃቱ በቀዛቃዛ የአየር ሁኔታ ውስጥ "በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች" ከኤሌትሪክ ኃይል ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።

    ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የተገደሉት እና የቆሰሉ ሰላማዊ ዜጎች አጠቃላይ ቁጥር በ2024 ከነበረው በ31 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነበር ተብሏል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ይህ ቁጥር በ2023 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ70 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሷል።

    እአአ በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ 8,423 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 12,670 ደግሞ ቆስለዋል።

  20. አሜሪካ፣ በሶማሊያ በሚገኙ የአይሲስ እና አል ሸባብ ዒላማዎች ላይ ተከታታይ ጥቃቶች ፈጸመች

    የአል ሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) ማክሰኞ ዕለት ጦሩ ከሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን የአልሸባብ ታጣቂዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናገረ።

    አፍሪኮም ጥቃቱ የተፈጸመው ቡድኑ “በአሜሪካ፣ የአሜሪካ ጦር እና አሜሪካውያን ላይ ስጋት ለመፍጠር ያለውን አቅም ለማዳከም ነው" ብሏል።

    ጥር 3 እና 5/2018 ዓ.ም. እንዲሁ በአይሲስ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    አሜሪካ በአይሲስ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመችባቸው አካባቢዎች መካከል በፑንትላንድ የሚገኘው የጎሊስ ተራራ ይገኝበታል።

    ጥር 1 2018 ዓ.ም. እንዲሁም ከሞቃዲሹ 154 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ቡር ሄይቦ በሚገኝ የአልሸባብ ዒላማ ላይ ድብደባ መፈጸሙ ተገልጿል።

    የአፍሪኮም ዕዝ ጥር 2 እና 3 /2018 ዓ.ም. በተጨማሪ “ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ጋር በጥምረት" ጥቃቶች መፈጸሙን ገልጿል።

    እስካሁን ድረስ በጥቃቱ ምን ያህል ታጣቂዎች እንደሞቱ ወይንም ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባለ ነገር የለም።

    አፍሪኮም በጥር ጥር 4/2018 ዓ.ም. ተጨማሪ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አስታውቋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተደጋጋሚ በሶማሊያ በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን በገለልተኝነት ሁኔታውን የሚከታተሉ ተቋማት ዘግበዋል።

    ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የአፍሪኮም አዛዥ የሆኑት ጄነራል ማይክል ኢ. ላንግሊ በሴኔት ፊት ቀርበው በአፍሪካ የሚገኙ የጂሃድ ቡድኖች አሜሪካ ላይ ስጋት መደቀናቸውን ተናግረው ነበር።

    “አይሲስ እና የአል ቃይዳ ቡድኖች እየተስፋፉ ስለመሆኑ ተጨባጭ መረጃ አለን፤ በአሜሪካ ላይ ቀጥተኛ ስጋት ይደቅናሉ” ብለዋል።

    አልሸባብ በሶማሊያ መንግሥት ላይ እአአ ከ2007 ጀምሮ ጦርነት ያወጀ ሲሆን በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ የሚገኙ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ይገኛል።

    በሶማሊያ የሚገኘው አይሲስ ግን በቁጥሩ አነስተኛ ሲሆን በብዛት የሚንቀሰቀሰውም በፑንትላንድ ተራራማ አካባቢዎች ነው።