የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ባለሥልጣኖቻቸውን ዒላማ ማድረጉን ተናገሩ

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በዋይት ሐውስ ዘጋቢዎች የእራት ግብዣ ላይ ተኩስ ከፍቶ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ለመርማሪዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዒላማው እንደነበሩ መናገሩን ዘገበ። ሲቢኤስ በስም ያልጠቀሳቸውን ምንጮች በእራት ግብዣው ላይ ከአምስት እስከ ስምንት የሚደርሱ ጥይቶች ተተኩሰዋል ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን አምባሳደር አሜሪካ በቀጣይ ድርድሮች ተጨባጭ አቋም መያዝ አለባት አሉ

    ጄኔቫ ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን አምባሳደር ሆኑት አሊ ባህሬኒ በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል የሚደረጉ ድርድሮች እንዲቀጥሉ የሚፈለግ ከሆነ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ማብቃት እንዳለበት ተናገሩ።

    ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት አምባሳደሩ፤ አሜሪካ ጣለችው እገዳ “ከፍተኛ” የተኩስ አቁም “ጥሰት” መሆኑን ገልጸዋል።

    በድጋሚ ድርድር ውስጥ በሚገባበት ወቅት “አሜሪካ ለኢራን መብቶች እና ለኢራን ምክንያታዊ ጥያቄዎች እውቅና በመስጠት ተጨባጭ አካሄድ ልትከተል” እንደሚገባ ተናግረዋል።

    ቴህራን ድርድር የምታደርገው “ሌላኛው ወገን ኢራንን ለማጥቃት ተጨማሪ ዝግጅት” የሚያደርግበት ዕድል ለመስጠት እንዳልሆነም አክለዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮች ትዕዛዝ የሚሰጣቸው ከሆነ በድጋሚ ዘመቻ ለመክፈት ዝግጁ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

    አምባሳደሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቀጣይ እርምጃ ምን መሆን አለበት የሚለውን በተመለከተ በኢራን ከፍተኛ አመራሮች መካከል ክፍፍል ተፈጥሯል መባሉን ውድቅ አድርገዋል። ይልቁንም ችግር የሆነችው “ሙሉ ተቃርኖ” እና ክፍፍል ውስጥ ያለችው አሜሪካ መሆኗን ተናግረዋል።

  2. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ፈንጂ ማጥመድ “የተኩስ አቁም ጥሰት” ነው አሉ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ፈንጂ ለማጥመድ የምትሞክር ከሆነ “እንደ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት” እንደሚቆጠር እና በዚያው አግባብ ምላሽ እንደሚሰጠው ተናገሩ።

    መከላከያ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ “ያለ ማመንታት እና ይቅርታ” እያስፈጸመች መሆኑን ገልጸዋል። አሜሪካ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በአጠቃላይ 34 መርከቦችን ማስመለሷንም ጠቅሰዋል።

    ያለ አሜሪካ ፈቃድ የትኛውም መርከብ በወሽመጡ አያልፍም ሲሉ የተናገሩት ሄግሴት “ተጨማሪ [መርከቦችን] እንይዛለን” ብለዋል።

    ዋሽንግተን ይህንን እገዳ የጣለችው ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ ጉዞን ከልክላ ከአንድ ወር በላይ ከቆየች በኋላ ነው። ኢራን ባለፉት ቀናት ሁለት መርከቦች ላይ ተኩስ እንደከፈተች እና እንደያዘች ተገልጾ ነበር።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት የተያዙት የአሜሪካ እና እስራኤል መርከቦች አለመሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም “ፈጣን ጀልባ ከሽጉጥ እና የተሳሳተ ዓላማ ጋር የያዘ ሰው በሙሉ ሊያደርገው ይችላል” ሲሉ የኢራንን እርምጃ አጣጥለዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በውሃ መተላለፊያው ላይ ፈንጂ ለማጥመድ ወይም የመርከቦችን ጉዞ ለማስተጓጎል የሚሞክሩ የኢራን ፈጣን ጀልባዎችን እንዲያወድም ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴትም “ያለ ምንም ማመንታት ለማውደም እንተኩሳለን” ብለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ፈንጂ እንደምታጠምድ ስለመዛቷም ተጠይቀዋል። “በግድ የለሽነት እና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ተጨማሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ የሚደረግ ሙከራ ካለ ምላሽ እንሰጠዋለን። የተኩስ አቁም ጥሰት ነው” ብለዋል።

    ኢራን አሁንም ቢሆን “ጥሩ እና ብልህ ስምምነት” ላይ ለመድረስ ዕድል እንዳላት ተናግረዋል። ኢራናውያን “በብልህነት ለመምረጥ መስኮቱ ክፍት እንደሆነ ያውቃሉ” ያሉት ሄግሴት፤ ማድረግ ያለባቸው “ትርጉም ባለው እና ሊረጋገጥ በሚቻል መልኩ የኒውክሌር መሣሪያን መተው” ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

  3. የኢራን ልዑክ ዛሬ ለንግግር ወደ ፓኪስታን ይጓዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ

    የኢራን ተደራዳሪ ልዑክን ከሚመሩት አንዱ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ዛሬ ማታ ኢስላማባድ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓኪስታን መንግሥት ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስ በበኩሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚጓዙት አነስተኛ ቁጥር ያለው አባላትን የያዘ ቡድን አስከትለው እንደሆነ እና ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ንግግር ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘግቧል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ የተሰማው ዛሬ ከፓኪስታን ባለሥልጣናት ጋር ንግግር ማድረጋቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ከፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የአገሪቱ ጦር ኃይሎች አዛዥ ጋር በነበራቸው ንግግር ከአሜሪካ ጋር ስለሚደረገው ግጭት ተወያይተዋል።

    በንግግራቸው ወቅት “ከተኩስ አቁም ጋር ተያያዙ ጉዳዮች” እንደተነሱ የተገለጸ ሲሆን ተኩስ አቁሙ ግን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ስላለው ይሁን በሊባኖስ እና እስራኤል መካከል ስለተፈጸመው በግልጽ አልተጠቀሰም።

    አሜሪካ እና ኢራን ሁለተኛ ዙር ንግግር የማድረጋቸው ጉዳይ እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጥበትም በአሸማጋይነት እየሰራች ያለችው ፓኪስታን ግን ድርድሩን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆና ቀጥላለች።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ፓኪስታን ያደርጉታል ተባለውን ጉዞ በተመለከተ ከኢራንም ሆነ ከአሜሪካ በኩል ይፋዊ ማረጋገጫ አልተሰጠም።

  4. እስራኤላውያን በጥርጣሬ የሚመለከቱት የተኩስ አቁም ስምምነት

    በሊባኖስ እንደታየው በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ እስራኤል ውስጥ የጎላ ክፍፍል የለም። ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል በሚለው ላይ ግን ብዙ ጥርጣሬ አለ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእስራኤል-ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት መራዘሙን ከማወጃቸው በፊት፣ ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል የድንበር ከተማ ነዋሪዎች ላይ የሮኬት ጥቃት ፈጽሟል።

    በርግጥ ያስወነጨፋቸው ሮኬቶች ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሱም።

    በሰሜን አካባቢ የሚኖሩ እስራኤላውያን አሁንም በአደጋ እና እርግጠኛ ባለመሆን ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ በመናገር ለጊዜው መደበኛ ሕይወታቸውን ማቆማቸውን ተናግረዋል።

    “ስለተኩስ አቁም ስምምነት ከፍተኛ ጥርጣሬ አለን” ሲሉ የኪርያት ሽሞና የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ገልጸዋል።

    “አልፎ አልፎ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች መደበኛ እንዲሆኑ ፈቃደኛ አንሆንም” ብለዋል።

    በካፋር ጊላዲ ነዋሪ የሆኑት ኒሳን ዜቪ ደግሞ “ይህ የይስሙላ እንቅስቃሴ ብቻ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ከፍተኛ ስጋት አላቸው፣ ሄዝቦላህ ራሱን እያስታጠቀ፣ ሊባኖስን ለመቆጣጠር እና እስራኤልን ለመጉዳት ያለውን ፍላጎት እንደገና እያደራጀ እና እየቀጠለበት” ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    እስራኤል ከሊባኖስ ጋር በምትዋሰንበት የሜቱላ ድንበር አቅራቢያ የሚኖሩት ሊያት ኮሄን ራቪቭ በበኩላቸው “እዚህ ጦርነት የሚፈልግ ማንም የለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    “የተኩስ አቁም ስምምነቱ በደህንነት እውነታ ላይ ለውጥ በማምጣት ስጋቱን በትክክል ማስወገድ እና የተለመደው ሕይወት ሲያስቀጥል ካላሳየ መፍትሄ አይሆንም። መዘግየት ብቻ ነው” ብለዋል።

  5. ኢራን እና ፓኪስታን “ከተኩስ አቁሙ ጋር በተያያዘ” ተወያዩ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በግጭቱ ዙሪያ መነጋገራቸው ተሰማ።

    አባስ አራጋቺ በቴሌግራም ላይ ባጋሩት መግለጫ ከፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር እንዲሁም ከመከላከያ አዛዡ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

    በንግግራቸው “በቀጠናዊ ሁኔታዎች እና በተኩስ አቁሙ ዙሪያ” መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

    አራጋቺ ከፓኪስታን ባለሥልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ያነሱት ከአሜሪካ ጋር ስላላቸው የተኩስ አቁም ይሁን ወይም እስራኤል እና ሊባኖስ ስለደረሱበት ስምምነት ያሉት ነገር የለም።

    የፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ሊደረግ ለሚችል ሁለተኛ ዙር የሰላም ውይይት ዝግጁ ሆና እየጠበቀች ቢሆንም መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን ድረስ የታወቀ ነገረ የለም።

  6. የኢራን አመራሮች አንድነታቸውን የሚያሳይ መልዕክት አስተላለፉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን አዳዲሶቹን መሪዎች “በሁከት” እና “በከባድ ሁኔታ የተከፋፈሉ ” ናቸው በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ገልጸዋል።

    ቴህራን ደግሞ እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ ለሁሉም የኢራን የሞባይል ተጠቃሚዎች የጽሑፍ መልዕክት አስተላልፋለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ልዩነትን ለመዝራት” ላደረጉት ጥረት ምላሽ ለመስጠት ከፕሬዝዳንቱ፣ ከፓርላማ አፈ ጉባኤው፣ ከፍትህ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተላከ “የጋራ መልእክት” ነው ተብሏል።

    “ኢራን ውስጥ አክራሪ ወይም ለዘብተኛ የሚባል ነገር የለም” ይላል መልዕክቱ። “ሁላችንም ኢራናውያን እና አብዮታዊ ነን… አንድ አገር፣ አንድ ሃሳብ” ይላል።

    ባለፈው ሳምንት በኢራን ሚዲያዎች ላይ በአንዳንድ ጥቃቅን ስልታዊ ጉዳዮች የአለመግባባት ምልክቶች በኢስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተገናኘ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኅን ላይ ታይቷል።

    መልዕክቱ ከአሜሪካ ጋር በሚደረጉ ድርድሮች ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ ዋና ዋና ውሳኔዎች ላይ መግባባት እንደሚሰፍን ለማሳየት የታሰበ ነው።

    ይህም የኢራንን ጉዳይ በርቀት ለሚከታተሉ ለሳምንታት በጦርነት እና በከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች እና አዛዦች ግድያ ምክንያት ስለመጣው ስርዓት የሚጋሩት ሃሳብ ነው።

    አሁን ብዙ ውሳኔ ሰጪዎች አሉ። አንዳንዶቹ የበለጠ ተራማጅ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ የበለጠ አክራሪ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ።

    ሆኖም ሁሉም ከኒውክሌር ፕሮግራሙ እስከ ሆርሙዝ ወሽመጥ ድረስ ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ቀይ መስመር ግልጽ ነው።

  7. የአውሮፓ ኅብረት በኢራን የሰላም ውይይት ውስጥ የኒውክሌር ባለሙያዎች እንዲሳተፉ ጠየቀ

    የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ የኒውክሌር ባለሙያዎች በኢራን የሰላም ድርድር ውስጥ ካልተሳተፉ ከቴህራን የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች "የበለጠ አደገኛ" ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናገሩ።

    ካጃ ካላስ በቆጵሮስ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ማንኛውም ስምምነት ከዚህ በፊት ከተደረጉት ደካማ የመሆን አደጋ አለው ብለዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር እአአ በ2015 የተፈራረመችው ስምምነትን የተቃወሙት ትራምፕ አገራቸውን ማስወጣታቸው ይታወሳል።

    በዚህ ስምምነት መሠረት ኢራን ሚስጥራዊ የሆኑ የኒውክሌር እንቅስቃሴዎቿን ለመገደብ እና ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ወደ ቴህራን እንዲገቡ በመፍቀድ በምላሹ የተጣሉባት የኢኮኖሚ ማዕቀቦቹ እንዲነሱ ተስማምታለች።

    "ውይይቱ ስለ ኒውክሌር (ፕሮግራሙ) ብቻ ከሆነ እና በጠረጴዛው ዙሪያ የኒውክሌር ባለሙያዎች ከሌሉ፣ ከቀደመው ጋር ሲነጻጸር ደካማ የሆነ ስምምነት ላይ እንደርሳለን" ሲሉ ካላስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    “እናም በቀጣናው ውስጥ ያሉት ችግሮች፣ የሚሳዔል ፕሮግራሞች፣ ድጋፍ ስለምትሰጣቸው ታጣቂዎች፣ እንዲሁም በአውሮፓ ውስጥ ያሉ የበይነ መረብ እንቅስቃሴዎች ካልተፈቱ፣ የበለጠ አደገኛ የሆነች ኢራን ትሆናለች” ሲሉ ተናግረዋል።

  8. የተኩስ አቁም የሊባኖስ መንግሥት ጥያቄ እንደነበር የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ገለጹ

    አንድ የሊባኖስ ከፍተኛ ባለሥልጣን መንግሥት የአገሪቱን ጦር በማሰማራት ሄዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት “ወሳኝ እርምጃዎች” ሊወስድ እንደሚችል ገለፁ።

    ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ጠቅልሎ መውጣት ይኖርበታል ብለዋል።

    የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ፖል ሞርኮሰ ለቢቢሲ ኒውስዴይ የተኩስ አቁሙ ለሦስት ሳምንታት እንዲራዘም መንግሥታቸው ጠይቆ እንደነበር ተናግረዋል።

    ከተኩስ አቁሙ ባሻገር “እስራኤል በሊባኖስ ላይ በአየር፣ በባሕር ወይም በእግረኛ ጦሯ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች እንዲቆም” የሚል እንደነበረበት አስረድተዋል።

    በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ቤይሩት የሄዝቦላህ እና “ሌሎች ከመንግሥት ውጪ የሆኑ ታጣቂዎች” በእስራኤል ዒላማዎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል “ተጨባጭ እርምጃ” መውሰድ አለባት።

    ሞርኮስ የሊባኖስ መንግሥት የአገሪቱን ጦር በማሰማራት እና ወታደሮች “በሊባኖስ የመሣሪያ የበላይነት እንዲኖረው ለማድረግ”፤ “ተጨባጭ እርምጃዎችን” መውሰዱን ተናግረዋል።

    ነገር ግን መንግሥት ይህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት መውሰድ የጀመራቸው እርምጃዎችን የእስራኤል “ወረራ” እና “ጥቃቶች”፤ “ባሉ ለውጦች ላይ እንቅፋት” መሆናቸውን አብራርተዋል።

    አክለውም “እነዚያን ተጨባጭ እርምጃዎች ሠራዊቱን ወደ ድንበር በማሰማራት ዳግም ለመጀመር ፈቃደኞች ነን” ብለዋል።

  9. ትራምፕ ኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይጠቀሙ ተናገሩ

    አሜሪካ በመደበኛ ሁኔታ ወታደራዊ ዓላማዎቿን አሳክታለች ያሉት ትራምፕ ኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይጠቀሙ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ይጠቀሙ እንደሆን ከጋጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ለምን እፈልገዋለሁ” በማለት ጥያቄውን “የማይረባ” ብለውታል።

    አክለውም “እኛ ያለ ኒውክሌር ጦር መሣሪያን ሙሉ በሙሉ ካጠፋናቸው ለምን እጠቀማለሁ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

    "የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማንም ሰው እንዲጠቀምበት ፈጽሞ መፍቀድ የለበትም።"

  10. በመንግሥታቱ ድርጅት የእስራኤል ልዑክ የተኩስ አቁሙ ግጭትን ስለማስቆሙ እርግጠኛ አይደለሁም አሉ

    በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የእስራኤል አምባሳደር በአገራቸው እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከሄዝቦላህ ጋር የሚኖረውን ግጭት ስለማስቆሙ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ተናገሩ።

    አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ለሲኤንኤን “የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህ ላይ ምንም ቁጥጥር የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።

    "ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማደናቀፍ ሮኬቶችን እየተኮሰ ነው፤ እስራኤልም አጸፋውን ልትመልስ ይገባል። ስጋት ባየን ቁጥር እርምጃ እንወስዳለን።"

    አምባሳደሩ አስተያየታቸውን የሰጡት የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች በዋይት ሐውስ ተገናኝተው ከተወያዩ እና የተኩስ አቁሙን ለሦስት ሳምንታት ካራዘሙ በኋላ ነው።

    ስምምነቱን በመጥቀስ “መቶ በመቶ የሚሆን አይመስለኝም” ያሉት አምባሳደሩ “የሊባኖስ ጦር ቢችል እና የተኩስ አቁሙን አስፈጽሞ ባይ. . .ተስፋ አደርጋለሁ ” ሲሉ ተናግረዋል።

  11. ሊቀ ጳጳስ ሊዮ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ሰላም ድርድሩ እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ

    ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም ወዳለመው የሰላም ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ።

    ጳጰሱ አክለውም ግጭቱ “በኢራን ውስጥ ንፁኃን ዜጎችን በሙሉ ስቃይ ውስጥ ጥሏቸዋል” ብለዋል።

    ሊቀ ጳጳሱ ይህን አስተያየት የሰጡት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስት ከገቡ በኋላ ነው። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት የሚቃወሙትን ጳጳሱን ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት አብጠልጥለዋቸዋል።

    አራት የአፍሪካ አገሮችን ጎብኝተው ወደ ሮም በተመለሱበት ወቅት “ለሰላም የሚደረገውን ውይይት እንዲቀጥል፣ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለማስፈን፣ የጦርነትን ስጋት ለማስወገድ እና ዓለም አቀፍ ሕግን ለማክበር የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    "እንደ መጋቢ፣ ጦርነትን መደገፍ አልችልም፤ ሁሉም ሰው ከጥላቻና ከመለያየት ሳይሆን ከሰላም ባህል የሚመጡ መልሶችን እንዲፈልግ ማበረታታት እፈልጋለሁ።"

    ባለፈው ዓመት ሊባኖስ በሄዱበት ወቅት "ፖፕ ሊዮ እንኳን ደህና መጡ" የሚል ወረቀት ይዞ ፎቶ የተነሳውን ሙስሊም ሊባኖሳዊ ሕፃን ምስል አሳይተው “በዚህ ጦርነት [ሕጻኑ] ተገድሏል” ብለዋል።

  12. በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በሦስት ሳምንት ተራዘመ

    ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት ሳምንት መራዘሙን አስታወቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም በሦስት ሳምንት መራዘሙን አስታወቁ።

    በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ውይይት ላይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዩ መገኘታቸው ታውቋል።

    ውይይቱ “በጥሩ ሁኔታ” ተካሄዷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ “ዩናይትድ ስቴትስ ሊባኖስ ራሷን ከሄዝቦላህ መከላከል እንድትችል በጋራ ትሠራለች” ብለዋል።

    የዚህ “ታሪካዊ ውይይት” ተሳታፊ መሆን “ትልቅ ክብር” እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ወደፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሊባኖሱን ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውንን ለመቀበል በጉጉት እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል።

    ትራምፕ፣ የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ዋይት ሐውስ እንደሚመጡ ተናግረው አገራቸው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ማደራደር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

    "ስለ ሄዝቦላህ ማሰብ አለባቸው" ያሉት ትራምፕ፣ "በዚያች አገር ነገሮችን ለማስተካከል ከሊባኖስ ጋር እንሰራለን" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

    አክለውም “ኢራን ውስጥ ከምንሰራው ጋር በአንድ ላይ እንዲሆን ማድረግ አስደናቂ ነገር ይመስለኛል” ብለዋል።

    የሁለቱም አገራት ከፍተኛ ተደራዳሪዎቸ የተኩስ አቁሙ በመራዘሙ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

    በአሜሪካ የሊባኖስ አምባሳደር ናዳ ሃማዴህ ሞዋድ፣ በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ዬቺኤል ሊተር፣ በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሚሼል ኢሳ እና በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቢ እያንዳንዳቸው ትራምፕን በድርድሩ ውስጥ ላበረከቱት ሚና አወድሰዋል።

    “ክቡር ፕረዚዳንት፡ በእርስዎ መሪነት ኢራን በጣም ተዳክማለች፤ ሄዝቦላህን የማዳከም እና ሊባኖስን ከወረራ ነፃ የማውጣት ዕድሉ እውን ነው” ያሉት ሌይተር፣ እስራኤል እና ሊባኖስ“ሄዝቦላህ ከተባለ ክፉ ተጽእኖ” ለማፅዳት ዓላማቸው አስተሳስረዋል ብለዋል።

    ሃክካቢ ሄዝቦላህን በሰፈር ውስጥ በሁሉም ሰው መስኮት ላይ ድንጋይ ከሚወረውር ልጅ ጋር በማመሳሰል ገልጸውታል።

    ሕፃኑን ማስቆም ከተቻለ በኋላ፣ እንደ ሊባኖስና እስራኤል ያሉ ሌሎች ጎረቤቶች በሰላም ይኖራሉ ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

  13. ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ስለሰነዘሩት ዛቻ ሲጠየቁ “ምንም ነገር ብል፤ ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ቢቢሲ በኢራን ላይ ስለሰነዘሩት ዛቻ ሲጠይቃቸው “ምንም ቢሆን የማደርገው፣ በጣም ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል” ሲሉ መለሱ።

    የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ኤዲተር ሳራ ስሚዝ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረገችው አጭር የስልክ ቃለ መጠይቅ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በመቃወም በሰጡት ማስጠንቀቂያ “ዛሬ ምሽት ሙሉ ስልጣኔ ይጠፋል” ማለታቸውን አስታውሳለች።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምላሻቸው “ሌላኛው ወገን ከስምምነት ለመድረስ እየተሟሟተ ነው” ካሉ በኋላ “ስለዚህ ምንም ነገር ብል፣ ወይም ምንም ነገር ባደርግ ጥሩ እየሰራ ይመስለኛል። በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

    ትራምፕ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)ን በሚመለከት ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት “ፈጽሞ አልፈልጋቸውም ነበር” ካሉ በኋላ “ነገር ግን እዚያ መገኘት ነበረባቸው” ብለዋል።

    ቢቢሲ ኔቶ ጦርነቱን እንዲቀላቀል ለምን እንደፈለጉ ሲጠይቃቸው፣ “ምክንያቱም ይሳተፉ እንደሆን እና እንዳልሆነ ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    አሜሪካ ምንጊዜም ከዩኬ እና ኔቶ ጎን መሆኗን የጠቀሱት ትራምፕ፣ ዩኬ “ትንሽ እንኳ ጥረት፤ ቢያንስ ጥሩ ቃል” አለመሞከሯን በመጥቀስ ተችተዋል።

    አክለውም "ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡ ብዙ ሰዎች" አገራቸው በጦርነቱ ውስጥ ላለመሳተፍ መወሰኗ "በሚገርም ሁኔታ መጥፎ ውሳኔ" እንደሆነ መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ለምታካሄደው ጦርነት ለ"መከላከያ" የአየር ጥቃቶች ብቻ እንድትጠቀም ፈቅዳለች።

    ቀደም ሲል ትራምፕ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ጋር ያላቸው ግንኙነት በተመለከተ ሲናገሩ "የሰሜን ባህርን ከከፈተ" እና "የስደት ፖሊሲያቸው ጠንካራ ከሆነ" "ያገግማል" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    ነገር ግን "ይህንን ካላደረገ፤ ዕድል ያለው አይመስለኝም" ብለዋል።

  14. ሊባኖስ፣ ከዋሺንግተኑ ድርድር በፊት አሜሪካ “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም ትፈልጋለች

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግሥታቸው አሜሪካ ከዋሺንግተኑ ንግግር በፊት “እስራኤል ላይ ያላትን ተጽዕኖ” እንድትጠቀም እንደሚፈልግ ለዋሺንግተን ፖስት ተናገሩ።

    ናዋፍ ሳላም ለጋዜጣው “አሜሪካ ወደጠራችው ወደዚህ ድርድር እየገባን ያለነው በእስራኤል ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የምትችል መሆኑን በማመን ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሚናቸው ወሳኝ ነበር። ያላቸውን ተጽዕኖ እስራኤል ላይ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ ብለን እናምናለን” ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ የሚያካሄደውን ዘመቻ እንደቀጠለ ሲሆን ሳላም አገራቸው እስራኤል ግዛታቸውን ሙሉ በሙሉ ለቅቃ እንድትወጣ እንደሚፈልጉ ተናግረው “የደህንነት ቀጣና ከሚባለው ጋር መኖር አንችልም” ብለዋል።

    እስራኤል ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ እንድምትፈልግ ተጠይቀው “በአንድ ሌሊት የሚከናወን ነገር አይደለም። ነገር ግን ዋናው ነገር ምንድን ነው ቁርጠኛ መሆናችንን አሳይተናል” ብለዋል።

  15. ትራምፕ የባሕር ኃይሉ ፈንጂ የሚያሰቀምጡ ጀልባዎች ላይ “እንዲተኩስ እና እንዲገድል” አዘዙ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂ የሚያስቀምጥ ማንኛውንም ጀልባ “ተኩሳችሁ ግደሉ” ሲሉ ለባሕር ኃይላቸው ትዕዛዝ ሰጡ።

    “የአሜሪካ ባሕር ኃይል ማንኛውም ጀልባ ላይ እንዲተኩስ እና እንዲገድል አዝዣለሁ፤ ትናንሽ ጀልባዎች ምንም እንኳን ... በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ፈንጂዎችን እያስቀመጡ ይሆናል" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ልጥፋቸው ላይ አስታውቀዋል።

    “ምንም ማመንታት አያስፈልግም” ያሉት ትራምፕ የአሜሪካ ፈንጂ “አስወጋጆች” ወሽመጡን “አሁን” እያጠሩ ነው ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ የባሕር ኃይላቸውን ፈንጂ የሚያጠምድ ማንኛውም የኢራን ጀልባ ላይ “ተኩሱና ግደሉ” ካሉ በኋላ፣ ኢራናውያን “መሪያቸው ማን እንደሆነ ለማወቅ ተቸግረዋል” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በአገሪቱ ውስጥ “ወግ አጥባቂ” እና “ለዘብተኛ” በሆኑ ባለሥልጣናት መካከል ፍትጊያ መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

    አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ “እየተቆጣጠረች ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ካለ አሜሪካ ፈቃድ አንድም መርከብ እንደማይገባ እና እንደማይወጣ አስታውቀዋል።

  16. ሕይወት “ጦርነትም ሰላምም በሌለባት” ኢራን

    አሜሪካ ከቴህራን ጋር የጀመረችውን የተኩስ አቁም ካራዘመች በኋላ በኢራን መደበኛ ሕይወት ቀጥሏል። የኢራን ሪፐብሊክ መንግሥት እስካሁን ድረስ በሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስለመሳተፉ በይፋ ያለው ነገር የለም።

    የተባበሩት መንግሥታት የልማት ኃላፊ አሌክሳንደር ዴ ክሮ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኢራን ጦርነት በነዳጅ እና በማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል ወደ ድህነት ይገፋሉ ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    አብዛኛው የዓለም ማዳበሪያ የሚመረተው በመካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን አንድ ሦስተኛው የዓለም አቅርቦቶች በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ በኩል ያልፋሉ። ኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ወሽመጡን ለመቆጣጠር እየተፋለሙ ነው።

    ኢራናውያን የምግብ እና የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ማሻቀቡን ይናገራሉ። ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ኢንተርኔት እንደተቋረጠ ነው።

  17. የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ኢራን በጦርነት ውስጥ 'የመቆየት አቅም' አላት አሉ

    የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ ኢራን የምጣኔ ኃብት ጫና ከአሜሪካ እና ዶናልድ ትራምፕ የበለጠ የመቋቋም አቅም አላት አሉ።

    ዲፕሎማቱ አሜሪካ ከኢራን ጋር የምታደርገው ጦርነት ውጤት የሚወሰነው “ማን ረዥም ጊዜ [ጦርነት ውስጥ] ይቆያል” በሚለው ነው ብለዋል።

    “በእኔ እምነት ኢራን ረዥም ጊዜ [ጦርነት ውስጥ] መቆየት ትችላለች” ሲሉ ለቱዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

    ዲፕሎማቱ አሜሪካ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱ እንዲባባስ በሚያደርጉበት “ቅርቃር” ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ሳተርፊልድ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃዎችን የምታጠናክር ከሆነ ኢራን በፍጥነት በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ አገራት ላይ የበለጠ ጉዳት ታደርሳለች ብለዋል።

  18. የአሜሪካ ጦር በሕንድ ውቅያኖስ የምትቀዝፍ ማዕቀብ የተጣለባት የኢራን መርከብን መያዙን ገለጸ

    የአሜሪካ ጦር ከኢራን ነዳጅ የጫነች ማዕቀብ የተጣለባት መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

    የመከላከያ ቢሮ በኤክስ ገጹ ላይ “የአሜሪካ ጦር ማዕቀብ በተጣለባት አገር አልባ መርከብ፣ ኤም/ቲ ማጅስቲክ ኤክስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ በኩል ከኢራን ነዳጅ በማጓጓዝ ላይ ሳለች አስቁሞ ፍተሻ አካሄዷል" ብሏል።

    ቢሮው ለኢራን “የቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ” ተብለው የሚጠረጠሩ መርከቦችን አስቁሞ መፈተሹን አንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።

    የባሕር ትራንስፖርት ክልከላ ማለት ሕግ ተላልፏል ወይም ስጋት ነው ተብሎ የተጠረጠረ መርከብን መፈተሽ ወይም በቁጥጥር ስር ማዋልን ያካትታል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እገዳ ከጣለች ጀምሮ በርካታ መርከቦች እንዲመለሱ ወይንም እንዲቆሙ አድርጋለች።

    መርከቧ ከኢራን ርቃ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ እየቀዘፈች የነበረ እንደሆነ ተገልጿል።

  19. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መሰሰብብ መጀመሯን አስታወቀች

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚተላለፉ መርከቦች የተሰበሰበ የመጀመሪያው የገንዘብ ክፍያ ወደ አገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አካውንት መግባቱን የኢራን ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባኤ አስታወቁ።

    ታስኒም የተባለው የኢራን ዜና ወኪል ምክትል አፈ ጉባኤው ሃሚድሬዛ ሐጂ ባቤ ገንዘቡ ገቢ መደረጉን እንጂ ከማን እና እንዴት እንደተሰበሰበ ዝርዝር ማብረሪያ እንዳልሰጡ ዘግቧል።

    ክፍያው መሰብሰቡን በተመለከተ ከባለሥልጣኑ ባሻገር ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም።

    ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ከመደረጉ በፊት ኢራን በወሳኙ ሆርሙዝ በኩል “ወዳጅ” አገራት ብቻ እንዲተላለፉ የፈቀደች ሲሆን፣ በወሳኙ የባሕር ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችም እንዲከፍሉ እንደምታደርግ ስትገልጽ ነበር።

    ይህ የኢራን ውሳኔ በአገሪቱ ፓርላማ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ግን ግልጽ ሳይሆን ቆይቷል።

    ባለፈው መጋቢት ኢራን አስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እያስከፈለች ነው በሚል ክስ የቀረበባት ሲሆን በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲዋ ግን ዜናውን አስተባብሏል።

    ሌላ የኢራን ፓርላማ አባል “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚተለላፉ መርከቦች ገንዘብ መሰብሰቧን ከአስተማማኝ ምንጮች ሰምቻለሁ” ሲሉ ለታስኒም ዜና ወኪል አረጋግጠዋል።

    ጨምረውም “ከእያንዳዱ መርከብ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን መርከቦቹ የያዙት ጭነት ዓይነት እና መጠንን መሠረት ደያረገ ሲሆን፣ ክፍያውም በኢራን የሚወሰን ነው” በማለት አገራቸው ያወጣችው መመሪያ ተግባራዊ እየሆነ መሆነን አመልክተዋል።

    ይህ ኢራን በወሽመጡ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ክፍያ እንደምትሰበስብ ካስታወቀች በኋላ አሜሪካ ተቃወሞ ከማሰማቷ ባሻገር ፕሬዝዳንት ትራምፕ መርከቦች ለኢራን ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቀው ነበረ።

  20. ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል በባህረ ሰላጤው እና በወሽመጡ ላይ 'የጸጥታ መደፍረስ ምንጭ' ናቸው አለች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካ እና የእስራኤል "ጥቃት" በባህረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ "የጸጥታ ችግር ምንጭ" ነው አሉ።

    የኢራን መንግሥት በኤክስ ገፁ ላይ በተከታታይ ባጋራቸው ልጥፎች አባስ አራግቺ በቴህራን ከደቡብ ኮሪያ ልዩ መልዕክተኛ ጋር እንደተገናኙ ገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራት "እነዚህን ጥቃቶች በማውገዝ ግልፅ እና ጠንካራ አቋም እንዲወስዱ" ማሳሰባቸውን ጠቅሷል።

    ኢራን ደኅንነቷን እና ጥቅሟን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ሕግ እርምጃዎችን ወስዳለች ማለታቸውም በልጥፉ ተካትቷል።

    አራግቺ አክለውም ለሚደርሰው ሁሉ “ኃላፊነቱ የሚወስደው ጥቃት ፈጻሚው ነው” ብለዋል።

    ኢራን በወሽመጡ ሁለት መርከቦችን "መያዟን" እና ሦስተኛ የጭነት መርከብ ላይም ጥቃት መሰንዘሯ ተገልጿል።