መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መንቀሳቀስ መጀመራቸው ተሰማ
የባሕር ላይ ትራንስፖርትን የሚከታተለው ማሪንትራፊክ የተሰኘ ድርጅት በኢራን ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “የመርከቦች እንቅስቃሴ ምልክት” መታየቱን አስታወቀ።
በወሽመጡ አንድ በግሪክ ባለቤትነት የተያዘች እና ሌላ ደግሞ በላይቤሪያ የተመዘገበች መርከብ ማለፋቸውን ጠቅሷል።
ቢቢሲ የመረጃውን ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን አላጣራም።
ባለፉት 40 ቀናት በወሽመጡ ላይ የሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴ የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ምንም እንኳ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ ወሽመጡ ክፍት ሆኗል።
የተወሰኑ አገራት ቀደም ብሎ ከኢራን ጋር መርከቦቻቸው በወሽመጡ በኩል ያለምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከእነዚህ አገራት መካከል ፊሊፒንስ፣ ፓኪስታን እና ሕንድ ይገኙበታል።
ቀሪው የዓለም አገራት መርከቦች ግን በወሽመጡ በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ ተደጋጋሚ ጥቃትን ከኢራን በኩል አስተናግደዋል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ በቆየባቸው ሳምንታት ውስጥ የነዳጅ ዘይት፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ነበር። ይህም የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልገው ግብዓት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከኢራን ጦር ጋር በመተባበር እና “የቴክኒክ ቀርነቶችን ከግንዛቤ በማስገባት” ያለምንም ችግር ማለፍ ይቻላል ብለዋል።