ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ አዘዙ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴን እንዲያግድ ማዘዛቸውን አስታወቁ። በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለረጅም ሰዓታት ፓኪስታን ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ ላይ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ እና ኢራን የሚያስማማቸውን መንገድ ያገኙ ይሆን?

    በፓኪስታን እስላማባድ በሚካሄደው የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ምን ውጤት ሊመጣ ይችላል የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

    ሁለቱም ወገኖች በይፋ የሚያወሩት ነገር እጅግ የተራራቀ እና የሚቀራረብ የማይመስል ነው።

    የዚህም ከፊል ምክንያቱ መሪዎች እና ተደራዳሪዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚያወሩት በቀጥታ አድማጫቸው ለሆነው የአገራቸው ሕዝብ ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን እያንዳንዳቸው የጦርነቱን አውድ ለመቅረፅ እየሞከሩ ነው። ማን ማንን ለምኖ ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንደቀረበ ምስል ለመሳል እየተሯሯጡ ናቸው።

    አሁንም ቢሆን ሁኔታዎችን ለማሻሻል ግን ተስፋ አለ። ቢያንስ ቢያንስ ጥርጣሬ ያሳደረውን የተኩስ አቁም ስምምነት መጠበቅ ይቻላል።

    ማስታወስ የሚያስገልገው ጉዳይ፤ አሜሪካ እና ኢራን ባለፈው የካቲት እየተደራደሩ ሳለ ዋሽንግተን ጠረጴዛውን በመርገጥ ከእስራኤል ጋር ሆና ጦርነቱን ከፍታለች።

  2. የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን ሊያደርጉ ያቀዱትን የሰላም ንግግር በበጎ እንደሚቀበሉ ገልጸው፤ ሁለቱም ወገኖች “በቅን ልቦና" ወደ ድርድር እንዲገቡ አሳሰቡ።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ያደረጉት የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ደዣሬክ፤ ጉቴሬዝ “ሁሉም ወገኖች ይህንን የዲፕሎማሲ እድል በመያዝ ወደ ዘላቂ እና አጠቃላይ ስምምነት ለመድረስ በቅን ልቦና እንዲሳተፉ” መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

    ዋና ጸሐፊው፤ ንግግሩ ውጥረቱን “የማርገብ እና ወደ ግጭት እንዳይመለስ የመከላከል” እድል እንደሚሰጥም አስታውሰዋል።

    “ዋና ጸሐፊው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ተጨባጭ አማራጭ እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ደዣሬክ ተናግረዋል።

    የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የግል ልዑክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለማገዝ ቀጣናው ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።

  3. የኢራን ተደራዳሪዎች ፓኪስታን ደርሰዋል፤ የአሜሪካ ልዑክም ወደ አገሪቱ እያመራ ነው

    በኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ የሚመራው የቴህራን ተደራደሪ ቡድን ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ንግግር ፓኪስታን መድረሱን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው የዋሽንግተን ልዑክም ወደ ዋና ከተማዋ ኢስላማባድ ጉዞ ጀምሯል።

    ከ40 ቀናት ውጊያ በኋላ ተኩስ አቁም ላይ ደረሱት አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ፓኪስታን ውስጥ ለድርድር ይቀመጣሉ። የኢራን ልዑክ ለድርድሩ ከተያዘው ጊዜ አስቀድሞ ፓኪስታን ደርሷል።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚመለክተው ተደራዳሪ ቡድን ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ፣ የመከላከያ ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ አክባር አህማዲና፣ የማዕከላዊ ባምክ ገዢው አብዶልናስር ሄማቲ እንዲሁም በርካታ የፓርላማ አባላት ተካትተዋል።

    ልዑኩ የሚመራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢራን መንግሥት ውስጥ ጎልተው እየወጡ ባሉት አፈ ጉባኤው ጋሊባፍ እንደሆነ ተገልጿል። አፈ ጉባኤው ቡድኑን እየመሩ ቢሆንም ባለፉት ቀናት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሯቸው ጽሑፎች አሜሪካ ወደ ንግግር የማምራቷ ጉዳይ ላይ ኢራን ያላትን ጥርጣሬ ሲገልጹ ነበር።

    ሌላኛው ቡድኑ አባል አባል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ናቸው። አራግቺ በአውሮፓውያኑ 2015 ተደርሶ የነበረው የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

    በአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው ልዑክም በተመሳሳይ ወደ ፓኪስታን ጉዞውን ጀምሯል። በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አማካሪያቸው የነበረው የልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ የተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ናቸው።

    ኩሽነር እና ዊትኮፍ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ሲካሄዱ በነበሩ ድርድሮች ላይም አሜሪካን ወክለው ሲነጋገሩ ነበር። የጋዛ ጦርነት እንዲቆም ባደረገው የተኩስ አቁም እንዲሁም በሩሲያ እና ዩክሬን ድርድሮች ላይም ተሳትፈዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ኢራናውያን በጥሩ ልቦና ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆኑ ያለጥርጥር እጃችንን ከፍተን እንዘረጋለን” ብለዋል።

    አክለውም ግን “ሊጫወቱብን የሚሞክሩ ከሆነ ግን ተደራደሪ ቡድኑ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ ያገኙታል” ሲሉ አሳስበዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአሜሪካው ተደራደሪ ቡድን “ግልጽ መመሪያዎችን” መስጠታቸውንም ጠቅሰዋል።

  4. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርድሩ ካልተሳካ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናገሩ

    ከኢራን ጋር ፓኪስታን ውስጥ ቅዳሜ የሚጀመረው ድርድር የማይሳካ ከሆነ ለቀጣይ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የሰላም ንግግሩ የማይሳካ ከሆነ በሚል አሜሪካ የጦር መርከቦቿን “ምርጥ የተባሉ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቀች ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ኒው ዮርክ ፖስት ከተባለው ጋዜጣ በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት የድርድሩን ውጤት “በ24 ሰዓታት ውስጥ የምናውቅ ይሆናል” ብለዋል።

    “መርከቦቻችንን በታሪክ ውስጥ ከተሠሩት ሁሉ የላቁ የጦር መሳሪያዎችን እያስታጠቅን ነው፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ከተጠቀምበንት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የበለጠ ነው።

    "እናም ከስምምነት ላይ ካልደረስን እነዚህን የጦር መሳሪያዎች በጣም ውጤታማ በመሆነ መንገድ እንጠቀማቸዋለን” ሲሉ ፕሬዝዳቱ አክለዋል።

    ኢራናውያንን በተመለከተም “የሚናገሩት እውነታቸውን ይሁን አይሁን ማወቅ የሚቻሉ ሕዝቦች አይደሉም" በማለት ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።

    ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም አሜሪካ እና ኢራን ከደረሱ በኋላ ፓኪስታን ውስጥ የመጀመሪያውን ድርድር ቅዳሜ ዕለት ይጀምራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራናውያን ”ዓለም አቀፍ የባሕር መተላለፊያዎችን በኃይል በመዝጋት ለማስገደድ ካሆነ ሌላ አማራጭ የላቸውም" ሲሉ ጽፈዋል።

    አሁንም "በሕይወት ለመቆየታቸው ብቸኛው ምክንያት ለመደራደር ነው” በማለት ከስምነምት ላይ ከመድረስ ውጪ ምንም ማድረግ አይችሉም ብለዋል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉበኤ ግን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሂደው ጥቃት ሳይቆም እና የታገዱ የኢራን ሀብቶች ሳይለቀቁ ድርድር አይኖርም የሚል ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።

  5. እስራኤል በሊባኖስ ተኩስ ሳታቆም ከአሜሪካ ጋር ደርድር እንደማትጀምር ኢራን አስታወቀች

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ነገ ቅዳሜ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማበድ ውስጥ ንግግር ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ውስጥ ተኩስ አቁም ሳይደረግ ድርድር እንደማይጀመር ኢራን ገለጸች።

    በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው አገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባጌር ጋሊባፍ እንዳሉት ከአሜሪካ ጋር የሚካሄደው ድርድር የሚጀመረው ሁለት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ ነው።

    አፈ ጉባኤው ወሳኝ ያሏቸው የድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ጥቃት የሚያስቆም ተኩስ አቁም እና እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የኢራን ሀብት መለቀቅ ናቸው።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳሉት እነዚህ ሁለት እርምጃዎች አሜሪካ እና ኢራን ከሁሉ በፊት ተግባራዊ እንዲሆኑ የተስማሙባቸው መሆቸወውን አመልክተዋል።

    ሁለቱ ነጥቦች “ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሊፈጸሙ የሚገቡ ናቸው” በማለት ቅድመ ሁኔዎች መሆቸወውንም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እንደከፈቱ እስራኤል በሌላ በኩል የኢራን አጋር በሆነው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያካሄደች ሲሆን፣ ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላም ዘመቻዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

    በርካታ የኢራን ባለሥልጣናት በሊባኖስም ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ እንዲሆን እየጠየቁ ሲሆን፣ አሁን አፈ ጉባኤው የሰነዘሩት አስተያየት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገውን ድርድር እንዳያጨናግፈው ተሰግቷል።

  6. በኢራን ጥቃት ጉዳት የደረሰበት የሳዑዲ ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ ተዘጋ

    በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ በጦርነቱ ምክንያት በደረሰበት ጉዳት መዘጋቱን የፈረንሳዩ ቶታል ኩባንያ አስታወቀ።

    የሳዑዲ አረቢያ ኤነርጂ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው የሳዑዲ መንግሥት ንብረት በሆነው አራምኮ እና በቶታል ሽርክና የሚሠራውን ማጣሪያ ጨምሮ ባለፉት ቀናት በነዳጅ ዘይት እና በጋዝ ማምረቻ ተቋማት ላይ “ተደጋጋሚ ጥቃቶች” ተፈጽመዋል ብሏል።

    ነገር ግን በማጣሪያው ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደደረሰ ወይም ሥራ መቆሙ በምርቱ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

    ቶታል እንዳስታወቀው ግን “ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ሌሊት ባጋጠሙት ጥቃቶች በማጣሪያው ሁለት ክፍሎች ላይ ጉዳት ሰርሷል።”

    ጥቃቱን ተከትሎ በደረሰው ጉዳት ላይ ምርመራ እየተደረገ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ሁለቱ ክፍሎች እንዲዘጉ ቢደረጉም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።

    የሳዑዲ የኤነርጂ ሚኒስቴር አንድ ባለሥልጣን ለአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪል እደንተናገሩተ ጥቃቶቹ “በቁልፍ የምርት ተቋማት ሥራዎች ላይ በርካታ መቋረጥን አስከትለዋል” ብለዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለሳምንታት ባደረገችው ጦርነት ውስጥ ሳዑዲን ጨምሮ በበርካታ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሚገኙ የነዳጅ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

  7. ኢራን በቅና ልቦና የምትደራደር ከሆነ አሜሪካ ለስምምነት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

    ከኢራን ጋር ፓኪስታን ውስጥ በሚካሄደው ድርደር ላይ ለመሳተፍ ጉዞ ጀመሩት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢራናውያን በቀና ልቦና ለድርድር እንዲቀመጡ አሳሰቡ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ለጎዞ ወደ አውሮፕላን ከመግባታቸው በፊት በሰጡት ቃል ኢራናውያን ተደራዳሪዎች የማይሆን ሙከራ እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

    "ድርድሩን ለማካሄድ እየጠበቅን ነው” በማለት ኢራናውያን በቀና ልቦና የሚመጡ ከሆነ አሜሪካ “እጆቿን ዘርግ ታትቀበላቸዋለች” ብለዋል።

    ነገር ግን ኢራናውያኑ ተደራዳሪዎች “ሊያሞኙን የሚሞክሩ ከሆነ” አሜሪካ ይህንን የመቀበል ፍላጎት የላትም በማለት ከስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ንግግር ፕሬዝዳንት ትራምፕ የድርድር መመሪያዎችን እንደሰጧቸው አሳውቀዋል።

    ድርድሩ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ውስጥ ነገ ቅዳሜ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሊቬት አስታውቀዋል።

    አሜካንን በመወከል በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከፕሬዝንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር ጋር በመሆን ነው።

    የኢራን ተደራዳሪዎችም ፓኪስታን ይገባሉ ተብሎ እተጠበቀ መሆኑን በፓኪስታን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

  8. የኢራን ፓርላማ የአሜሪካ እና የእስራኤል መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ሊያግድ ነው

    በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚመረተው የነዳጅ ምርት የሚተላለፍበት ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር የሚያስችል ወሳኝ ዕቅድ የኢራን ፓርላማ አዘጋጅቶ በሚቀጥለው ሳምንት ድምጽ እንደሚሰጥበት ተነገረ።

    በዚህ ዕቅድ ውስጥ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በመተላለፊያው በኩል እንዳይጠቀሙ በዘላቂነት ዕገዳ የሚጥል ሃሳብ እንደተካተተበት ፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ያለውን ደኅንነት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚል በተዘጋጀው በአዲሱ ዕቅድ መሠረት በመርከቦች እንቅስቃሴ እና የሚገኝ ገቢን በተመለከተ ጉልህ ለውጥ እንደሚኖር የፓርላማው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮሚሽን ኃላፊ ተናግረዋል።

    ኃላፊው ለፋርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተዳደርበት አዲሱ አሠራርን የተመለከተው ዕቅድ በኢራን ፓርላማ “ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ተግባራዊ” ይሆናል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም የኢራን መንግሥት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚኖረውን ቁጥጥር እና የበላይነት ለማረጋገጥ በተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ ውስጥ አምስት ዋና ዋና ነጥቦች መካተታቸውን ኃላፊው ዘርዝረዋል።

    የጠላት መርከቦች እንዳይተላለፉ መከልከል፡ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው ነዳጅ ጫን መርከቦች በዘላቂነት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ይታገዳሉ።

    በወሽመጡ ከሚተላለፉ መርከቦች ክፍያ መሰብሰብ፡ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ለደኅንነታቸው እና ለሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ለሚያገኙት አገልግሎት ክፍያ ይጠበቅባቸዋል።

    የኢራን ገንዘብን ማጠናከር፡ የኢራን ገንዘብ የሆነውን ሪያል ለማጠናከር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚያልፉ መርከቦች የሚሰበሰቡት ሁሉም ክፍያዎች በኢራን ገንዘብ ብቻ ይሆናል።

    ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚለው ስም ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፡ ሁሉም በወሽመጡ የሚተላለፉ መርከቦች በሚኖራቸው የደብዳቤ ልውውጥ፣ በሚያዘጋጇቸው ሰነዶች እና የሬዲዮ መልዕክቶቻቸው ይፋዊውን እና ታሪካዊውን ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚለውን ስያሜ እንዲጠቀሙ ማድረግ።

    የሚሰበሰበው ገንዘብ አጠቃቀም፡ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚገኘው ገቢ ውስጥ 30 በመቶው የኢራን ወታደራዊ አቅምን ለማጠናከር ሲውል፣ 70 በመቶው ደግሞ የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት ለማሻሻል ይውላል።

    ለስድስት ሳምንታት በተካሄደው ጦርነት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ ፍጆታ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ችላለች።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር የደረሰችውን የተኩስ አቁም ተከትሎ ፓኪስታን ውስጥ በሚደረገው ድርድር የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።

  9. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆርሙዝ ጋር በተያያዘ ስለ ወታደራዊ አማራጮች መወያየታቸውን ገለጹ

    በመካለኛው ምሥራቅ ጉዞ እያደረጉ ያሉት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ለማድረግ ስለሚያስፈልጉት ወታደራዊ አቅሞች እና ሎጂስቲክስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ።

    “በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ ዕቅድ ላይ እየሠራን ነው፤ ነገር ግን ወታደራዊ አማራጮች እና… በወሽመጡ በኩል መርከቦች ለማንቀሳቀስ [ስለሚያስፈልገው] ሎጂስቲክስ እየተመለከትን ነው” ማለታቸውን የዜና ወኪሎ ሮይተርስ ዘግቧል። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ “የአገራት ጥምረት” እንዲኖር እየሠሩ መሆኑንም አክለዋል።

    ትናንት ምሽት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያደረጉት “ውይይት ትኩረትም” ይህ ጉዳይ እንደነበር አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ መረጃዎችን አልሰጡም።

    ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ንግግር አሜሪካ ከኔቶ ልትወጣ ትችላለች ስለሚለው ስጋት አንስተው እንደሆነ የተጠየቁት ስታርመር፤ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጡም ጥምረቱ ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ ጥቅም የሚበጅ መሆኑን ገልጸዋል።

    "ኔቶ ላለፉት አስርት ዓመታት እኛ ከምናደርገው በላይ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደረገ የመከላከያ ጥምረት ነው” ብለዋል።

  10. ሊባኖስ በድርድሩ የምትሳተፈው ተኩስ አቁም ከተደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገለጸች

    ሊባኖስ በሚቀጥለው ሳምንት ከእስራኤል ጋር ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር የምትሳተፈው ከንግግሩ በፊት ተኩስ አቁም ላይ ከተደረሰ ብቻ እንደሆነ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ አረጋገጠ።

    ባለፉት ቀናት የእስራኤልን ከፍተኛ ጥቃቶች ያስተናገደቸው ሊባኖስ በሚቀጥለው ሳምንት አሜሪካ ውስጥ ከቴል አቪቭ ጋር ንግግር እንደምታደርግ ተገልጾ ነበር።

    ሊባኖስ እና እስራኤል ቀጥተኛ ንግግር ማድረጋቸው ከዚህ በፊት ያልታየ ባይሆንም ያልተለመደ ነው። ብዙውን ጊዜ ሁለቱ አገራት የሚነጋገሩት እንደ አሜሪካ ባሉ በአሸማጋዮች አማካኝነት ነው።

    በትናትነው ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር ንግግር እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጸው፤ ተኩስ አቁም ግን እንደማይኖር አስታውቀዋል።

  11. ፓኪስታን እና ፈረንሳይ በሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት “ከፍተኛ የተኩስ አቁም ጥሰት” ነው አሉ

    የፓኪስታን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሊባኖስ ውስጥ እየተፈጸመ ባለው “ከፍተኛ የተኩስ አቁም ጥሰት” የተሰማቸውን ስጋት ገለጹ።

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን ኖይል ባሮት ከፓኪስታን አቻቸው መሐማድ ኢሻቅ ዳር ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር፤ አገራቸው የፓኪስታንን የሰላም ጥረት እንደምትደገፍ አስታውቀዋል። ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ “በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት” ሊያመጣ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ “ሁለቱም መሪዎች በሊባኖስ እየተፈጠረ ያለውን ከፍተኛ የተኩስ አቁም በተመለከተ ስጋታቸውን ገልጸዋል” ብሏል።

    “የተኩስ አቁሙ በሙሉ በሙሉ መተግበር እና ስምምነቱን ማክበር ስላለው አስፈላጊነትም አጽንኦት” እንደሰጡ ገልጿል።

    የሁለቱ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይህንን ያሉት አሜሪካ እና ኢራን በመጪዎቹ ቀናት ፓኪስታን ውስጥ የሚያደርጉት የሰላም ንግግር እየተጠበቀ ባለበት ጊዜ ነው። ድርድሩ የመካሄዱ ጉዳይ ግን ጥርጣሬ እየተነሳበት ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድርድሩ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች “እስካሁን እንዳልተጠናቀቁ” ተናግሯል። በትናትናው ዕለት የኢራን ልዑክ ወደ የፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እንደደረሰ የተሰራጨው መረጃ ማስተባበያ ተሰጥቶበታል።

    ድርድሩ በእቅዱ መሠረት የመካሄዱ ነገር ላይ እርግጠኛ የሆነች የምትመስለው ፓኪስታን በበኩሏ ዝግጅት ማድረጓን ቀጥላበታለች። በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ የሚገኙ መንገዶች እንዲሁም የመንግሥት ሕንጻዎች እና ኤምባሲዎች ተዘግተዋል።

  12. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙ “በመጣሱ” በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

    በሊባኖስ የሚገኘው የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድን ሄዝቦላህ፤ እስራኤል በአሜሪካ እና በኢራን ተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት “በመጣሷ” በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኝ ከተማ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።

    ሄዝቦላህ እንደገለጸው ሮኬቶችን የተኮሰው በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኘው ኪርያት ሽሞና እንዲሁም በሰሜናዊ እስራኤል ሚስጋቭ አም አካባቢ ነው።

    “እስራኤል እና አሜሪካ በአገራችን እና በሕዝባችን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እስከሚቆም ድረስ ይሄ ምላሽ ይቀጥላል” ብሏል።

    አሜሪካ እና ኢራን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስቆም የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደው ጥቃት ቀጥሏል። ኢራን እና አሸማጋይዋ ፓኪስታን የተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጸዋል። አሜሪካ እና እስራኤል በበኩላቸው ሊባኖስ የስምምነቱ አካል እንዳልሆነች እየተናገሩ ነው።

    እስራኤል የተኩስ አቁሙ በተደረሰ ማግሥት ረቡዕ ዕለት በከፈተችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቆስለዋል። እስራኤል አሁንም የደቡባዊ ሊባኖስን ሰፊ መሬት ተቆጣጥራ ይዛለች።

    የእስራኤሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ድርድር እንደሚደረግ ቢናገሩም፤ “ሊባኖስ ውስጥ ተኩስ አቁም አይኖርም” ሲሉ ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

  13. ትራምፕ በኢራን ጦርነት ያላቸው ሥልጣን እንዲገደብ የሚያደርገው ሕግ በሪፐብሊካኖች ውድቅ ተደረገ

    በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙ ሪፐብሊካኖች ዋሽንግተን ኢራን ላይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች እንዲቆሙ ለማድረግ በዴሞክራቶች የቀረበውን ሕግ ከመጽደቅ ማገዳቸውን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

    ሪፐብሊካኖች የፓርቲያቸው ተመራጭ የሆኑትን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ለመገደብ የሚደረጉ ጥረቶች እንዳይሳኩ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

    የተወሰኑ ዴሞክራቶች የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያበቃ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ ያለ ግምገማ በሙሉ ድምጽ እንዲጸድቅ ከመጠየቃቸው በፊት ሪፐብሊካኑ የኒው ጀርዚ ተወካይ ክሪስ ስሚዝ ስብሰባው እንዲጠናቀቅ አድርገዋል።

    ትናንት ሐሙስ የተካሄደው ይህ ስብሰባ በአመዛኙ ከትምህርታዊነት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ እና በሴኔት የሚገኙ ዋነኛ ዴሞክራቶች ኮንግረሱ በሚቀጥለው ሳምንት ከእረፍት ሲመለስ የትራምፕን ሥልጣን ሚገድበው ሕግ በድጋሚ ድምጽ እንዲሰጥበት ለማድረግ ዝተዋል።

    ዴሞክራቶች የጦርነት ሥልጣንን የተመለከተውን ሕግ ለማጽደቅ ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ሞክረው አልተሳካላቸውም። ዴሞክራቶች በዚህ ሕግ አማካኝነት ትራምፕ ከኮንግረስ ፈቃድ ሳያገኙ ጦርነት እንዳይከፍቱ የማደረግ ፍላጎት አላቸው።

    በኮንግረስ የሚገኙ ዴሞክራቶች ይህንን ጥረታቸው በድጋሚ አሁን የጀመሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት “ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” በማለት ኢራን ላይ ከዛቱ በኋላ ነው።

  14. የእስራኤል እና የሊባኖስ ደርድር በአሜሪካ ሊካሄድ ነው

    ባለፉት ቀናት የሄዝቦላህ “ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች” ስትል በገለጸቻቸው ዒላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ያባባሰችው እስራኤል፤ ከሊባኖስ ጋር የምታደርገው ድርድር በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ከተማ ውስጥ እንደሚካሄድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ።

    አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የተኩስ አቁም ሊባኖስንም የሚያካትት የመሆን፣ አለመሆኑ ጉዳይ ሲያወዛግብ ከቆየ በኋላ በትናንትናው ዕለት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ጋር ድርድር እንዲጀመር ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

    የሊባኖስ ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ተደርጎ ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል። ከዚህ ጥያቄ በኋላ ለሰሜናዊ እስራኤል ነዋሪዎች መልዕክት ያስተላለፉት ኔታንያሁ ግን “ሊባኖስ ውስጥ የተኩስ አቁም አይኖርም” ብለዋል።

    እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች ባለፉት ቀናት በከፍተኛ መጠን ጨምረው ከቆዩ በኋላ ከትናንት ምሽት አንስቶ ለጊዜው ጋብ ያለ ይመስላል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኤንቢሲ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ እስራኤል የሰላም ንግግሩን ለማገዝ ሲባል የምትፈጽመውን ጥቃት “እየቀነሰች” መሆኑን ገልጸዋል።

    “ከቢቢ [የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚስትር] ጋር ተነጋግረናል፤ እናም [ጥቃቱን] ይቀንሰዋል። ከዚህም የበለጠ መቀነስ እንዳለብን አስባለሁ” ሲሉ ከኔታንያሁ ጋር በስልክ ካደረጉት ንግግር በኋላ አቋማቸውን አስረድተዋል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው እስራኤል እና ሊባኖስ በሚቀጥለው ሳምንት “ዋሽንግተን ውስጥ እየተተገበረ ስላለው የተኩስ አቁም ድርድር” ይነጋገራሉ።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት ከሊባኖስ ጋር የሚደረገው ድርድር ሄዝቦላህን እና በኢራን የሚደገፉ አማጺ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል። በሁለቱ አገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት የመመስረት ጉዳይም የድርድሩ አካል ነው ተብሏል።

    ይሁን እንጂ የሊባኖስ መንግሥት እና እስራኤል የሚያደርጉት ድርድር ሄዝቦላህ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ አይደለም።

    የሊባኖስ መንግሥት ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከተጀመረበት መጋቢት አንስቶ የሄዝቦላህን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አግዷል። ይህ እገዳ ግን ቡድኑ እስራኤል ላይ ሮኬቶችን ከማስወንጨፍ አላገደውም።

    በተጨማሪም እስራኤል ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ ቁርጠኝነት ባላሳየችበት ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ድርድር ፍሬያማ የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗል።

    እግረኛ ወታደሮቿን ሊባኖስ ውስጥ ያሰማራችው እስራኤል፤ በአገሪቱ ደብባዊ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ግዛቶችን መውረሯን ቀጥላለች።

    ባለፉት ቀናትም ሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ መንደሮችን ሆነ ብላ አውድማለች። የእስራኤላውያን ደኅንነት እስካልተጠበቀ ድረስ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።

  15. ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የያዘችው “በተስማማንበት" መንገድ አይደለም አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን በወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፈውን ነዳጅ የያዘችበት መንገድ “እጅግ ደካማ ሥራ” ነው አሉ። ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር “የደረስነው ስምምነት ይህ አይደለም” ሲሉም ወቅሰዋል።

    ትራምፕ ከዓለም ነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ 20 በመቶ የሚሆነው ስለሚተላለፍበት ወሽመጥ አስተያየት የሰጡት በሶሻል ትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ነው።

    ትራምፕ፤ “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ክፍያ እስያከፈለች እንደሆነ ሪፖርቶች እየወጡ ነው” ብለዋል። “እያደረጉ ባይሆን ይሻላቸዋል፤ ከሆነም ቢያቆሙ ይሻላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በሌላ ጽሑፋቸው ደግሞ “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ እንዲያልፍ መፍቀድን በተመለከተ እያከናወነች ያለችው እጅግ ደካማ ሥራ ነው፤ አንዳንዶች አዋራጅ ብለው ይገልጹታል” ሲሉ ተችተዋል። “ያለን ስምምነት ይህ አይደለም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

    ለ40 ቀናት ሲዋጉ የቆዩት አሜሪካ እና ኢራን የደረሱበት ተኩስ አቁም ከሚያካትታቸው ነጥቦች አንዱ የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ነው።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ ያሰባሰባቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከስምምነቱ በኋላም በወሳኙ የባሕር ኮሪደር በኩል ያለፉ መርከቦች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነው። ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት በየቀኑ በአማካይ 138 መርከቦች በወሽመጡ በኩል ያልፉ ነበር።

  16. ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከሊባኖስ ጋር ድርድር እንዲጀመር አዘዙ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሠራዊታቸው ከባድ ጥቃት እየፈጸመ ካለባት ሊባኖስ ጋር ሚኒስትሮቻቸው ቀጥተኛ ንግግር እንዲጀምሩ ማዘዛቸውን አስታወቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ በእብራይስጥ ቋንቋ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከሊባኖስ በኩል ቀጥተኛ ድርድር እንዲደረግ ቀረበ ባሉት “ተደጋጋሚ ጥሪ” መሠረት ካቢኔያቸው ንግግሩን “በአስቸኳይ” እንዲጀምር መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

    ኔታኒያሁ ጨምረውም የሚደረገው ንግግር “ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ” ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ይህንን ከማሳወቃቸው ቀደም ብሎ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አዎንስ ብቸኛው መፍትሄ ሁለቱ አገራት ተኩስ አቁም አድርገው “ቀጥተኛ ድርድር” ማካሄድ ነው ሲሉ ተናግረው ነበረ።

    ፕሬዝዳንቱ የሊባኖስ የፀጥታ ኃይሎች “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን” ሕግ የማስከበር ሥራቸውን ሙሉ ለሙሉ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

    እስራኤል የኢራን አጋር የሆነውን የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህን ዒላማ በማድረግ ከአንድ ወር በላይ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ እግረኛ ወታደሮቿንም በደቡባዊ ሊባኖስ አሰማርታለች።

    እስራኤል ባለፉት ሁለት ቀናት ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ እና በሌሎች በርካታ የሊባኖስ አካባቢዎች በፈጸመቻቸው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  17. ዴሞክራቶች የትራምፕን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ እየጣሩ ነው

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ደስተኛ ያልሆኑት ዴሞክራቶች፤ የፕሬዝዳንቱን ጦርነት የማወጅ ሥልጣን የሚገድበው ሕግ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለምክር ቤቱ ሊያቀርቡ ነው።

    በአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት አገራቸው ከኢራን ጋር ባካሄደችው ጦርነት ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ ሰኞ ዕለት ትራምፕ የኢራንን ሥልጣኔ “በአንድ ሌሊት እንደሚያጠፉ” ከዛቱ በኋላ ስጋታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መደረሱ ተነግሯል።

    ከአሜሪካ ምክር ቤት አባላት መካከል ጥቂት የማይባሉትም በፕሬዝዳንቱ ላይ የተሰማቸውን ቁጣ ወደ ሕግ ለመቀየር በአገሪቱ ሕግ መሠረት ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማንሳት የሚያስችለው 25ኛው የሕግ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

    ነገር ግን ሕግ አውጪዎቹ ፕሬዝዳቱን ለመቆጣጠር ሊጠቀሙበት የሚችሉት ቁልፍ አሠራር ትራምፕ ጦርነት ለማካሄድ ያላቸው ሥልጣን የሚገድበውን ደንብ ተግባራዊ ማስደረግ ነው።

    ይህ እርምጃ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ ኮንግረስ እስካልፈቀደ ድረስ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ አይችልም።

    በየካቲት ማብቂያ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈታቸውን ካሳወቁ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ በሁለቱም የአገሪቱ ምክር ቤት ድምጽ ቢሰጥም ተቀባይነት የሚያስገኘውን ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል።

    ዛሬም በድጋሚ በምክር ቤቱ የሚገኙ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በድጋሚ የትራምፕ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣንን የሚገድበው ሕግ ተቀባይነት እዲያገኝ ሙከራ ያደርጋሉ።

    ውሳኔው አሁንም ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ቢሆንም፣ አሜሪካውያን ለጦርነቱ ያላቸውን አቋም ለማሳየት ያስችላቸዋል ተብሏል።

  18. ስለ ኢራን ልናውቃቸው የሚገቡ አንዳንድ እውነታዎች

    ከእስላማዊው አብዮቷ በኋላ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆና የቆየችው ኢራን ለስድስት ሳምንታት ከእነዚሁ አገራት ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

    በዓለም የሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱት መካከል ፋርስ ተብሎ የሚታወቀው ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ሕዝብ ያላት እና በተፈጥሮ ሀብትም የታደለች ናት።

    ከምዕራባውያን ጋር በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ጥርስ ውስጥ ገብታ በተለያዩ ማዕቀቦች ጫና ውስጥ ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥቃት ሲፈጸምባት ቆይቶ የለየለት ጦርነት ተከፍቶባታል።

    ለ40 ቀናት ያህል ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ስለተፋለመችው ኢራን ልናውቃቸው የሚገቡ ዋና ዋና እውነታዎች እዚህ ይመልከቱ።

  19. በጦርነቱ ከ3,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያካሄዱት ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኢራን የሕክምና ምርመራ ድርጅት ዋና ኃላፊ የሆኑትን አባስ ማስጄዲ አራኒን ጠቅሰው እንደዘገቡት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በተጀመረው ጦርነት ከ3 ሺህ በላይ ኢራናውያን ሞተዋል።

    በአሜሪካ መቀመጫውን ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪዎች የዜና ተቋም የሆነው ሂራና እንደዘገበው አስከ መጋቢት 29 ድረስ 254 ሕጻናትን ጨምሮ 1,701 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

    የዜና ወኪሉ ጨምሮም 1,221 የኢራን ጦር ሠራዊት አባላት እና 714 ማንነታቸው ያልተለዩ ሰዎች ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተገድለዋል ብሏል።

    ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ሌሎች ድርጅቶች በኢራን ውስጥ ለመንቀሳቀስ ስለማይፈቀድላቸው በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።

    በተጨማሪም ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ መረጃዎችን ማግኘት እና ማጣራት አዳጋች ሆኗል።

  20. እስራኤል ነዋሪዎች ከተለያዩ የቤይሩት አካባቢዎች እንዲወጡ አዘዘች

    በሄዝቦላህ "ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች" ላይ ላይ ተጨማሪ ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ የያዘችው እስራኤል፤ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ የከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈች።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራኢ በእነዚ አከባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስራኤል "እናንተን የመጉዳት ዕቅድ የላትም... ስለሆነም ለደኅንነታችሁ ሲባል በአስቸኳይ ለቅቃችሁ መውጣት አለባችሁ" ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር የለቅቃችሁ ውጡ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው፤ ሃሬት ህሬክ፣ ጎቤይሪ፣ አል ሊላኪ፣ ሀዳት፣ ቦርጅ ኤል ባራጅነህ፣ ታህዊታት አል-ጋዲር፣ ሺያህ እና አል-ጃናህ የተባሉት አካባቢዎች ናቸው።

    እስራኤል ቤይሩት ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት በከፍተኛ መጠን የጨመረችው አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስን የማካተቱ ጉዳይ አከራካሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

    ኢራን እና ስምምነቱን ያሸማገለችው ፓኪስታን ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ቢገልጹም እስራኤል አቋሟ በተቃራኒው እንደሆነ አሳውቃለች።

    ኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ሊባኖስ ውስጥ የሚፈጸሙት ጥቃቶች የተኩስ አቁም ጥሰት እነደሆኑ ገልጸዋል።

    ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ተኩስ ካስወነጨፈ በኋላ በተከፈጠው ዘመቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።