ኢራን፣ አሜሪካ የፈጸመችው አዲስ ጥቃት የተኩስ አቁሙን የጣሰ ነው አለች
አሜሪካ ራስን መከላከል በሚል አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ኢራን ከፈጸመች በኋላ ቴህራን ዋሺንግተን የተኩስ አቁሙን ጥሳለች ስትል ከሰሰች።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር “ጥቂት ቀናት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ሆርሞዝጋን አውራጃ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቆ የተኩስ አቁሙ “ግልጽ ጥሰት ነው” ሲል ተናግሯል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አሜሪካ “ጠብ አጫሪ እና ተቀባይነት ለሌለው ድርጊቷ” ተጠያቂ ትሆናለች ብሏል።
አሜሪካ ጥቃት የፈጸመችበት ሆርሞዝጋን ክልል ከሆርሙዝ ወሽመጥ ጋር የሚዋሰን ነው።
ኢራን በመግለጫው “ያለምንም ጥርጥር የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ምላሽ ሳይሰጥ የሚተወው ምንም ክፋት የለም እንዲሁም የኢራን ዜጎችን ከመከላከልም ወደ ኋላ አይልም” ብላለች።
ሁለቱ አገራት እስከ ትናንት ሰኞ ድረስ በመግባቢያ ሰነዱ ዙሪያ የሚደረገው ንግግር ለውጥ ማሳየቱን ሲናገሩ ነበር።
አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ንግግር በስምምነት ከተቋጨ ለሦስት ወር የዘለቀውን ጦርነቱን ያስቆማል፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ያስከፍታል እንዲሁም የተኩስ አቁሙን በ60 ቀናት ይራዘማል ተብሎ ነበር።
የአሜሪካ ጦር በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን አስታወቋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ አስታውቋል። ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።