አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት መድረሳቸውን እና ትራምፕ እስኪያጸድቁት እየተጠበቀ መሆኑን አክሲዮስ ዘገበ
አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁሙን በ60 ቀናት ለማራዘም እና በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ለመደራደር መስማማታቸው ተዘገበ።
አክሲዮስ ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ስምምነቱን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስኪያጸድቁት ድረስ እየተጠበቀ ነው።
ሁለቱ አገራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተዘገበው ኢራን በኩዌት የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ከተዘገበ በኋላ ነው።
አክሲዮስ ሁለቱ አገራት መስማማታቸውን ከዘገበ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ ታይቷል።
አሜሪካ ሌሊት ላይ በኢራን የወደብ ከተማ ባንዳር አባስ ውስጥ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ለአየር እና ለባሕር ኃይሏ ስጋት እንደሆኑ የገለጸቻቸውን ወታደራዊ ማዕከላት መምታቷን አስታውቃለች።
የአሜሪካ ኃይሎች "በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ ስጋት ደቅነው የነበሩ" አራት የኢራን ድሮኖችንም መትተው እንደጣሉ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ገልጿል።
እንደ ሴንትኮም ገለጻ ባንደር አባስ ውስጥ የሚገኘው ወታደራዊ ስፍራ ጥቃት የተፈጸመበት አምስተኛውን ድሮን ለመተኮስ ሲዘጋጅ ነው። የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከከተማው በስተምሥራቅ አቅጣጫ የፍንዳታ ድምፆች መሰማታቸውን ዘግበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የራዳር መከታተያውን አጥፍቶ ሊያልፍ የነበረ የአሜሪካ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ማስቆሙን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ዘገባው እንዳመለከተው የአብዮታዊ ዘቡ ባሕር ኃይል በመርከቡ ላይ ተኩስ ከፍቶ ወደ መጣበት እንዲመለስ ማስገደዱንም ገልጿል።