‘ኢራን [ስምምነቱ] ቶሎ እንዲጠናቀቅ ትፈልጋለች”-ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ፈረንሳይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያካሄዱት ሁለተኛው ዙር ድርድር “ጊዜውን ጠብቆ ይሄዳል” ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።
“ኢራን በቶሎ እንዲጠናቀቅ ትፈልጋለች፤ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ ይፈልጋሉ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ስምምነቱ ይፋ ለምን እንደማይሆን ሲጠየቁ “መጀመሪያ በይፋዊ መፈራረሙ እንዲቀድም” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
“ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራትም፤ ያንን ነው የሚለው. . . ያ ነው 99.9 በመቶ የምፈልገው የነበረው”
የሆርሙዝ ወሽመጥ ከ60 ቀናት በኋላም “ያለምንም ክፍያ” ክፍት ይሆናል ሲሉም አብራርተዋል።
ትራምፕ ስምምነቱን “ቃል በቃል” ለማንበብ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚጠሩም ጨምረው አስረድተዋል።
“ምክንያቱም በጣም ወሳኝ ሰነድ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራትም ካሉ በኋላ “እውነቱን ለመናገር ሌላው አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ስምምነቱን “ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ በተቃራኒ የቆመ ግድግዳ” ሲሉ ገልጸውታል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከኢራን ጋር ካደረጉት ስምምነት ጋር በማነጻጸርም “መካከለኛው ምሥራቅን ሊያጠፋ ይችል ነበር” ብለዋል።
የተብላላውን ዩራኒየም ከኢራን ያወጡ እንደሆን ሲጠየቁም፣ መቼ ይወጣል የሚለው ላይ ምንም ጥድፊያ እንደሌለ ተናግረዋል።
ትራምፕ ስምምነቱ እንዲጸድቅ ወደ ኮንግረስ እንደሚላክ ጨምረው አስረድተዋል።



















