ቭላድሚር ፑቲን፡ “1 ቢሊዮን ዶላር የምታወጣው” ግሪንላንድን ማንም ቢወስዳት ሩሲያ አይጨንቃትም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የግሪንላንድ ባለቤትነት ጉዳይ የሩሲያ ጭንቀት እንዳልሆነ ተናገሩ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ፑቲን የግሪንላንድን ጉዳይ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዴንማርክ ሊፈቱት ይገባል ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክ ክፍል የሆነችው ራስ ገዟን ደሴት ለመቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት በአፅንዖት መግለፃቸው በዩኤስ እና በአውሮፓ መካከል ክፍተት ፈጥሯል።
የግሪንላንድን ጉዳይ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ሐሳባቸውን የገለፁት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው የትራምፕን ዕቅድ እንደማትቃወም ጠቁመዋል።
“በግሪንላንድ የሚፈፀም ማንኛውም ጉዳይ የኛ ጭንቀት አይደለም” ሲሉ ፑቲን በሩሲያ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
“ዴንማርክ ግሪንላንድን እንደ ቅኝ ግዛት ነበር የምትቆጥራት። ጭካኔ የተሞላበት ነበር ማለትም ይቻላል” ሲሉ አክለዋል።
ዴንማርክ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉ ሀገራት መካከል መሆኗ ሩሲያን አስቆጥቷል።
ትራምፕ ረቡዕ በዳቮስ ባደረጉት ንግግር በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ሰላም ለማምጣት እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአውሮፓው 1867 ሩሲያ አላስካን ለአሜሪካ በ7.2 ሚሊዮን ዶላር መሸጧን ያወሱት ፑቲን፤ ግሪንላንድ ብትሸጥ ዋጋዋ 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ቢሆን ነው ሲሉ ተደምጠዋል።






















