ትራምፕ በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባለቸው አገራት ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፈረሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አገራቱ ከቴህራን ጋር መገበያየት የሚቀጥሉ ከሆነ ቀረጡን ሊጥሉ እንደሚችሉ ተናገሩ። ኦማን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ንግግር ኢራን "ስምምነት ላይ ካልደረሰች ውጤቱ በጣም ከባድ ይሆናል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ማዕከላዊ አሜሪካዊቷ አገር ኮስታሪካ ሁለተኛዋን ሴት ፕሬዚደንት መረጠች

    የወግ አጥባቂውን ‘ሶቨሪን ፒፕል ፓርቲ’ ዕጩ የሆኑት ላውራ ፈርናንዴዝ በማዕከላዊ አሜሪካ የምትገኘው ኮስታሪካ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ።

    እስካሁን ባለው ሂደት 88 በመቶ ያህሉ ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን፣ ከተፎካካሪያቸው አልቫሮ ራሞስ የ48 በመቶ ልዩነት ስላላቸው ማሸነፋቸውን አረጋግጠዋል።

    በዚህም በአውሮፓውያኑ 2010 ከተመረጡት ላውራ ቺንቺላ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የአገሪቱ ሴት ፕሬዚደንት ሆነዋል።

    የ39 ዓመቷ ፈርናንዴዝ ለፕሬዚደንትነት ከመወዳደራቸው በፊት በፕላን ሚኒስትርነት እንዲሁም በሌሎች ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

    ተመራጯ ፕሬዚደንት ወንጀልን በመከላከል ረገድ ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ሮድሪጎ ቻቭስ ሲያከናውኑት የነበረውን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

    በኮስታሪካ ሕገ መንግሥት ፕሬዚዳንቶች ከሁለት ተከታታይ የሥልጣን ዘመን በላይ ማገልገል ስለማይችሉ አሁን አገሪቷን እየመሩ ያሉት ሮድሪጎ ቻቭስ በምርጫው አልተወዳደሩም።

    ፈርናንዴዝ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  2. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋን ሊከሱ ነው

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደቡብ አፍሪካዊውን ታዋቂ ኮሜዲያን እና የቴሌቪዥን ፕሪግራም አቅራቢ ትሬቨር ኖዋ በግራሚ ሽልማት ወቅት በተናገረው “ስሜን አጥፍቷል” በማለት እንደሚከስሱት ዛቱ።

    በሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ኖዋ የዓመቱን ምርጥ ሙዚቃ ባስተዋወቀበት ጊዜ “የዓመቱ ምርጥ ሽልማት የኤፒስታይን ደሴት ስለሌለ ትራምፕ ከቢል ክሊንተን ጋር የሚዝናኑበትን ግሪንላንድ ደሴትን አጥብቀው እንደሚፈልጉት ሁሉ ሁሉም አርቲስት የሚፈልገው ሽልማት” ብሎ ነበር።

    ትራምፕም ይህንን ንግግሩን ፍጹም ውሸት በማለት ስለቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ምንም ማለት እንደማይችሉ፤ ነገር ግን በወሲብ ጥቃት ወንጀል ስሙ በስፋት በሚነሳው የኤፕስቲን ደሴት እንዳልተገኙ እንዲያውም ከአቅራቢያው እንዳልደረሱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    እንዲህ ያለው ክስም በመደበኛ መገናኛ ብዙኃኖች እንኳን እንዳልቀረበባቸው በመጥቀስ ኖዋ የተናገረው ነገር “የቀልድ መስመርን ያለፈ ስም ማጥፋት ነው” ብለዋል።

    ስለዚህም ጠበቆቻቸውን በማዘዝ ትሬቨር ኖዋ “ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብኛል” በማለት በሕግ እንደሚጠይቁት ዝተዋል።

    ይህ የትራምፕ ቁጣ የኤፕስቲን ምሥጢራዊ ሰነዶች ከመውጣታቸው ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንቱ ቢያስተባብሉም ከዚህ በፊት ከግለሰቡ ጋር ጋር ግንኙነት አላቸው የሚለውን ክስ በማስታወስ በድጋሚ መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።

  3. የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስትር ‘ትራምፕ እርምጃ ካልወሰዱ ኢራን መልሳ ትጠናከራለች’ አሉ

    የሳዑዲ አረቢያው የመከላከያ ሚኒስትር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደዛቱት በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ የማይወስዱ ከሆነ ኢራን የበለጠ “ትጠናከራለች” ብለዋል መባሉ እያነጋገረ ነው።

    የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ የመከላከያ ሚኒስትሩ ልዑል ኻሊድ ቢን ሳልማን አርብ ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ በተደረገ የግል ውይይት ላይ አሜሪካ ኢራንን ካልመታች አገዛዙ ተጠናክሮ ይወጣል ማለታቸውን በስፍራው የነበሩ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን “የአንድን አገር አቋም በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ብቻ አንመዝንም” ዘገባውን አጣጥለው አገራቸው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ቋሚ ግንኙነት እያደረገች መሆኑን አመልክተዋል።

    እሁድ ዕለት የወጣው አሽራቅ አል አውሳጥ ጋዜጣ አንድ የሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ በኢራን ላይ ያላት አቋም አልተቀየረም ሲሉ አስተባብለዋል።

    ስማቸው ያለተጠቀሰው ባለሥልጣን እንደተናገሩት ሳዑዲ በኢራን እና በሳዑዲ መካከል የተከሰተው ችግር በዲፕሎማሲ እና በንግግር እንዲፈታ ትፈልጋለች ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አብዶልራሂም ሙሳቪ ደግሞ በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከባድ ምላሽ እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

    “ጠላታችን የምትፈጽመው አንድ ስህተት አሜሪካውያንን ለአደጋ ይዳርጋቸዋል እንዲሁም ከቀጣናው የሚነሳው እሳትም አሜሪካን እና አጋሮቿን ይበላቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  4. እስራኤል ወደ ጋዛ የሚያስገባውን ቁልፍ የራፋህ ድንበር እንደገና ከፈተች

    እስራኤል የጋዛ ሰርጥን እና ግብፅን የሚያገናኘውን ቁልፍ የራፋህ ድንበር ለሰዎች እንቅስቃሴ እንደገና ከፈተች።

    ይህንንም ተከትሎም በጦርነቱ የተሰደዱ እንዲሁም ለሕክምና የሚወጡ ፍልስጤማውያን ወደ ራፋህ ድንበር መግባት ጀምረዋል።

    በጋዛ በኩል ያለው የራፋህ ድንበር በእስራኤል ኃይሎች ከተያዘበት ከአውሮፓውያኑ ግንቦት 2024 ጀምሮ ዝግ ሆኖ ነበር የቆየው።

    እስራኤል እና ሐማስ ከስምምነት በደረሱበት እና ጥቅምት ወር ላይ ተግባራዊ መሆን በጀመረው የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ዕቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወቅት መከፈትም ነበረበት።

    ሆኖም እስራኤል በጋዛ የመጨረሻው ታጋች ዜጋዋ አስክሬን እስከሚመለስ ድረስ ዘግታው ቆይታለች።

    ባለፈው ሳምንት የመጨረሻው ታጋች አስክሬን ከተመለሰላት በኋላ አሁን ላይ ድንበሩ እንዲከፈት አድርጋለች።

    ይህም ለበርካታ ፍልስጤማውያን እፎይታን ሰጥቷል።

    ነገር ግን አሁንም በድንበሩ ማለፍ የሚፈቀድላቸው ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው እና ምንም ዓይነት ቁሳቁስ ይዞ መግባት ባለመቻሉ ስጋት ገብቷቸዋል።

    በአካባቢው እንዳሉ ሆስፒታሎች እና የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ህመምተኛ እና ጉዳት የደረሰባቸው ፍልስጤማውያን ለሕክምና ከጋዛ ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው።

    ከእስራኤል የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ በአንድ ቀን በድንበሩ መውጣት የሚችሉት ከአንድ ወይም ከሁለት አስታማሚ ጋር 50 ህሙማን ብቻ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ቀን በጦርነቱ ወቅት የተሰደዱ 50 ሰዎች ብቻ ወደ ጋዛ መመለስ እንደሚችሉ ተነግሯል።

    ከ30 ሺህ በላይ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ጋዛ ለመመለስ በካይሮ በሚገኘው የፍልስጤም ኤምባሲ ተመዝገብው እንደሚገኙም ተገልጿል።

  5. ኢራን በመጪዎቹ ቀናት ለአውሮፓ ኅብረት የአሸባሪነት ፍረጃ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ገለጸች

    የአውሮፓ ኅብረት፤ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን በአሸባሪነት መፈረጁን ተከትሎ ቴህራን በአገሯ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የኅብረቱ አምባሳደሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ እንደጠራች እና በመጪዎቹ ቀናት የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥም ገለጸች።

    የኢራን መንግሥት በመላ አገሪቱ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማፈን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በአስር ሺህዎች እንዲታሰሩ ያደረገ እርምጃ ወስዷል። ይህንን ተከትሎም የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሳምንት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካትቷል።

    ከዚህ ቀደም እንደ አሜሪካ እና ካናዳ ያሉ አገራትም ይህንን ወታደራዊ ኃይል በአሸባሪ ድርጅትነት ፈርጀው ነበር። ይህ ዓይነቱ እርምጃ በአዛኛው ትዕምርታዊ ቢሆንም አብዮታዊ ዘቡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተጽዕኖ ቀላል ባለመሆኑ የኢራን ምጣኔ ሀብትን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ይከትተዋል።

    ይህንን እርምጃ የተቃወመችው ኢራን ከእሑድ ዕለት ጀምሮ አምባሳደሮች መጥራት መጀመሯን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባግሃይ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ዘግቧል። ይህ ሂደት ዛሬ ሰኞም ቀጥሎ እንደሚውልም ቃል አቀባዩ አክለዋል።

    ቃል አቀባዩ፤ ሊወሰዱ የሚችሉ “ተከታታይነት ያላቸው እርምጃዎች ተገምግመዋል። በርካታ አማራጮች እየተዘጋጁ ነው፤ ወደ ውሳኔ ሰጪ አካላት ተልከዋል” ብለዋል።

    “በመጪዎቹ ቀናት የኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ የአውሮፓ ኅብረት ለወሰደው ሕገ ወጥ፣ ኢ-አመክንዮአዊ እና እጅግ የተሳሳተ እርምጃ የሚሆን የአጸፋ ምላሽ ላይ ውሳኔ ታሳልፋለች” ሲሉም ጠቁመዋል።

    ከዚህም ባሻገር፤ ኢራን በአውሮፓውያኑ 2019 የወጣን ሕግ በመጠቀም ሁሉምን አውሮፓ ኅብረት ሠራዊቶች በአሸባሪነት ለመፈረጅ እያሰበች መሆኑን አገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ገልጸዋል።

    ኢራን እነዚህን እርምጃዎች እየወሰደች ያለችው ከአሜሪካ የተቃጣባት የወታደራዊ እርምጃ ስጋት እያየለ ባለበት ወቅት ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች በመግደሉ እና የጅምላ የሞት ቅጣት ሊፈጸም እንደሚችል በመግለጽ እርምጃ ለመውሰድ መዛታቸው ይታወቃል።

    የአሜሪካ ጦር “ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን” የተባለው ግዙፍ የጦር መርከብ እንዲሁም በርካታ ሚሳኤል አውዳሚ መሣሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አንቀሳቅሷል።

    እስካሁን ድረስ ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኃይል ለመጠቀም ይወስኑ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እንዳይነሳ እየጣሩ ያሉ የቀጣናው አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።

  6. እስራኤል ኤምኤስኤፍ በጋዛ እንዳይሠራ ልታግድ ነው

    እስራኤል፤ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋዛ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደምታግድ አስታወቀች።

    የተራድኦ ድርጅቱ በጋዛ ያሉትን ሠራተኞች ዝርዝር ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት እገዳው እንዲጣል መወሰኑ ተገልጿል።

    የእስራኤል መንግሥት 37 ተቋማት አገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋዛ ያሉ ሠራተኞቻቸውን የተመለከቱ ሰነዶች እንዲያስረክቡ ጠይቋል።

    የእስራኤል መንግሥት ከኤምኤስኤፍ ሠራተኞች የተወሰኑት ከሐማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ ቢከስም ድርጅቱ ክሱን አስተባብሏል።

    ተቋሙ የፍልስጤማውያን እንዲሁም የሌሎች አገራት ሠራተኞቹን ዝርዝር ለእስራኤል መንግሥት እንደማይሰጥ አስታውቋል። የሠራተኞቹ ደኅንነት የተጠበቀ ስለመሆኑ ከእስራኤል ማረጋገጫ እንዳላገኘም ገልጿል።

    የእስራኤል መንግሥት “ኤምኤስኤፍ ሌሎች በቀጣናው እንደሚሠሩ ተቋማት የአገር ውስጥ ሠራተኞቹን ዝርዝር ለመስጠት አልፈቀደም” ብሏል።

    ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ እስራኤል “አዲሱን የምዝገባ ሒደት አልተከተሉም” ያለቻቸውን የ37 ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶችን ፈቃድ እንደምትሰርዝ አስታውቃለች።

    ተቋማቱ በጋዛ እና በግዳጅ ይዞታ ሥር ባለው ዌስት ባንክ ይሠሩ የነበሩ ናቸው። ከተቋማቱ መካከል ኤምኤስኤፍ፣ አክሽንኤድ እና ሮርዌጅያን ሬፍዩጂ ካውንስል የሚገኙበት ሲሆን፤ ሥራቸውን በ60 ቀናት ውስጥ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

  7. ቻይና ምያንማር ውስጥ የሳይበር ማጭበርበሪያ ካምፖችን የሚመሩ ተጨማሪ አራት ሰዎችን በሞት ቀጣች

    ቻይና፤ ምያንማር ውስጥ የሳይበር ማጭበርበሪያ ካምፖችን ከሚያስተዳድሩ ቡድኖች አንዱ የሆነው ‘ባይ’ የተሰኘ የቤተሰብ ማፊያ ቡድን አባላት የሆኑ አራት ሰዎችን በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    በሞት የተቀጡት ግለሰቦች፤ በማጭበርበር፣ በነፍስ ግድያ፣ በአካል ጉዳት ማድረስ እና በሌሎች ወንጀሎች ከተፈረደባቸው 21 የቤተሰቡ አባላት እና ግብረ አበሮቻቸው መካከል ናቸው።

    ባለፈው ኅዳር ላይ የቤተሰቡ መሪ የሆነው ባይ ሱኦቼንግን ጨምሮ አምስት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ የማፊያ ቤተሰቡ መሪ ከፍርዱ በኋላ ታምሞ ሕይወቱ እንዳለፈ የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ ያመለክታል።

    በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኙት የሳይበር ማጭበርበሪያ ማዕከላት ላይ ዘመቻ የከፈተችው ቻይና፤ ‘ሚንግ’ የተባለ ሌላ የማፊያ ቤተሰብ አባል የሆኑ 11 ሰዎችን ባለፈው ሳምንት በሞት ቀጥታለች።

    የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሆነባቸው የባይ እና ሚንግ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ቤተሰቦች የምያንማር የድንበር ከተማ የሆነችው ላውካይንግን ተቆጣጥረው የቁማር፣ የወሲብ ንግድ እና የሳይበር ማጭበርበር ተግባራት ለዓመታት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

    እነዚህ ተግባራት የሚፈጸሙባቸውን ማዕከላት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው ስቅይት እና እንግልት ሲፈጸምባቸው ነበር። ታይላንድ ውስጥ ሥራ እንደሚያገኙ ተነግሯቸው ወደ እነዚህ ካምፖች የተወሰዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ባለፈው ዓመት ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

    ካምፖቹን ከሚመሩ ቤተሰቦች መካከል “ቁጥር አንድ” ላይ የሚቀመጠው የባይ ቤተሰብ እንደሆነ የባይ ሱኦቼንግ ልጅ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግሮ ነበር።

    የቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት የባይ ቤተሰቦች የራሳቸውን ሚሊሻ የሚያስተዳድሩ ሲሆን ለሳይበር ማጭበርበር እና ለቁማር የሚውሉ 41 ካምፖችን መስርተው ነበር።

    በእነዚህ ካምፖች ውስጥ በሚገኙ የግዳጅ ሠራተኞች ላይ ድብደባ እና ስቅይት መፈጸም የተለመዱ ተግባራት እንደነበሩም ተገልጿል። የቤተሰቡ የወንጀል ድርጊቶች ስድስት ቻይናውያን እንዲሞቱ፣ አንድ ሰው ራሱን እንዲያጠፋ እንዲሁም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት እንደሆኑ ፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

  8. የኢራን ጠቅላይ መሪ ኻሜኒ አሜሪካ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ቀጣናዊ ጦርነት እንደሚነሳ አስጠነቀቁ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘውን ኃይሏን እያጠናከረች ካለችው አሜሪካ ጋር የተፋጠጡት የኢራን የጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፤ ዋሽንግተን ቴህራን ላይ የምትፈጽመው ማንኛውም ጥቃት ቀጣናዊ ጦርነት እንደሚያስነሳ አስጠነቀቁ።

    ኻሜኒ፤ “አሜሪካውያኖቹ ጦርነት ከጀመሩ በዚህ ጊዜ [የሚነሳው] ቀጣናዊ ጦርነት እንደሚሆን ማወቅ አለባቸው" ሲሉ መናገራቸውን ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ግንኙት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን "ቁም ነገር ያለው ውይይት" ላይ እንደሆነች እና ይህ ውይይት "ተቀባይነት ያለው" ውጤት ላይ እንደሚያደርስ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸው ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው፤ በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ "ስምምነት ላይ መድረስ እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ" ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን ኒውክሌር የማበልጸግ ፍላጎት እና ጸረ መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ በወሰደችው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የገደለ እርምጃ ምክንያት በማድረግ ጣልቃ እንደሚገቡ ዝተዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ፤ "እንደ አለመታደል ሆኖ አሜሪካን እንደ ተደራዳሪ አጋር ለማየት ያለን እምነት አጥተናል" ብለዋል።

    ሆኖም በቀጣናው ባሉ ወዳጅ አገራት በኩል የሚደረገው የመልዕክት ልውውጥ ከዋሽንግተን ጋር "ፍሬያማ" ንግግር እንዲኖር እያመቻቸ መሆኑን አክለዋል።

    የኢራን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን አሊ ላሪጃኒ የድርድር ማዕቀፍ የማዘጋጀት ሂደት ለውጥ እየታየበት እንደሆነ ገልጸው ነበር።

    በቀጣናው የሚገኘው ኃይሏን እያጠናከረች ያለችው አሜሪካ፤ ‘የዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን’ የተሰኘውን የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ አካባቢው ልካለች። ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በአረቢያን ባሕር ላይ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል።

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ኻሜኒ፤ "[ትራምፕ] በየጊዜው መርከቦችን አመጣሁ ይላል... የኢራን ሕዝብ እነዚህን ነገሮች አይፈራም" ብለዋል።

    ኢራን ከዓለም ወሳኝ የመርከብ መተላለፊያዎች አንዱ በሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ከእሑድ ዕለት አንስቶ ለሁለት ቀናት የሚቆይ እና ተኩስን የሚያካትት የባሕር ኃይል ልምምድ ማድረግ እንደምትጀምር ሲጠበቅ ነበር።

    ይሁን እንጂ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ያነጋገራቸው አንድ የኢራን ባለሥልጣን፤ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል እንዲህ ዓይነት ልምምድ የማድረግ ዕቅድ እንደሌለው መግለጻቸውን እሑድ ዕለት ዘግቧል።

    የዓለም ገበያ ላይ ከሚቀርበው ነዳጅ ውስጥ አንድ አምስተኛው የሚሆነው የሚተላለፈው ኢራን በምትቆጣጠረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነው። ቴህራን ከዚህ ቀደም ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ወሽመጡን እንደምትዘጋ ዝታ ነበር።