ትራምፕ በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባለቸው አገራት ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፈረሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አገራቱ ከቴህራን ጋር መገበያየት የሚቀጥሉ ከሆነ ቀረጡን ሊጥሉ እንደሚችሉ ተናገሩ። ኦማን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ንግግር ኢራን "ስምምነት ላይ ካልደረሰች ውጤቱ በጣም ከባድ ይሆናል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በናይጄሪያ የአሜሪካ ጦር መሰማራቱ ሲገለጽ ታጣቂዎች ከ100 በላይ ሰዎችን ገደሉ

    በናይጄሪያ ምዕራባዊ ግዛት ክዋራ ውስጥ በሁለት መንደሮች ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት እና የመብት ተሟጋቾች ተናገሩ።

    አጥቂዎቹ ሱቆችንና ቤቶችን እንዲሁም የባህል መሪውን መኖሪያ ቤት አቃጥለው የኑኩ እና የዎሮ ማኅበረሰቦችን ለቅቀው እንዲወጡ ማስገደዳቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን ሳይዱ ባባ አህመድ ለቢቢሲ ሃውሳ ተናግረዋል።

    ባለሥልጣናት ለጥቃቱ አክራሪ ቡድኖችን ተጠያቂ አድርገው ወታደሮችን ወደ ኳራ ካይማ አሰማርተዋል።

    ማክሰኞ ዕለት የተፈፀመው ጥቃት፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በናይጄሪያ ከተከሰቱት በርካታ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው።

    የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ወታደሮች ቡድን በስለላ እና በስልጠና ለመርዳት ወደ ናይጄሪያ ገብተዋል።

    የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቢ ለጥቃቱ የጂሃዲስት ቡድኑን ቦኮ ሃራምን ተጠያቂ አድርገዋል። የአካባቢው ሕግ አውጪ መሐመድ ኦማር ባዮ በበኩላቸው ለጥቃቱ ከኢስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት ያለው የታጠቀ ቡድን፣ ላኩራዋ ተጠያቂ ነው ብለዋል።

    የክዋራ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልራህማን አብዱልራዛቅ 75 ሰዎች "በጭካኔ ተገድለዋል" ብለዋል።

    አህመድ መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ ሃውሳ ቢያንስ 35 ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩ ቢሆንም ነገር ግን የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሟቾች ቁጥር አራት እጥፍ እንደሚበልጥ ተናግረዋል።

    በክዋራ የሚገኙ የቀይ መስቀል ኃላፊ የሆኑት ባባኦሞ አዮዴጂ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት "ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የሟቾች ቁጥር አሁን 162 ደርሷል፤ ተጨማሪ አስከሬኖችን ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ቀጥሏል" ብለዋል።

    አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ከ170 ሰዎች በላይ መገደላቸውን ገልጾ አብዛኞቹ የሞቱት ከቅርብ በተተኮሰባቸው ጥይት መሆኑን አስታውቋል።

  2. የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች በከፊል ከሚኒሶታ ሊወጡ ነው

    ከፍተኛ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው የአሜሪካ 700 ኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ከሚኒሶታ በከፊል ለቅቀው እንደሚወጡ ተገለፀ።

    ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከአሜሪካ በማባረር ጉዳይ የትራምፕ ቀኝ እጅግ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ቶም ሆማን የትራምፕ አስተዳደር በሚኒሶታ የሚገኙትን የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ቁጥርን ለመቀነስ ከግዛቲቱ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

    በታኅሣሥ ወር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚኒሶታ የሚገኙ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ለፌደራሉ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ ከ2000 በላይ የኢሚግሬሽን እና የጉሙሩክ ተቆጣጣሪዎች ከጥር ጀምሮ በሚኒሶታ ተሰማርተዋል።

    በዛሬው ዕለት ውሳኔው ይፋ ከመደረጉ በፊት የተወሰኑ የፌደራል ተቆጣጣሪዎች ሚኒሶታን ለቅቀው መውጣታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በግዛቲቱ የሚቆዩት የተወሰኑ የኢሚግሬሽን እና የጉሙሩክ ሠራተኞች ብቻ ይሆናሉ ተብሏል።

    የፌደራል የኢሚግሬሽን እና የጉሙሩክ ተቆጣጣሪዎች በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ሁለት ነጭ አሜሪካውያንን ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።

    የግዛቲቱ ነዋሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው ነበር። ይህንንም ተከትሎ የሚኒሶታ አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝ እና የሚኒስታ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ የፌደራል የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ከግዛቲቱ ዋና ዋና አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    ትራምፕ ግን አስተዳደራቸው ነገሮችን “ትንሽ እንደሚያረግብ” ተናግረው ነበር።

    ሆማን በዛሬው ውሳኔያቸው የፌደራል መንግሥቱ ተቆጣጣሪዎች ቁጥር ከታኅሣሥ በፊት ወደነበረበት መመለሱን ተናግረዋል።

    ነገር ግን ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎችን ለማስወጣት የአካባቢው ሕግ አስከባሪዎች እና የሰፊው ማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

  3. አሜሪካ የኢራንን ድሮን መትታ ከጣለች በኋላ በወርቅ ዋጋ ላይ ለውጥ ታየ

    ባለሃብቶች እንደ ደህንነቱ የጠበቀ መገበያያ የሚቆጥሩት ወርቅ አሜሪካ የኢራንን ድሮን መትታ ከጣለች በኋላ ዋጋው ዳግም ከ5000 ዶላር በላይ ከፍ ብሏል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ የግምጃ ቤት ኃላፊ ለመሾም ከመረጡ በኋላ የወርቅ ዋጋ ቅናሽ አሳእቶ ነበር።

    የወርቅ ዋጋ የአሜሪካን የንግድ ፖሊሲ፣ ቀጠናዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት ተከትሎ በከፍተኛ ፍጥነት ለውጥ እያሳየ ሲሆን ማዕከላዊ ባንኮችም ግዢያቸውን ጨምረዋል።

    ረቡዕ ዕለት የወርቅ ዋጋ ከ5,061 ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ዋጋ የ80 በመቶ ብልጫ እንዲያሳይ አድርጎታል።

    አሜሪካ፤ በአረቢያ ባህር ላይ ወደሚገኘው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ "በኃይል ሲቃረብ" የነበረ የኢራን ድሮንን መትታ መጣሏን የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ድሮኑ ላይ ጥቃት የፈጸመው “ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን” ከተባለው ግዙፍ የአሜሪካ የጦር መርከብ የተነሳ ኤፍ-35 ሲ የተሰኘ የራዳር እይታን የሚያመልጥ ተዋጊ ጄት እንደሆነ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቲም ሀውኪንስ ተናግረዋል።

    ቴህራን ማክሰኞ ዕለት ስለተፈጠረው እስካሁን ድረስ ምንም ያለችው ነገር የለም።

    የወርቅ ዋጋ ከአንድ ወር በፊት 5,500 ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ባለፈው ሳምንት አርብ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፌደራል ግምጃ ቤትን እንዲመሩ ኬቨን ዋርሽን መምረጣቸውን ተከትሎ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።

    አርብ ዕለት በወርቅ ዋጋ ላይ የታየው የ9 በመቶ ቅናሽ እአአ ከ1983 ወዲህ በአንድ ቀን የተመዘገበ ትልቅ ቅናሽ ሆኗል።

    ከ1979 ወዲህ የወርቅ ከፍተኛ ዓመታዊ ሽያጭ የተመዘገበው በ2025 ነው።

    የትራምፕ ታሪፍን ጨምሮ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የፈጠረው ስጋት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ክስተቶች ወርቅ በተከታታይ ዋጋው እንዲንር አድርገዋል።

  4. እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን ሆስፒታሎች አሳወቁ

    በሰሜን እና ደቡብ ጋዛ በእስራኤል በተፈጸመ ጥቃት 17 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ሆስፒታሎች አስታወቁ።

    የእስራኤል ጦር ጥቃቱ የተፈጸመው በሰሜናዊ ሰርጥ “አሸባሪዎች” ተኩስ ከፍተው በቢጫው መስመር ውስጥ በግዳጅ ላይ የነበረን ወታደር ክፉኛ ካቆሰሉ በኋላ ነው ብሏል።

    እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ እስራኤል የምትቆጣጠራቸው ስፍራዎች በቢጫ መስመር ተለይተው ተቀምጠዋል።

    የእስራኤል ጦር አክሎም የተኩስ አቁም ስምምነቱን “በግልጽ የጣሰ” ላለው ጥቃት የአየር ኃይሉ እና የምድር የጦሩ አባላት ዒላማውን የለየ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግሯል።

    የሆስፒታል ኃላፊዎች በጋዛ ከተማ እና ኻን ዮኒስ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከተገደሉት መካከል ስድስት ሕጻናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

    በጋዛ ከተማ የሚገኘው አል ሺፋ ሆስፒታል በድንኳናቸው እና መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሳሉ የተገደሉ የአምስት ሕጻናትን ጨምሮ የ13 ሰዎች አስከሬንን መረከቡን አስታውቋል።

    በኻን ዮኒስ የሚገኘው ናስር ሆስፒታል በበኩሉ በደቡባዊ ቂዛን ራሽዋን በሚገኝ መጠለያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሕጻንን ጨምሮ የአራት ሰዎች አስከሬን መረከቡን ይፋ አድርጓል።

    እስራኤል እና ሐማስ በጥቅምት ወር የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በመጣስ እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።

    የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ከተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 529 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጽ የእስራኤል ጦር በበኩሉ አራት ወታደሮቹ በፍልስጤማውያን ጥቃት እንደተገደሉበት ይፋ አድርጓል።

  5. ፔፕ ጉዋርዲዮላ፡ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የሚወጡ የሕፃናት ምስሎች “ያሳምሙኛል”

    ፔፕ ጉዋርዲዮላ ያላቸውን ቦታ ተጠቅመው “ለተሻለ ማኅበረሰብ” ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

    የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ባለፈው አርብ በትውልድ ከተማቸው ባርሴሎና በተካሄደው እና ለፍስልጤም ሕፃናት ፍትሕ በሚጠይቀው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ነበር።

    ክለባቸው ሲቲ በካራባዎ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ከኒውካስል ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጉዋርዲዮላ፤ በዓለማችን ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የሚወጡ የሕፃናት ምስሎች “ያሳምሙኛል” ብለዋል።

    አሰልጣኙ በፍልስጤም፣ ዩክሬን እና ሱዳን እንዲሁም በአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ አስፈፃሚ ፖሊሶች (አይስ) የሚፈፀሙ ግድያዎችን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

    “ማየት እስኪያቅተን ከመሆናችን በፊት ብንመለከተው መልካም ነው፤ በጣም ያሳምመኛል። በጣም አዝናለሁ። መናገሬን እቀጥላለሁ። ሁሌም። በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን ሰዎችን መግደል? ያሳምማል” ሲሉ ሐሳባቸውን ገልፀዋል።

    “ሰዎች ይህ ነገር እንዴት እንደማይሰማቸው ይገርመኛል። በየቀኑ የአባቶችን፣ የእናቶችን፣ ሕፃናትን ምስል ስታዩ፤ ሕይወታቸው ተመሳቅሎ ሲታይ እንዴት ይህ ነገር አይሰማቸውም?” ሲሉ ጠይቀዋል።

    “በሰው ልክ ታሪክ እንዲህ ያለ ግልፅ የሆነ መረጃ ታይቶ አይታወቅም። የፍልስጤም ዘር ጭፍጨፋ፣ በዩክሬን እየሆነ ያለው ነገር፤ በሩሲያ እየሆነ ያለው ነገር፤ በመላው ዓለም - በሱዳን፣ ሁሉም ቦታ።”

    በጋዛ ጦርነት ድምፃቸውን ካሰሙ የእግር ኳስ ዓለም ሰዎች አንዱ የሆኑት ስፔናዊው አሰልጣኝ በመርከብ ተጭነው ወደ አውሮፓ ስለሚመጡ ስደተኞችም አስተያየት ሰጥተዋል።

    “ይህን የሚያደርጉ ሰዎች፤ ከሀገራቸው ሸሽተው በባሕር አቋርጠው በጀልባ የሚመጡ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ትክክል ነው አይደለም ብላችሁ አትጠይቁ። መጀመሪያ ታደጓቸው። ይህ የሰብዓዊነት ጉዳይ ነው” ብለዋል

  6. ስደተኞችን የጫነ ጀልባ ከግሪክ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ ጋር ተጋጭቶ 15 ሰዎች ሞቱ

    ስደተኞችን ጭኖ ከቱርክ የተነሳ ፈጣን ጀልባ በቺዮስ ደሴት አካባቢ ከግሪክ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ ጋር ተጋጭቶ ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

    የግሪክ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ግጭቱ የፈጠረው በቭሮንታደስ መንደር አቅራቢያ በሚገኘው የቺዮስ የባሕር ወሽመጥ ላይ ነው። አደጋው በደረሰበት ወቅት ስደተኞችን የጫነው ጀልባ አደገኛ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደነበረ ገልጸዋል። የባሕር ጠባቂዎችም ክትትል እያደረጉበት እንደነበር አክለዋል።

    የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች፤ ከቱርክ የባሕር ዳርቻ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገኘው ቺዮስ ደሴት ስደተኞችን የምታጓጉዝ አነስተኛ ጀልባ ተመልክተው ወደ መጣችበት እንድትመለስ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበር አንድ ባለሥልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ባለሥልጣኑ "አዘዋዋሪዎቹ ጀልባዋን ወደ ባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከቧ በማስጠጋት ግጭቱ እንዲከሰት አድርገዋል" ሲሉ ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጸዋል።

    ጀልባው ላይ ከ30 እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር የዐይን እማኞች መናገራቸውን ባለሥልጣኑ አክለዋል።

    ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ 25 ሰዎችን ማዳን ተችሎ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን አዲት ስደተኛ ሕይወቷ እንዳለፈ ተገልጿል። በሕይወት ከተረፉት ውስጥ አንዳንዶቹ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጀልባው ላይ የነበሩ ሌሎች ስደተኞች ደግሞ አሁንም እንደጠፉ መሆኑ ተዘግቧል።

    የግሪክ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ጉዳት ከደረሰባቸው ስደተኞች መካከል ሰባት ሕፃናት እና አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ይገኙበታል። ሁለት የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መኮንኖችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

    ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ዜግነት እስካሁን አልታወቀም። በአውሮፓ ደቡብ ምሥራቅ ጥግ ላይ የምትገኘው ግሪክ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ የሚመጡ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ይመርጧታል።

  7. በቱርክ ይካሄዳል የተባለው የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር ወደ ኦማን ተዛወረ

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ቱርክ ውስጥ ሊደረግ የነበረው ድርድር በኢራን ጥያቄ መሠረት ወደ ኦማን ተዘዋውሮ አርብ ዕለት እንደሚካሄድ ተነገረ።

    ለሳምንታት የዘለቀውን ውጥረት ያረገበው የንግግር ስምምነት በኢራን የኒውክሌር ፐሮግራም ላይ አተኩሮ ኦማን ውስጥ አርብ ዕለት መካሄድ እንደሚጀምር ሮይተርስ አክሲዮስን ጠቅሷ ዘግቧል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ወደ ጦርነት የሚያመራ ውጥረት ለማርገብ ቱርክ ጥረት ስታደርግ ቆይታ ንግግሩም በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ ኢስታንቡል ውስጥ እንዲካሄድ ዕቅድ ተይዞ ነበር።

    ነገር ግን ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ኢራን የድርድሩ ስፍራ ወደ ኦማን እንዲዞር ያቀረበችውን ጥያቄ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ተቀብሎታል።

    ከአሜሪካ እና ከኢራን በተጨማሪ በድርድሩ ላይ ሌሎች የአረብ እና የሙስሊም አገራት ይሳተፉ እንደሆነ ለመወሰን ንግግር እየተካሄደ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

    አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ግዙፍ የባሕር ኃይል መርከቦቿን ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ካሰማራች በኋላ በኢራን ላይ ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚል ስጋት አይሎ ነበር።

    ነገር ግን ኢራን ለድርድር ፈቃደኛ በመሆኗ እና አሜሪካም ስለተቀበለችው ይህ ሳምንት ከመጠናቀቁ በፊት ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ ንግግሩ ውጤት የማያመጣ ከሆነ እርምጃ እንደሚውስዱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እያስጠነቀቁ ነው።

  8. የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ለእስራኤል የማዕድን መብት እንደሚሰጡ ተናገሩ

    የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት በቅርቡ ከእስራኤል ጋር የንግድ ስምምነት እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ`።

    ከሮይተርስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሒ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር በቅርቡ “የንግድ ስምምነት” እንደምትፈፅም ተናግረዋል።

    ሀገራቸው “በማዕድን፣ ነዳጅ እና ግብርና ሀብት የበለፀገች” እንደሆነች የተናገሩት ፕሬዝደንቱ፤ እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳልተፈፀመ ቢናገሩም በቅርቡ እንደሚፈፀም “መቶ በመቶ” እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

    ለቴል-አቪቭ የማዕድን መብት ለመስጠት ቃል የገቡት ፕሬዝደንት በምትኩ ሶማሊላንድ ከእስራኤል የምትፈልገው ቴክኖሎጂያዊ ትብብር እንደሆነም አስረድተዋል።

    ሶማሊላንድ ለባትሪ እና ለኤሌክትሪክ መኪና ወሳኝ የሚባለውን ሊቲየም የተባለ ማዕድን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች እንዳሏት ትገልፃለች።

    በአውሮፓውያኑ 2024 ኪሎማስ የተሰኘው የሳዑዲ ማዕድን አውጭ ኩባንያ ሊቲየም እና ሌሎች አስፈላጊ ማዕድኖችን ለማውጣት ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል።

    አብዱላሒ ለተሰጣቸው የሀገርነት እውቅና አመስግነው ሶማሊላንድ ከእስራኤል ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ እንደምትሻ ቢገልፁም እስራኤል ወታደራዊ ሰፈር በምትገነባበት ጉዳይ ላይ ውይይት እንዳልተካሄደ አሳውቀዋል።

    እስራኤልን ለመጎብኘት ከኔታኒያሁ ግብዣ ቀርቦላቸው ቢቀበሉም ቀን እንዳልተቆረጠ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና ተከትሎ ሶማሊያ፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ ግብፅ እና የአፍሪካ ኅብረት ቁጣቸውን አሰምተዋል።

    ፕሬዝደንቱ ከእስራኤል በተጨማሪ ሌሎች የተባበሩት መንግሥት ሀገራት በተለይ ደግሞ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች እና ዩናይትድ ስቴትስ ለሶማሊላንድ እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

  9. አሜሪካ ወደ ጦር መርከቧ ሲበር የነበረን የኢራን ድሮን መትታ መጣሏን አስታወቀች

    አሜሪካ፤ በአረቢያ ባህር ላይ ወደሚገኘው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ "በኃይል ሲቃረብ" የነበረ የኢራን ድሮንን መትታ መጣሏን የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ገለጹ።

    ድሮኑ ላይ ጥቃት የፈጸመው 'ዩኤስኤስ አብርሀም' ሊንከን ከተባለው ግዙፉ የአሜሪካ የጦር መርከብ የተነሳ ኤፍ-35 ሲ የተሰኘ የራዳር እይታን የሚያመልጥ ተዋጊ ጄት እንደሆነ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቲም ሀውኪንስ ተናግረዋል።

    እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ የማክሰኞ ዕለቱ "ራስን የመከላከል እርምጃ" የተወሰደው አውሮፕላን ተሸካሚውን መርከብ እና ሠራተኞቹን ለመጠበቅ ሲባል ነው።

    ሲበር የነበረበት “ዓላማ ግልጽ እንዳልሆነ” የተገለጸው ድሮን በሚጠጋበት ወቅት የአሜሪካ የጦር መርከብ ከኢራን የባህር ዳርቻ በግምት 805 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደነበረም ተገልጿል።

    ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ የተጎዳ የአሜሪካ ወታደርም ሆነ ንብረት የለም ተብሏል። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለው ውጥረት እየበረታ መሆኑን ተከትሎ ዋሽንግተን በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ ኃይል እያጠናከረች ባለችበት ወቅት ነው።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመገደብ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ድርድር ካላደረገች እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ የአገሪቱ መንግሥት በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰደውን እርምጃ በመቃወም ጣልቃ እንደሚገቡ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

    የኢራን ድሮን ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት፤ አሜሪካ እና ኢራን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለማካሄድ የቀጠሩት ድርድር አሁንም እንደተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

    ትራምፕ "ሁልጊዜም ለዲፕሎማሲ ቅድሚያ ለመስጠት ቁርጠኛ" እንደሆኑ የተናገሩት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ ነገር ግን "ሁሉም ቢሆን ወታደራዊ ኃይልን መጠቀም ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች ጠረጴዛ ላይ እንዳሉ" አስገንዝበዋል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በበኩላቸው አገራቸው ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት ጥቃት “ቀጣናዊ ጦርነት” እንደሚያስነሳ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

    የትናንቱን የድሮን ክስተት በተመለከተ ግን እስካሁን ድረስ ከቴህራን በኩል የተሰ አስተያየት የለም።

    በሌላ በኩል ማክሰኞ ዕለት፣ የኢራን የእስልማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ሲያልፍ በነበረ “የአሜሪካ ባንዲራ የሰቀለ እና አሜሪካዊ ሠራተኞችን የያዘ የንግድ መርከብ ላይ ትንኮሳ" እንደፈጸመ የአሜሪካ ጦር ገልጿል።

    ይሁን እንጂ ለመርከቡ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ተደርጎ ሁኔታው እንደተረጋጋ እና መርከቡ በሰላም እንዳለፈ ካፒቴን ሀውኪንስ ገልጸዋል።

  10. የ14 ዓመት የቤት ሠራተኛዋን የገደለች ሴት ሶማሊያ ውስጥ ተረሸነች

    በሶማሊያዋ ከፊል ራስገዝ ክልል ፑንትላንድ ውስጥ የ14 ዓመት ታዳጊ የቤት ሠራተኛዋን በድብደባ ገድላለች የተባለች ሴት በጥይት የሞት ፍርድ ተፈጸመባት።

    የ34 ዓመቷ ተከሳሽ ሆዳን ሞሐመድ ዲሪዬ የቤት ሠራተኛዋን ባለፈው ኅዳር መግደሏ ይፋ ከሆነ በኋላ በሕዝቡ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን፣ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ጋልካዮ ውስጥ ዛሬ ተረሽናልች።

    ታዳጊዋ ሟች የአንድ ዓመት ሕጻን ሳለች ወላጆቿ በመሞታቸው በዘመዶቿ ያደገች ሲሆን፣ ገዳይ የቤት ሠራተኛ እንደምትፈልግ በገለጸችበት ባለፈው ዓመት ነበር የወሰደቻት።

    ታዳጊዋ በቆይታዋ ተደጋጋሚ ድብደባ እና ስቃይ እንደተፈጸመባት የፖሊስ ምርመራ ከማረጋገጡ በተጨማሪ፣ ከገዳይ ስልክ ላይ ይህንን የሚያጋልጥ የድምጽ እና የቪዲዮ ቅጂ ተገኝቷል።

    ባለሥልጣናት እንዳሉት የሞት ቅጣቱ የተፈጸመው የሟች ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ ሳይሆን በፍርዱ መሠረት ተከሳሿ እንድትገደል በመጠየቃቸው ነው።

    ይህም በግዛቲቱ ውስጥ ተግባራዊ በሚደረገው እስላማዊ ሕግ መሠረትነት መሆኑ ተነግሯል።

    የሞት ቅጣቱ በሚፈጸምበት ወቅት የሟች እና የገዳይ ቤተሰቦች በሥፍራው እንደነበሩ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እንዳሉት እንዲህ ያለው የሞት ቅጣት በሴት ተከሳሽ ላይ ሲፈጸም ከአስር ዓመታት በኋላ ነው።

    የመጨረሻው የሞት ቅጣት የተፈጸመው ከ13 ዓመት በፊት አንድ ታዋቂ እስላማዊ መምህርን በመግደል ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ አንዲት ሴት የምትገኝበት 13 የአል ሻባብ አባላት በተረሸኑበ ጊዜ ነበር።

  11. ኬንያውያን ለፍቅረኞች ቀን ከገንዘብ ኖት የአበባ እቅፍ እንዳይሠሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

    የኬንያ የገንዘብ ኖትን ተጠቅመው የአበባ እቅፍ የሚሠሩ ኬንያውያን ከአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።

    ከገንዘብ የአበባ እቅፍ መሥራት በተለይም ከፍቅረኞች ቀን ጋር በተያያዘ እየተለመደ መጥቷል።

    ኬንያውያን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ከገንዘብ የተሠራ የአበባ እቅፍ ይዘው የሚሠሯቸው ቪድዮዎች ዝነኛ ናቸው።

    የተለያየ ዋጋ ያለው የኬንያ ሽልንግ በመጠቀም የአበባ እቅፍ የሚያዘጋጁ ሰዎች እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ የኬንያ ብሔራዊ ባንክ አስጠንቅቋል።

    “የገንዘብ ኖት ታጥፎ፣ ተጠቅልሎ፣ እርስ በርሱ ተጣብቆ እና በሌላም ቅርጽ አበባ እየሆነ ነው። ይህም ዋጋውን ያሳጣዋል” ሲል ብሔራዊ ባንኩ አስታውቋል።

    ገንዘቡ ኤቲኤም ማሽኖችን እያበላሸ እንደሆነ እንዲሁም አገሪቱ ለአላስፈላጊ ወጪ እንደተዳረገች መሆኑን አክሏል።

    የገንዘብ ኖት በስጦታ መቅረቡን እንደማይቃወም የገለጸው ባንኩ፤ ከእቅፍ አበባ ውጪ ሌሎች አማራጮች እንዲፈለጉም አሳስቧል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የባንኩን ውሳኔ በመደገፍ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ።

    “ወንዶች ለፍቅረኞች ቀን ተፈጥሯዊ አበባ ወደመግዛት ተመለሱ” ሲል አንድ ሰው በኤክስ ገጹ ጽፏል።

    ሌላ ኬንያዊ ደግሞ “የገንዘብ የአበባ እቅፍ ውድ ነው፤ ብክነትም ነው” ብሏል።

  12. የፈረንሳይ ፖሊስ ኢሎን መስክ የሚያስተዳድረውን የኤክስ ቢሮ ፈተሸ

    የፈረንሳይ ፖሊስ የበይነ መረብ ወንጀል ክፍል እና ዩሮፖል (የአውሮፓ ኅብረት ፖሊስ)፤ ኢሎን መስክ የሚያስተዳድረው የኤክስ ቢሮን መፈተሻቸው ተገለጸ።

    የፓሪስ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ብርበራው የተካሄደው የኤክስ ቻትቦት የሆነው ግሮክ ላይ እየተደረገ ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ነው።

    በኤክስ ገጽ ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና አስተያየት የሚሰጠው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቻትቦት ግሮክ፤ የተዛባ መረጃ እያቀረበ ነው በሚል እየተከሰሰ ይገኛል።

    መስክ እና የኤክስ የቀድሞ ዋና ኃላፊ ሊንዳ ያኮሪኖ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ታዝዘዋል።

    ኤክስ ጉዳዩን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

    ግሮክ በዲፕፌክ የተሠሩ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምሥሎችን እያቀረበ ነው በሚል ምርመራ ተከፍቶበታል። ኤክስ ግን የንግግር ነጻነትን የሚቃረን “ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ” ውንጀላ ነው ሲል አጣጥሎታል።

    ግሮክ የሕጻናት ምሥል ወሲባዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ፣ በዲፕፌክ የሰዎች ምሥል ወሲባዊ እንዲሆን በማድረግ እና የግለሰቦችን መረጃ በመበዝበዝ ተከስሷል።

    የሴቶች ምሥል ያለፈቃዳቸው ወሲባዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረጉ ግሮክም እየተከሰሰ ይገኛል።

    የፓሪስ ዐቃቤ ሕግ የኤክስ ገጹን አጥፍቶ በኢንስታግራም እና ሊንክድኢን አማካኝነት መረጃ ማስተላለፍ ጀምሯል።

  13. “[የባሕር በር ማግኘት] በባሌም ሆነ በቦሌ አይቀርም”- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የባሕር በር ጥያቄን በሚመለከት ስለሚሠሩ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ሲናገሩ “የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በዲፕሎማሲ እና በሰጥቶ መቀበል ለማሳካት እየጣርን ነው፤ ነገር ግን በባሌም ሆነ በቦሌ መሳካቱ አይቀርም" አሉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የባሕር በርን "በሆነ ምክንያት መከልከል ቢታሰብ በቀጣይት መከልከል አይቻልም" በማለት “ወደማያስፈልግ ነገር ከመገባቱ በፊት በሰላም፣ በድርድር መጨረስ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

    "ኢትዮጵያ የባሕር በር አያስፈልጋትም ብሎ የሚያምን ተፈጥሯዊ ሕግ የሳተ ይመስለኛ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በሆነ ጊዜ መድከም እና ማርጀት ቢኖርም ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም" ብለዋል።

    ከምጽዋ ጫፍ እስከ ሞቃዲሾ 5 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የጠየቀችው 50 ኪሎ ሜትር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    ኢትዮጵያ የባሕር በር በጦርነት ሳይሆን ሰጥቶ በመቀበል መርኅ ከሕዳሴ ግድብ ወይንም ከአየር መንገዱ ድርሻ በመውሰድ በሰላማዊ መንገድ በንግድ ሕግ ለማግኘት እንደምትፈለግ በመገልጽ ይህንን መቀበል “የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የግድ ይመስለኛል” ብለዋል።

    ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት የሚፈሱትን ወንዞች መከልከል እንደማይቻለው እና ትክክል አንዳልሆነ እኛም ማጋራት አለብን እነርሱም ማጋራት አለባቸው ብለዋል።

    “እኛ ስጡን ብቻ አላልንም። እኛም ጋር የቀረ ነገራችሁን ውሰዱ፤ ያጠፋነውን ይቅርታ አድርጉ፤ ግን በቀጣይነት ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ጸጋዋ ማስቀረት ያስቸግራል።”

    የተለያዩ የዓለም አገራት ተወካዮችን ሲያነጋግሩ በአንድ አፍ ‘ይገባችኋል፤ ተገቢ ጥያቄ ነው ግን በጦርነት መሆን የለበትም” እንደሚሏቸውም ተናግረዋል።

    ወዳጆቻችን “እንወያይ እንምከር ጊዜ ስጡን” ብለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም ጊዜ ወስደው እንዲወያዩ መስማማቷን ተናግረዋል።

    130 ሚሊዮን ሕዝብ የሁሉ ጎረቤት ዕዳ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር የማይኖራት ከሆነ “ኢትዮጵያ ያሰበችውን ብልጽግና ማሳካት አትችልም” ሲሉ ተናግረዋል።

    በዲፕሎማሲ ረገድ መልካም ጅማሮዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ጊዜያቸውን ጠብቀው ፍሬ እነደሚያፈሩ በመግለጽ የባሕር በር የማግኘቱ ጉዳይ “በባሌም ሆነ በቦሌ አይቀርም” ብለዋል።

  14. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ የተጀመረው በትግራይ ጦርነት ወቅት ነው" አሉ

    በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል በአሁኑ ጊዜ የሚታየው መቃቃር የተፈጠረው በቅርብ ጊዜ ሳይሆን በትግራይ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ።

    "አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ችግር የተከሰተው የኢትዮጵያ መንግሥት የቀይ ባሕር ጉዳይን ስላነሳ ነው ብለው" አንደሚያስቡ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ይህ ግን ስህተት ነው" ብለዋል።

    "ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ችግር ነበረ።አኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልገንም ይቅርብን ብለን ለምነናል።

    "ፀቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባሕር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም አንጂ።

    "አክሱምን ይዘን ስናልፍ፤ አክሱም ገብቶ ወጣቶችን በጅምላ ሲረሽን ፀብ ተፋገፍሟል። አድዋን ይዘን ስናልፍ፣ አድዋ ሄዶ ፋብሪካዎችን ሲፈታታ፣ ሲሰርቅ ፀብ ተጋግሏል።

    "አዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅሎ የማይነቀለውን ሲያፈራርስ ፀቡ ጫፍ ደርሷል። ግን ያኔ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህም በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም።"

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን መላካቸውን ተናግረዋል።

  15. የኢራን እና የአሜሪካ ተወካዮች ለድርድር ሊቀመጡ ነው

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤስኪያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከአሜሪካ ጋር ፍትሐዊ ድርድር እንዲደረግ ማዘዛቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አስታወቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሉት "ወዳጅ መንግሥታት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ጥቅማችንን በሚያስከብር ሁኔታ ለፍትሐዊ እና ለትክክለኛ ድርድር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታን እንዲያመቻቹ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ያስታወቁት፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተወካያቸው ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን እና ግንኙነቱ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ትራምፕ አሁንም የሚደረጉ ንግግሮች ውጤት የማያስገኙ ከሆነ “መጥፎ ነገር ይከሰታል” በማለት በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።

    በቀጣይ ቀናት ምናልባትም በመጪው አርብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ ሊገናኙ ቀጠሮ እንደተያዘላቸው ዘገባዎች እየወጡ ነው።

  16. "በሕዳሴ ላይ አንድም ብር እርዳታ፣ አንድም ብር ብድር ኢትዮጵያ አልወሰደችም"- ጠ/ሚ ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት አንድም ብድር እና እርዳታ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ወገን አለመውሰዷን ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሚሰጡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

    "በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም፤ በአገርም ውስጥ ከአገር ውጪም ባሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሠሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ለግድቡ ግንባታ ብድርም ሆነ እርዳታ እንዳልወሰደች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የታላቁ ሕዳሴ ግደብን ግንባታን በገንዘብ መደገፏን በቅርቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆየ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በከፍተኛ ባለሥልጣን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ገንብታ ብቻ እንዳልቆመች በመግለጽ "ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነውን ኮይሻን እየሠራች ነው" ብለዋል።

    በኢትዮጵያ ውስጥ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ሥራ አለመቆሙን ለምክር ቤት አባላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአፍሪካ አንደኛው ኤርፖርት ግንባታም ተጀምሯል ብለዋል።

  17. የቀድሞው የ'አርሚ 15' አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ገብረ በዋስ ተለቀቁ

    የቀድሞው የ'አርሚ 15' አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ገብረ በዋስ መለቀቃቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት እና የቤተሰብ አባላት ተናገሩ።

    ጄነራሉ በዋስ የተፈቱት ሰኞ ጥር 25/2018 ዓ.ም. ወታደራዊ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል።

    “ቀደም ሲል በሕግ ሂደት ምክንያት የታሰሩት ጄነራል ጉዕሽ ገብረ፣ ከውጭ ሆነው ክሳቸውን አንዲከታተሉ በዋስ ተለቀዋል” ሲል የትግራይ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

    ጥር 9/2018 ዓ.ም. በየፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ብርጋዴር ጄነራል፡ “ከጠላት ጋር በመገናኘት፣ ሠራዊቱን ለማፍረስ እና የከፍተኛ አመራሮችን ትዕዛዝ በመጣስ” ክስ ተመሥርቶባቸዋል ሲሉ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

    ቤተሰቦቻቸው በጄነራሉ አያያዝ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ የሰነበቱ ሲሆን፣ የትግራይ የሰላም እና የፀጥታ ባለሥልጣናት ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ከቤተሰቦቻቸው እንዲገናኙ ማድረጉን ይገልፋል።

    የትግራይ ኃይል የአርሚ 15 የቀድሞ አዛዥ ጄነራል ጉዕሽ እስካሁን ድረስ ስለተመሠረተባቸው ክስ ይፋዊ መግለጫ ባይሰጡም፣ ደጋፊዎቻቸው ግን በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት እንደታሰሩ ይገልጻሉ።

    በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነትና አለመግባባት ባለፈው ዓመት ወደ ከፍተኛ የጦር አዛዦችን መዛመቱን የሚታወስ ሲሆን ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ አስገብቷቸዋል።

    አብዛኞቹ ከፍተኛ የትግራይ ኃይሎች አዛዦች በዶ/ር ደብረጽን የሚመራውን የህወሓት አንጃ ደግፈው፣ በአቶ በጌታቸው ረዳ ሲመራ የነበረውን የቀድሞውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈረስ መወሳነቸውን ተክትሎ ነው ውጥረቱ የተፈጠረው።

  18. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ጀመረ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቀናት አቋርጦት የነበረውን ወደ ትግራይ የሚያደርገውን በረራ ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ በተደረገ በረራ መልሶ ተጀመረ።

    ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ነበር በረራዎች ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ የተቋረጡት።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቦታ መያዥ የበይነ መረብ ገጽ በትግራይ ክልል ወደ ሚገኙ ሁሉም መዳረሻዎች የሚደረጉ በረራዎች ክፍት መሆናቸውን ያመለክታል።

    ባለፈው ሳምንት በረራዎች ከመቋረጣቸው በፊት አየር መንገዱ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በየቀኑ ስምነት በረራዎች ያደርግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ወደ አምስት በረራዎች መቀነሱትን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  19. በአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ የሚሰማሩ የፌደራል ኃይሎች የሰውነት ካሜራ ሊገጠምባቸው ነው

    ባለፉት ሳምንታት በተቃውሞ ስትናጥ በቆየችው የሚኒሶታ ግዛቷ ሚኒያፖሊስ ከተማ የሚሰማሩ የፌደራል ኢሚግሬሽን ኃይሎች የሰውነት ካሜራ አድርገው መንቀሳቀስ እንደሚጀምሩ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት አስታወቀ።

    መስሪያ ቤቱ ይህንን አዲስ እርምጃ ያስታወቀው የፌደራል ኢሚግሬሽን ኃይሎች አሌክስ ፕሬቲ እና ሬኔ ጉድ የተባሉት ሁለት አሜሪካውያንን በሳምንታት ልዩነት ውስጥ መግደላቸውን ተከትሎ መንግሥት ላይ ተቃውሞ በመነሳቱ ነው።

    የሁለቱን ሰዎች ሕይወቱ የቀጠፈውን እርምጃ የወሰዱት የፌደራል ኃይሎቹ የተሰማሩት ስደተኞች ለመያዝ ሚኒያፖሊስ ውስጥ ከተሰማሩ በኋላ ነው።

    የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክርስቲ ኖም “ከአሁን ጀምሮ ሚኒያፖሊስ ውስጥ የሚሰማሩ ሁሉም መኮንኖች ላይ የሰውነት ካሜራ እንገጥማለን” ሲሉ ሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    የሄነፒን ካውንቲ የህክምና መርማሪ ባደረገው ምርመራ በፌደራል ኃይሎች እርምጃ ምክንያት የተከሰተውን የፕሬቲ ሞት ‘ግድያ’ እንደሆነ ደምድሟል። ይህ ድምዳሜ አንድ ሰው በሌላ ሰው መገደሉን የሚያመለክት ቢሆንም በትክክል ወንጀል ተፈጽሟል የሚለውን የሚያረጋግጥ ላይሆን ይችላል።

    ሰኞ ዕለት የወጣው የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው፤ ፕሬቲ በአንድ ወይም ከዚያ በሚበልጡ የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰበት ጥይት “በርካታ የተኩስ ቁስሎችን” አስተናግዷል።

    ግለሰቡ ሚኒያፖሊስ ውስጥ ወደሚገኘው የሄነፒን ካውንቲ የሕክምና ማዕከል የድንገተኛ ክፍል ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ ማለፉንም መረጃው ያመለክታል።

    የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር መስሪያ ቤት እንደሚገልጸው ከሆነ የፕሬቲ ሞት ውስጥ እጃቸው ያለበት ሁለቱ የፌደራል ላይሎች የሰውነት ላይ ካሜራ አድርገው ነበር። ወኪሎቹ ለጊዜው ከሥራ ታግደው እንዲቆዩ መደረጉንም መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

    የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር በበኩሉ በፕሬቲ ሞት ዙሪያ የሲቪል መብት ጥሰት ምርመራ መክፈቱን ገልጿል።

    የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክርስቲ ኖም፤ የገንዘብ ድጋፍ እንደተገኘ ፌደራል ኃይሎች ላይ የሰውነት ካሜራ የመግጠም ስራው በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከወን ይደረጋል።

    ስለዚህ እቅድ አስተያየታቸው የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሰውነት ካሜራ ሲገጠም “በጥቅሉ የሕግ አስከባሪዎች ጥሩ ወደመሆን እንዲያዘነብሉ ያደርጋል፤ ምክንያቱም ሰዎች ስለሚፈጠረው ነገር መዋሸት አይችሉም" ብለዋል።

    "በአጠቃላይ ሲታይ 80 በመቶ ያህል ለሕግ አስከባሪዎች ጥሩ ይመስለኛል" ብለዋል።

  20. "የሚያከብረንን እናከብራለን፤ ለሚዝትብን ደግሞ ተመሳሳይ መልስ እንሰጣለን” ኢራን

    ኢራን የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ከየትኛውም ወገን ለሚሰነዘር አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ነገር ተመጣጣኝ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታወቀች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ በኩል የሚሰነዘሩትን ዛቻዎች እና የውይይት ሃሳቦች በመጥቀስ ኢራን ለሁሉም እንዳመጣጡ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

    "በአክብሮት ለሚያናግረን በአክብሮት እንመልሳለን። በማስፈራራት ለሚያናግረንም በተመሳሳይ ቋንቋ መልስ እንሰጣለን።ለዲፕሎማሲ ዝግጁ ነን፤ ነገር ግን ዲፕሎማሲ ከማስፈራራት እና ከጫና ጋር አብሮ አይሄድም።ዲፕሎማሲ የራሱ መንገድ አለው” ብለዋል።

    የኢራን ዋነኛው ዲፕሎማት ጨምረውም አሜሪካ ወደ ዲፕሎማሲው ፊቷን ያዞረችው በሕዝባዊ ተቃውሞው አማካይነት የታሰበው ‘ሴራ’ ስላልተሳካ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

    ሚኒስትሩ በድጋሚ አሜሪካ እና እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለውበታል በተባለው ለሳምንታት በዘለቀው ተቃውሞ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ከስሰዋቸዋል።

    በኢራን የተካሄደው ተቃውሞ ኢራን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ባለፈው ዓመት ሰኔ ለ12 ቀናት ያደረጉት ጦርነት ተከታይ ጥቃት ነው በማለት “ተቃውሞዎቹ ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም” ብለዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም እየዛተች እና ኢራን ምላሽ እንደምትሰጥ እያስጠነቀቀች ባሉበት ጊዜ ንግግር ለመጀመር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን የንግግር ሃሳብ የመጣው "ሴራቸው ከከሸፈ በኋላ ነው፤ አሁን እነሱ ናቸው ስለዲፕሎማሲ የሚያወሩት። እኛ ሁሌም ለዲፕሎማሲ ዝግጁ ነን” በማለት “በእኩልነት፣ በጋራ መከባበር እና ለጋራ ጥቅም” እንደሚደራደሩ ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ ንግግር የተሰማው በዋሺንግተን እና በቴህራን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚደረገው ጥረት በተጠከናረበት እና በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ ድርድር ለመጀመር አመቺ ሁኔታዎች እንዳሉ እየተነገረ ባለበት ጊዜ ነው።