የኢራን እና አሜሪካን የሰላም ንግግር ለማስቀጠል የፓኪስታን ባለሥልጣን ቴህራን ገቡ

የፓኪስታን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሞህሲን ናቂቭ በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተቋረጠውን የሰላም ንግግር ለማስቀጠል ቴህራን መግባታቸው ተገለጸ። የጉዞው ዓላማ “ንግግሮች እንዲካሄዱ ለማመቻች እና ቀጣናዊ ሰላም ለማስፈን” መሆኑ ተገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቻይና ቴህራን ላይ የሚጣል ማዕቀብ ኩባንያዎቼን ይጎዳል በሚል ተቃወመች

    የቻይና እና የአሜሪካ ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ መቀመጫቸውን ቻይና ባደረጉ ሦስት ኩባንያዎች ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ቤይጂንግ ተቃወመች።

    ቤይጂንግ ተቃውሞዋን ያሰማችው ኩባንያዎቹ የኢራንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ደግፈዋል በሚል ውንጀላ ከቀረበባቸው በኋላ ነው።

    ሰኞ ዕለት ጠንካራ ተቃውሞዋን የገለጸችው ቤይጂንግ ማዕቀቦቹን ሕገ ወጥ እና የአንድ ወገን ውሳኔ ብላ ጠርታዋለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ጉኦ ጂያኩን “ምንጊዜም የቻይና ኩባንያዎችን ሥራቸውን በሕግ እና መመሪያዎች መሠረት እንዲያከናውኑ እናደርጋለን፤ እንዲሁም የቻይና ኢንተርፕራይዞችን ሕጋዊ መብቶች እና ጥቅሞች በጽኑ እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    "ሌሎች አገራትን በስህተት ከመኮነን እና ከመተቸት አንገብጋቢው እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ጦርነቱ ዳግም እንዳይጀመር መከላከል ነው” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዢ ጂንፒንግ ጋር ለመገናኘት በዚህ ሳምንት ወደ ቻይና ያመራሉ። ከግንቦት 5 እስከ 7 2018 ዓ.ም. የሚቆየው ይህ ጉብኝት በአስር ዓመታት ውስጥ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ቻይና የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉዞ ይሆናል ተብሏል፡፡

  2. ትራምፕ የኢራንን የሰላም ዕቅድ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ናፍጣ የሚቀዳ ሞተር ሳይክል

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለአሜሪካ የሰላም ዕቅድ የሰጠችውን ምላሽ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።

    ቴህራን ምላሹን የሰጠችው በአደራዳሪዋ ፓኪስታን በኩል ሲሆን ግጭቱ ወዲያውኑ እንዲቆም እንዲሁም ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ጥቃት እንደማይፈጸምባት ማረጋገጫ እንዲሰጣት መጠየቋን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ሰኞ ዕለት ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በእስያ ገበያ በበርሜል የ4.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 105.50 ዶላር ተሸጧል።

    የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ከየካቲት የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ ዝግ ሀኗል።

    ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል።

    የዓለም አንድ አምስተኛው ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ በኋላ ቴህራን ለማቋረጥ የሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም በመግለጽ አስጠንቅቃለች።

    ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት 21/ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ 26 የነዳጅ እና ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።

    መርከቦቹ ላይ ጥቃት የደረሰው በተወንጫፊዎች፣ በአነስተኛ ጀልባዎች፣ በቦምብ ሲሆን አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከኦማን የባሕር ዳርቻ ወጣ ባለ ስፍራ እንዲሁም የዩኤኢ ፉጃይራህ ወደብ አቅራቢያ ነው።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት በሆርሙዝ ወሽመጥ ከ1500 እስከ 2000 መርከቦች እንዲሁም 20 ሺህ ባህረተኞች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን አስታውቋል።

    ዋና ዋና የኢነርጂ ኩባንያዎች የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ትርፋቸው መጨመሩን ይፋ አድርገዋል።

    እሁድ ዕለት አራምኮ ባለፉት ሦስት ወራት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።

    ባለፈው ወር እንዲሁ ቢፒ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ትርፉ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የገለጸ ሲሆን ሼል ደግሞ ባለፈው ሳምንት ትርፉ ከፍ ማለቱን ተናግሯል።

  3. ኢራን በወሽመጡ ላይ የሚሰማሩ የፈረንሳይ እና የብሪታኒያ ባሕር ኃይሎችን አስጠነቀቀች

    ቴህራን የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚጓጓዝበትን መስመር አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከከፈቱባት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ዘግታዋለች።

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የፈረንሳይ ወይም የብሪታኒያ ባሕር ኃይሎች የሚሰማሩ ከሆነ “ወሳኝ እና ፈጣን ምላሽ” እንደምትሰጥ አስጠነቀቀች።

    የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማክሮን አገራቸው በወሽመጡ ላይ የባሕር ኃይሏን ለማሰማራት “ዕቅድ እንደሌላት” ገልጸው ነገር ግን “ከኢራን ጋር በመተባበር” የደህንነት ተልዕኮ የሚሰጠው ጦር እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ቅዳሜ ዕለት የብሪታኒያ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚኖርን የመርከቦች እንቅስቃሴ ለመከላከል የሚደረግ ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ላይ ለመሳተፍ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የጦር መርከቡን መላኩን አስታውቋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት በጋራ በመሆን ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ይጀመራል የተባለውን ይህንን ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ደግፈው ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለት ከ40 አገራት በላይ የሚውጣጡ የመከላከያ ሚኒስትሮች በዩኬ የበላይነት የሚመራውን እና በወሽመጡ ላይ የሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴን የመከላከል ዘመቻ ዕቅድ ላይ ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የዩኬው ኮን ሄይሊ እና የፈረንሳዩ አቻቸው ካትሪን ቫውትሪን በጋራ በመሆን ስብሰባውን የሚመሩ ሲሆን ጦርነቱ ከቆመ በኋላ በወሽመጡ ላይ የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቃሴዎችን እንዴት እንደሚጠብቁ ይመካከራሉ ተብሏል።

    ቴህራን የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚጓጓዝበትን መስመር አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከከፈቱባት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ዘግታዋለች።

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ ሞሐመድ አክራሚኒያ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ከቴህራን ጋር በቅድሚያ የማይተባበሩ ከሆነ “ከባድ እርምጃ” እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቃቸውን የኢርና የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አክራሚኒያ አክለውም አሜሪካኖች “ይህንን በሰሜን ሕንድ ውቅያኖስ የሚገኝ ሰፊ የባሕር ክፍል በጦር መርከቦቻቸው ቢሞሉት እንኳ ሙሉ በሙሉ መዝጋት አይችሉም" ሲሉ ተናግረዋል።

    አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው አገራት በኳታር፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ዩኤኢ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኦማን የጦር ሠፈሮች አሏት።

  4. ትራምፕ ኢራን ለሰላም ዕቅዱ የሰጠችውን ምላሽ ውድቅ አደረጉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ላቀረበችው ዕቅድ የሰጠችውን ምላሽ “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ውድቅ አደረጉ።

    በከፊል ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የቴህራን ምላሽ በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል መላኩን ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ የቴህራን ምላሽ ውስጥ በሁሉም ግንባሮች የሚካሄዱ ውግያዎች እንዲቆሙ፣ አሜሪካ የኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው እገዳ እንዲነሳ፣ እንዲሁም ወደፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ዋስትና እንዲሰጥ ይጠይቃል።

    ከሁለት ወር በላይ በዘለቀው የኢራን ጦርነት አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጦች ቢኖሩም በአብዛኛው የተኩስ አቁሙ እንደቀጠለ ነው።

    ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ ትራምፕ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት “በፍጥነት ይጠናቀቃል” ብለው ነበር።

    ነገር ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ ተጠናቅቋል ከማለታችን በፊት ኢራን ያከማቸችው የበለጸገ ዩራኒየም “መውጣት አለበት” ሲሉ ጠይቀዋል።

    ኔታንያሁ ሲቢኤስ ላይ በሚቀረበው ‘60 ሚኒትስ’ ለተሰኘ ፕሮግራም በሰጡት ቃለ ምልልስ “አሁንም ያልወደሙ የማበልጸጊያ ማዕከላት አሉ” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የሰላም ዕቅዱን በቀጥታ ሳይጠቅሱ “በጠላቶቻችን ፊት አንገታችንን አንደፋም። የንግግር ወይም የድርድር ሃሳብ ሲመጣ እጅ መስጠት ወይም ማፈግፈግ ማለት አይደለም” ብለዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “በተወካይ በኩል ቀረበ የተባለውን የኢራንን ምላሽ አነበብኩት፤ አልወደድኩትም። ምንም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ጽፈዋል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የሆነው አክሲዮስ ውስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ያቀረበችው ባለ 14 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ኢራን ኒውክሌር ማበልጸጓን እንድታቋረጥ፣ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገው ነጻ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚጠይቁ ሃሳቦችን የያዘ ነው።

    መገናኛ ብዙኃኑ በዘገባው ስለ ዕቅዱ ማብራሪያ የተሰጣቸውን ሁለት በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን እና ሁለት ሌሎች ግለሰቦችን ጠቅሷል።

    እንዚህ ምንጮች በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ ነጥቦች ለመጨረሻው ስምምነት መነሻ በመሆን ያገለግላሉ ብለዋል።

    ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍበትን የባሕር ወሽመጡን እንደዘጋች ነው።

    አሜሪካ በበኩሏ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦችን የከለከለች ሲሆን ይህም ቴህራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው።

    ትራምፕ እአአ ግንቦት 6 በትሩዝ ሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን በቀረበላት የሰላም ሃሳብ የማትስማማ ከሆነ ዳግመኛ የቦምብ ድብደባው እንደሚጀመር ጽፈው “ከዚህ በፊት ከታየው ሁሉ የከፋ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።