በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና የሕከምና ተቋማት እስራኤል ሐማስ ላይ በከፈተችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የተነሳ አጣብቂኝ
ውስጥ ወድቀዋል።
የበርካቶች ዋናው ትኩረት በትልቅነቱ ቀዳሚ በሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል ነው።
በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከ2ሺህ 300 በላይ ሰዎች በሆስፒታሉ አቅራብያ በሚካሄዱ ግጭቶች የተነሳ መላወስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሌሎች የሕክምና ተቋማት ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።
የኃይል አቅርቦት እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት በሆስፒታሎቹ ሕክምና ለማግኘት የሚጠባበቁ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎታል።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት
መረጃ ከሆነ በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ 22 ሆስፒታሎችን ጨምሮ፣ 36 የሕክምና ተቋማት ወድመዋል።
በጣት የሚቆጠሩት ብቻ
ናቸው በስራ ላይ ያሉት።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት
መግለጫ ከሆነ በጋዛ ከተማ የሚገኘው እና 700 አልጋዎች ያሉት ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ አገልግሎት መስጠት አቋርጧል።
ጤና ድርጅቱ አክሎም
በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን ሁኔታ “ አሰቃቂ እና አደገኛ” ሲል ጠርቶታል።
በሆስፒታሉ ዙርያ የሚገኙ
መንገዶች በሐማስ እና በእስራኤል ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች እየተናጡ ነው።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት
መረጃ ከሆነ ወሳኝ የሚባሉ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሞትን
አልያም ጉዳትን ሳይጋፈጡ ከሆስፒታሉ መውጣት የሚታሰብ አይደለም።
እንደ ፍልስጤም ቀይ ጨረቃ መረጃ ከሆነ በጋዛ ሰርጥ የሚገኘው
እና ከአል -ሺፋ በመቀጠል ሁለተኛ የሆነው አል-ቁድስ ሆስፒታል ስራውን አቋርጧል።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ
ቅዳሜ ዕለት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ከ500 ሕሙማን እና ከ14 ሺህ ተፈናቃዮች ጋር መላወሻ አጥተው ይገኛሉ።
ቅዳሜ ዕለት ሆስፒታሉ
በነዳጅ አቅርቦት አለመኖር እና የኤሌትሪክ ኃይል በመቋረጡ የተነሳ አገልግሎት መስጠት ማቋረጡ ይፋ ተደርጓል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች
ማህበር ቅዳሜ ዕለት፣ በሆስፒታሉ የሚሰራ እና ከእነ ቤተሰቡ የተጠለለ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን እና አሁን
ስላለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቆ ነበር።
በሰሜን ጋዛ ከተማ የሚገኙት
ለሕጻናት ሕክምና የሚሰጠው ራንቲሲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በአቅራብያው የሚገኘው አል-ናስር ሆስፒታል ያሏቸውን ሕሙማን እና ሠራተኞቻቸውን ለማትረፍ ለቅቀው እንዲወጡ የተደረገው አርብ ዕለት ነበር።
ራንቲሲ በጋዛ ከተማ
የሕጻናት ካንሰር ሕክምና የሚሰጥ ብቸኛው ተቋም ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት
የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ቅዳሜ ዕለት በምዕራብ ጋዛ የሚገኘው የስዊዲሽ ክሊኒክ “በአየር ድብደባ መመታቱን እና መውደሙን” ይፋ
አድርጓል።
በክሊኒኩ 500 ሰዎች
የተጠለሉ መሆናቸውን እና ስለደረሰው ጉዳት ይፋዊ መረጃ አለመኖሩንም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።