‘ሆስፒታሎች የጦር ሜዳዎች አይደሉም’ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን
የእስራኤል ወታደሮች ጋዛ ውስጥ ወደሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ መግባታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ተቃውሟቸውን አሰሙ።
“በጋዛው አል-ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ የተካሄደውን ወታደራዊ ወረራን በተመለከተ እየወጡ ባሉት ዘገባዎች አዝኛለሁ” ሲሉ ግሪፊትስ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ጨምረውም “የጨቅላ ሕጻናትን፣ የህሙማንን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን እንዲሁም የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅ ከምንም በላይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሆስፒታሎች የጦር ሜዳዎች አይደሉም” ብለዋል።
ቀደም ሲል እንደተዘገበው የእስራኤል ጦር ኃይል አባላት ወደ ሆስፒታሉ የገቡ ሲሆን፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ላገኗቸው ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ምርመራ እያካሄዱ ነው። በተጨማሪም በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ወንዶችን በአንድ ቦታ ላይ እያሰባሰቧቸው መሆኑ ተነግሯል።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት ሐማስ ከሆስፒታሉ ስር የዕዝ ማዕከል እንዳለው በመግለጽ ቢከስም ሐማስ ግን ይህንን ያስተባብላል።
ሠራዊቱ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት በአል-ሺፋ ሆስፒታሉ ውስጥ “የተመረጡ ዘመቻዎችን” እያከሄደ ነው።