የአዲስ መንግሥት ምስረታ በዓለ ሲመት በመስቀል አደባባይ

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ ዛሬ አዲስ መንግሥት ተመስርቷል። አዲሱ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራው ሲጀምር ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመሩትን ዐቢይ አሕመድን ሰይሟል። በመስቀል አደባባይ በተካሄደ በዓለ ሲመት ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የታደመ ሲሆን የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር አድርገዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

    ዐብይ አሕመድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመ።

    ምክር ቤቱ ሹመቱን ያጸደቀው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብልጽግና ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ዕጩ አድርጎ ካቀረባቸው በኋላ ነው።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፍተኛውን የሕግ አስፈጻሚ አካል ስልጣን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ይይዛሉ።

    በዚህ መሠረት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ መስተዳድር መሪ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይሆናሉ።

    ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ተግባራት መካከል የሚመርጧቸውን የሚኒስትሮች ምከር ቤት አባላትንና ሌሎች ላላፊዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው እንዲሾሙ ያደርጋሉ።

  2. ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚንሰትር እንዲሆኑ በፓርቲያቸው ታጩ

    ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲመሩ በፓርቲያቸው ዕጩ ሆነው ቀረቡ።

    በአገሪቱ ሕግ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብላጫ ድምጽ ያለው ፓርቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚጸድቅ ከሆነ፤ ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ይቀጥላሉ።

  3. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ታገሰ ጫፎን አፈ ጉባኤ አድርጎ ሾመ

    Tagese Chafo

    የፎቶው ባለመብት, PM office

    አቶ ታጋሰ ጫፎ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው በምክር ቤቱ ተሰይመዋል።

    አቶ ታገሰ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን አሁንም ለቀጣይ አምስት ዓመታት በቦታቸው እንዲቆዩ ምክር ቤቱ መርጧቸዋል።

    የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ስልጣንና ተግባር በተመለከተ፤ ምክር ቤቱ እረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የምክር ቤቱ አባላት ስብሰባ እንዲጠራ በሚጠይቁበት ጊዜ አፈ ጉባኤው ስብሰባ የመጥራት ኃላፊነት/ግዴታ አለበት።

    ይሁን እንጂ በአንቀጽ 66 ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባዔው የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት አሉት።

    •የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል

    •ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደደር ስራዎች ይመራል

    •ምክር ቤቱ በአባሎቹ ላይ የወሰነውን የዲሲፕሊን እርምጃ ያስፈጽማል

  4. የመንግሥት መስረታ ሥነ ሥርዓት መካሄድ ጀመረ

    ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, ETV

    አዲሶቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቃለ መሐላ ፈጽመው አዲስ መንግሥት የመመስረት ሥር ሥርዓት ተጀምሯል።

    የምክር ቤቱን አባላትን ቃለ መሐላ ያስፈጸሙት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ማዕዛ አሸናፊ ናቸው።

  5. የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ

    Abiy Ahmed

    የፎቶው ባለመብት, @PMAbiyAhmedAli

    የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሐማዱ ቡሃሪ በጠቅላይ ሚንስትሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል

    በመንግሥት ምስረታ ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

    የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሐማዱ ቡሃሪ እና የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል አዲስ አበባ ገብተዋል።

    መሪዎቹ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ መሪዎቹ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ደስ ብሎኛል ብለዋል።

  6. በመንግሥት ምስረታ ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም የተለያዩ አገራት መሪዎች ገብተዋል

    የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, PM Office

    በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ምስረታ ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም የተለያዩ አገራት መሪዎች እና ባለስልጣናት አዲስ አበባ ገብተዋል።

    ከእነዚህም መካከል

    - የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሀማዱ ቡሃሪ

    - የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል

    - የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዜዳንት ኦሌሴንጎ ኦቦሳንጆ

    - የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ አዲስ አበባ ገብተዋል።

  7. ዛሬ የሚጠበቁ ዋና ዋና ክስተቶች

    ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, HPR Facebook

    ረፋድ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምስረታና የመክፈቻ ጉባኤ ይካሄዳል።

    ለሁለቱም ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ይሰየማሉ።

    በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ።

    የምርጫ 2013 አሸናፊው የሆነው ብልፅግና ፓርቲ እጩ አድርጎ የሚያቀርባቸው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይሾማሉ።

    በብልጽግና ፓርቲ የሚቀርቡ ጠቅላይ ሚንሰትር ሹመትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሹመቱ የሚፀድቅላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በምክር ቤቱ ንግግር ያደርጋሉ።

    የሚሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን ያዋቅራሉ ፤ ይፋ ያደርጋሉ።

    በመስቀል አደባባይ ልዩ የመንግሥት ምስረታ እና የተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ ሲመት ስነስርዓት ይካሄዳል።

  8. አዲስ መንግሥት ለኢትዮጵያ

    ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY

    ዛሬ ሰኞ መስከረም 24/2014 ዓ.ም. በፌዴራል ደረጃ በሕዝብ የተመረጠው መንግሥት ይመሠረታል።

    አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስራቸውን ይጀመራሉ።

    ምክር ቤቱ አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራውን ግለሰብ ይሰይማል።

    በምክር ቤቱ የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትርም በሚኒስትርነት የሚያገለግሉ ዕጩዎችን ለምክር ቤቱ አቅርበው ያስሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  9. እንደምን አደራችሁ!

    የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የያዘ ወጣት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት ይመሠረታል።

    በዛሬው ዕለት በርካታ አበይት ጉዳዮች ይከናወናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    እኛም ከዚህ ከአሁን ጀምሮ ትኩስ መረጃዎችን በቀጥታ የዘገባ ገጻችን እናደርሳችኋለን።

    መልካም ቀን!