የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ባይደን እንደሚያሸንፉ ተነበዩ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ እስካሁን ባለው ከ99 ሚሊዮን አሜሪካውያን በላይ ቀድመው መምረጣቸው ተገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ንጋት 11 ሰዓት ላይ ያለው የምርጫ ውጤት

    US Election

    የአሜሪካ ምርጫ ውጤት ጥቅምት 25 ንጋት 11 ሰዓት ላይ

  2. ዕፀ-ፋርስ፣ ፅንስ ማቋረጥና ሌሎች መመሪያዎች የሚወሰኑባት እለት

    ዕፀ ፋርስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዘንድሮው ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ብቻ አይደሉም የሕዝብ ድምጽ የሚሰጣቸው።

    ሁለቱም ፓርቲዎች (ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት) የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫን በትኩረት የሚከታተሉት ሲሆን ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮችም የሕዝብ ድምጽ ያስፈልጋቸዋል።

    ለምሳሌ የዕጸ ፋርሰ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ነው።በአሪዞና፣ ሞንታና፣ ኒው ጀርሲ እና ሳውዝ ዳኮታ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለመዝናኛ መፈቀድ አለበት በሚለው ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።

    በተመሳሳይ በሚሲሲፒ ደግሞ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለሕክምና መፈቀድ አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ላይ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

    በኦሪጎን መራጮች እንደ ሄሮይን እና ኮኬይን ያሉ ጠንከር ያሉ እጾችን በትንሽ መጠን ለግል ጥቅም ማዋል ወንጀል መሆን አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።በኮሎራዶ ደግሞ 22 ሳምንት ያለፈውን ጽንስ ማቋረጥ ሕገወጥ ይሁን የሚል ሀሳብ የቀረበ ሲሆን መራጮች በዚህ ጉዳይ ላይም ድምፃቸውን ይሰጣሉ።

  3. ተቀናቃኞቹ ጆ ባይደንና ትራምፕ በምርጫው እለት ቀናቸውን እንዴት እያሳለፉት ነው?

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለተመራጮቹም ሆነ ለደጋፊዎቻቸው የምርጫ ዕለት ትንቅንቅ ያለባት ቀን ናት። የምርጫ ጣቢያዎች ሲዘጉ ደግሞ ጥበቃ ይጀመራል።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዛሬው ዕለት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በዋይት ሃውስ ነው። የተለያዩ ቃለ መጠይቆችን ከማድረግ በተጨማሪ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚሰጡትን ሽፋን ያያሉ።

    ትራምፕ ከሚወዱት የፎክስ ኤንድ ፍሬንድስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋርም ዛሬ ቀጠሮ እዘዋል።

    በባለፉት ሶስት ቀናት 14 ያህል የምረጡኝ ቅስቀሳ ያደረጉት ትራምፕ እረፍት በተሞላበት መልኩ ሊያሳልፉባት የሚችሉባት እለት ነው ተብሎ ተጠብቋል። ነገር ግን ያ እረፍታቸው አይቀጥልም ምሽት ላይ በዋይት ሃውስ ደመቅ ያለ ፓርቲም ያዘጋጃሉ።

    ትራምፕ ከቤተሰቦቻቸውና ከምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ ጋርም ሆነ ውጤቱን በጉጉት እንደሚጠብቁ ሳይታለም የተፈታ ነው።

    ጆ ባይደን በበኩላቸው የምርጫዋን እለት ቁልፍ በሆነችውና በርካቶችን ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ ባልተገመተባት የፔንስልቬንያ ግዛት በመጨረሻዋም ሰዓት ቢሆን የመራጮችን ድምፅ ለማግኘት ይሞክራሉ ተብሏል።

    የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት የልጅነት ጊዜያቸውን ባሰለፉባቸው ስክራንተንና ፊላደልፊያም አንዳንድ ቅስቀሳዎችንና ስብሰባዎችን እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

    በመጨረሻም ዴላዌር ወደሚገኘው ቤታቸው አቅንተው የምርጫውን ውጤት ይጠባበቃሉ።

    አመሻሹም ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቁ ሲሆን፤ በመድረኩም ላይ ባለቤታቸው ጂል ባይደን፣ ካማላ ሃሪስና ባለቤቷ ዳግላስ ኤምሆፍ ያጅቧቸዋል።

    ባይደን የሚያደርጉት ንግግር በምርጫው ውጤት የሚወሰን ይሆናል፤ ይህም በአሜሪካውያን መራጮች እጅ ማለት ነው።

  4. 'ሳኒታይዘር' የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ያበላሻል ተባለ

    ድምፁን እየሰጠ ያለ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ምርጫ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠላው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በርካቶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በሚያመሩበት በአሁኑ ወቅት ምርጫው ላይ በተለየ መንገድ ተፅእኖ ሊያደርስ ይችላል ተብሏል።

    የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማዕከል (ሲዲሲ) አልኮል ያለባቸው ፀረ ተህዋሲያን (ሳኒታይዘር) የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ያበላሻሉ ሲል አስጠንቅቋል።

    በፀረ-ተህዋሲያን የረጠቡ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በቀላሉ የመቀደድ ወይም ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ድምፅ መስጫ ማሽኖችን ይዘጋሉ ብሏል።

    በአገሪቱ የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ ሳኒታይዘሮች ማቅረብ አለባቸው የሚለው ሲዲሲ ነገር ግን መራጮች የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ከመነካካታቸው በፊት እጃቸው መድረቁን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥቷል።

    ከዚህ ቀደም በነኒው ሃምሻየር በነበረ የአካባቢ ምርጫ የረጠቡ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እክል ፈጥረው የነበረ ሲሆን ባለፈው ወርም እንዲሁ በካሊፎርኒያ፣ ሳክራመንቶ መራጮች የድምፅ መስጫ ወረቆቶቻቸውን በሳኒታይዘር በመርጨታቸው ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ተብሏል።

    ሳኒታይዘር የተረጨባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ቀለማቸው ለቅቆ ማንበብም ባለመቻሉ እንደገና እንዲርጡ ሆነዋል።

  5. አሜሪካን ለሁለት የከፈለው ምርጫ

    መራጮች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በአሜሪካ ታሪክ ዜጎችን እንዲህ ባለ መልኩ ለሁለት የከፈለ ምርጫ በቅርብ ዓመታት አልታየም በተባለለት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕና ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ተፋጠዋል።

    እስካሁን 100 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን በአሜሪካ ታሪክ ይህ ያክል ቁጥር ያለው ሰው በዚህ ፍጥነት ድምፁን ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነውም ተብሏል።

    ሁለቱም ተቀናቃⶉች ወሳኝ በሚባሉት ግዛቶች በመሄድ ለሰአታት የፈጀ ቆይታ አድርገዋል።

    እስካሁን ባለው አካሄድ ጆ ባይደን ዶናልድ ትራምፕን እየመሯቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የምርጫውን ውጤት ይወስናሉ በሚባሉት ግዛቶች ግን እስካሁን ሁለቱም ተቀራራቢ ድምጽ እንዳገኙ ተጠቁሟል።

    አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ብዙ ድምጽ ማግኘት ብቻ በቂ አይደለም። በኢሌክቶራል ኮሌጅ የምርጫ ሥርዓት መሠረት ሁለቱም ተፎካካሪዎች ካሉት 538 ድምጾች ቢያንስ 270 ለማግኘት ነው እየታገሉ ያሉት።

  6. ጆ ባይደን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን አቀኑ

    ጆ ባይደን ከቤተሰቦቻቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዲሞክራቱ እጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዴላዌር በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሄደው ነበር።

    ቤተ ክርስቲያኑ ለባይደን ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው ተብሏል፤ ምክንያቱም የመጀመሪያ ባለቤታቸውና ጨቅላ ህፃን ልጃቸው የተቀበሩ እዚህ ነው። ሁለቱም የሞቱት በጎሮጎሳውያኑ 1972 ባጋጠመ የመኪና አደጋ ነው።

    ከዚህም በተጨማሪ ከአምስት አመት በፊት በጭንቅላት ካንሰር ያጡት የ46 አመት ልጃቸው ቢውና ወላጆቻቸውም መካነ መቃብር በዚህ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል።

    ጆ ባይደን ከቤተሰቦቻቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  7. የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል እንደሚገባ የቀድሞ አቃቤያነ ህግ አስጠነቀቁ

    ሚካኤል ሙካሴና ኤሪክ ሆልደር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images/ Reuters

    የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል እንደሚገባ የአሜሪካ ሁለት የቀድሞ ጠቅላይ አቃቤያነ ህግ አስጠንቅቀዋል።

    ኤሪክ ሆልደር በዲሞክራቱ ባራክ ኦባማ አገዛዝ ወቅት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩ ሲሆን ሌላኛው ሚካኤል ሙካሴ በሪፐብሊካኑ ጆርጅ ቡሽ ዘመን ያገለገሉ ናቸው።

    በዋሽንግተን ፖስት ላይ በወጣ ፅሁፍ ከዚህ ቀደም ሁለቱም በአገሪቱ ህጎችና ፖሊሲዎች የተለያዩ ዕይታ እንዳላቸው ገልፀው ይሄም ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል።

    በጥምረትም በፃፉት ፅሁፍ ላይ የአገሪቱ ህገ መንግሥትም ሆነ አሜሪካውያን የተለያዩ እይታዎች ቢኖራቸውም የሚፈልጉት የፖለቲካ ውጤት ሊያዩ እንደሚገባ አስምረዋል።

    "ይህንን ማለት የማይገባን ቢሆንም መባል አለበት ብለን እናምናለን። የፖለቲካ መሪዎቻችን ወደ ግጭት የሚያመራ ነገር ሊያቀጣጥሉ አይገባም፤ሁከትንም ሊያበረታቱ አይገባም" ብለዋል።

    የህግ ባለሙያዎች እንደ ማስጠንቂያ ሊወሰድ ይገባል ብለው ባወጡትም ፅሁፍ "በዚህ ወቅት የአንደኛው አሸናፊ መሆን የመጨረሻ በአገሪቱ መጥፎ ነገር መስሎ ለሚታያቸው አካላት የምርጫውን ውጤት አልቀበልም በማለታቸው ምርጫ ትርጉም ሊያጣ የሚችልበትም አገር መኖርን አስቡት" ብለዋል።

  8. ቅድመ ምርጫውን ማን እየመራ ነው?

    ባይደን እና ትራምፕ

    ነገ አሜሪካውያን ቀጣይ መሪያቸውን የሚመርጡበት ወሳኝ ቀን።

    ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ? ወይስ ይቀጥላሉ? የሚለው የሚለይበት ቀን።

    ማን ይረታ ይሆን?

    ነገር ግን የአሜሪካ የምርጫ ትንቅንቅ የምርጫ ዕለት ብቻ የሚታይ አይደለም። የቅድመ ምርጫ ምርጫም አለው። ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅቶች የትኛውን ዕጩ ነው የምትመርጡት እያሉ ከአሜሪካውያን የሚሰበስቡትን ድምፅ ይፋ የሚያደርጉበት ነው ቅድመ ምርጫ ማለት።

    እና በዚህ ቅድመ ምርጫ ማን እየመራ ነው? ትራምፕ ወይስ ባይደን?

  9. ትራምፕ እና ባይደን በምጣኔ ኃብት እና ጤና ላይ ያላቸው የፖሊሲ ልዩነት

    ባይደን እና ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን በምጣኔ ሃብት እና በጤና ላይ ያላቸው የፖሊሲ ልዩነት ምንድነው?

    በምጣኔ ሃብት ጉዳይ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- በ10 ወራት 10 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ቃል ገብተዋል። 1 ሚሊዮን አነስተኛና ጥቃቅን ሥራ እፈጥራለሁ ብለዋል። የግብር እፎይታ ለትልልቅ ኩባንያዎች በመስጠት ሥራ ፈጠራ እንዲፋፋም አደርጋለሁ ይላሉ።

    ጆ ባይደን፡-ትልልቅ ኩባንያዎች ላይ ግብር በመጫን ሕዝቡን የሚጠቅሙ ልማቶች ላይ አተኩራለሁ ይላሉ። ነገር ግን ግብር የምጭነው ገቢያቸው በዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር በሚያገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ብቻ ነው ብለዋል።

    በቀን ዜጎች የሚያገኙት ዝቅተኛ ገቢ በሰዓት 15 ዶላር እንዲሆን አደርጋለሁ ብለዋል። አሁን ያለው ትንሹ በሰዓት የሚከፈለው 7.25 ዶላር ነው።

    በኅብረተሰብ ጤና ጉዳይ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- የኦባማ የጤና መድኅን ጨርሶ ለማጥፋት ይፈልጋሉ። በዚህ ‹አፎርደብል ኬር አክት› በሚባለው አዋጅ መሰረት የፌዴራል መንግሥት የግል የጤና መድኅን ሰጪዎችን ይቆጣጠራል። መድኅን ሰጪዎች ቀደም ብሎ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎችን መድኅን ሲጠይቁ የሕክምና ወጪ አልሸፍንም ማለት አይችሉም።

    ትራምፕ ግን ይህንን ረብ የለሽ ኦባማ ኬር ቀዳድጄ በሌላ ጥዬ በሌላ እተከዋለሁ እያሉ ይዝታሉ። የመድኃኒት ዋጋ አሁን ካለበት እንዲወርድ አደርጋለሁ፤ በርካሽ ከሌሎች አገሮች መድኃኒት እንዲገባም እፈቅዳለሁ ብለዋል።

    ጆ ባይደን፡- የኦባማ የጤና ሽፋን መድኅንን አስጠብቃለሁ ይላሉ። በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያገኙትን የጤና ትሩፋቶችን አስፋፋለሁ፤ ለዚህ ትሩፋት የሚያበቃውን ዕድሜም ከ65 ወደ 60 አወርደዋለሁ ብለዋል። ሁሉም አሜሪካዊያን የኅብረተሰብ ጤና መድኅን የመመዝገብ ምርጫ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።

  10. ትዊተር የዶናልድ ትራምፕን መልዕክት ደበቀ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫው ሰአታት በፊት በትዊተር ገጻቸው ምርጫውን በተመለከተ ያሰፈሩትን መልእክት ትዊተር ደብቆታል።

    ትራምፕ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፔንሲልቬኒያ በርካታ የሰዎች ድምጽን በፖስታ በኩል እንዲመጣ መወሰኑ 'በጣም አደገኛ ነው'' በሚል ነበር በትዊተራቸው ላይ የጻፉት።

    ትዊተር የፕሬዝዳንቱን መልዕክት ከደበቀው በኋላ ጽሁፉ ''የሚያከራክርና አሳሳች ሊሆን የሚችል ነው'' የሚል ማስጠንቀቂያ አስቀምጦበታል።

    ትዊተር ከዚህ በፊትም በፕሬዝዳንቱ የትዊተር አካውንት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ አይረሳም።

    ዶናልድ ትራምፕ አክለውም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ''በአደባባይ አመጽ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል፤ የሆን ነገር መደረግ አለበት'' ሲሉም ጽፈዋል።

    ፌስቡክ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ያስተላለፉትን መልዕክት አላጠፋውም። ነገር ግን በአሜሪካ ታሪክ በአካል ሄዶ መምረጥም ሆነ በፖስታ መምረጥ ልዩነት እንደሌለውና ሁለቱም ታማኝ መሆናቸውን ገልጿል።አክሎም በሁሉም አማራጮች ድምጽ መጭበርበር ብዙም እድል እንደሌለው አስታውቋል።

  11. ምርጫ በወረርሽኝ ወቅት- 100 ሚሊዮን ያህል አሜሪካውያን ቀድመው መርጠዋል

    ጭምብል ያጠለቀች ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ እስካሁን ባለው ከ99 ሚሊዮን አሜሪካውያን በላይ ቀድመው መምረጣቸው ተገልጿል።

    ከአሜሪካ የምርጫ ፕሮጀክት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ ቁጥር በአካል እንዲሁም በፖስታ የመረጡትን ያካተተ ነው።

    ቁጥሩም ከአራት አመት በፊት ከነበረው ምርጫ ብልጫ ያሳየ ሲሆን በወቅቱም በአጠቃላይ የመረጡ ሰዎች ቁጥር 138 ሚሊዮን ነው።

    የምርጫ ታዛቢዎች እስካሁን ያለውን የመራጭ ቁጥርም በማጤን በዚህ አመት ከፍተኛ የሚባል የመራጭ ድምፅ ሊመዘገብ እንደሚችል እምነቱ አላቸው።

    ቀድመው የመረጡ ሰዎች ቁጥር እንዲህ በከፍተኛ ሁኔታም የጨመረው በተወሰነ መልኩ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል።

    በርካቶች በወረርሽኙ ምክንያት የምርጫ ጣቢያዎች ሄደው ለመምረጥ በመስጋታቸው ቀድመው ድምፃቸውን ሰጥተዋል ተብሏል።

    በዚህ አመት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ከአገሪቱ ህዝብ ለመራጭነት ብቁ ከሆኑት መካከል 60 በመቶ አካባቢ መርጠዋል ተብሏል፤ ይህ አሃዝ ከአራት አመት በፊት 58.1 በመቶ ነበር ተብሏል።

    በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀድመው ከመረጡት መካከል የካሊፎርኒያ ግዛት በ12 ሚሊዮን መራጮች የቀዳሚነት ቦታውን የያዘች ስትሆን በመቀጠልም ቴክሳስ 9.7 ሚሊዮን፣ ፍሎሪዳ 8.9 ሚሊዮን ይከተላሉ።

    ከምርጫ ጣቢያዎች በተገኘው መረጃ መሰረት ከሪፐብሊካኖች በበለጠ ዲሞክራቶች በፖስታ ድምፃቸውን መስጠት የሚመርጡ ሲሆን ይህም ለዲሞክራቱ ጆ ባይደን የበለጠ ይጠቅማቸዋልም እየተባለ ነው።

  12. ጆ ባይደን ማን ናቸው?

    ጆ ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ጉምቱ ፖለቲካኛ ናቸው።

    የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።

    ደጋፊዎቻቸው ባይደን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አዋቂ ናቸው ይሏቸዋል። በእርጋታቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ በግል ሕይወታቸው አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፈዋል።

    ሙሉ ዘገባ »»» ጆ ባይደን ማን ናቸው?

  13. በአሜሪካ ፕሬዘዳንት የሚመረጠው እንዴት ነው?

    መራጭ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፕሬዝደንት ሆኖ ይመረጣል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከ100 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች 60 ሚሊዮን ያገኘ እጩ ፕሬዝደንት ሆኖ የማይመረጥበት አጋጣሚ ይኖራል።

    ለምሳሌ እአአ 2016 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ፤ ሂላሪ ክሊንተን ከትራምፕ በበለጠ በርካታ ድምጽ አግኝተው ነበር። ይህ ግን የአሜሪካ ፕሬዝደንት አላደረጋቸውም።

    ለዚህ ምክንያቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የሚመረጠው ቀጥታ በመራጮች ሳይሆን በኤሌክቶራል ኮሌጅ ስለሆነ ነው።

    "ኤሌክቶራል ኮሌጅ" ምንድነው? ዝርዘሩን ይመልከቱ።

  14. ትራምፕ እና ባይደን የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻቸውን አካሄዱ

    ትራምፕ በሰሜን ካሮላይና በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በሰሜን ካሮላይና በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

    ፕሬዝደንት ትራምፕ እና ጆ ባይደን የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻቸውን ቁልፍ በሚባሉ ግዛቶች አከናውነዋል።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ዊስኮንስን፣ ሚሺጋን፣ ሰሜን ካሮላይና እና ፔንስልቫኒያ የመጨረሻ ዘመቻ ያደረጉባቸው ግዛቶቸች ናቸው።

    ጆ ባይደን በኦሃዮ ግዛት በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጆ ባይደን በኦሃዮ ግዛት በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

    ዲሞክራቱ እጩ ጆ ባይደን በበኩላቸው በፔንስልቫኒያ እና ኦሃዮ የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻ አከናውነዋል።

    ከምርጫ በፊት የተሰበሰቡት የሕዝብ አስተያየቶች ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ምርጫውን እየመሩ እንደሆነ የሚጠቁም ናቸው።

    ይህ ግን የምርጫውን ውጤት እንደማያሳይ ተጠቁሟል።

  15. ትራምፕ እና ባይደን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው አቋም ምድነው?

    ባይደን እና ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- የአየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር የለም፤ ቅጥፈት ነው ይላሉ። ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል አቅርቦትን ማስፋፋት ይሻሉ። ነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እንዲቀጥል፣ እንዲጧጧፍ ያበረታታሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በሚል የሚወጣ ወጪ እንዲቆም ያደርጋሉ። ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ወጥተዋል።

    ጆ ባይደን፡- ነጩ ቤተ መንግሥት እንደገቡ ወዲያውኑ ወደ ፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መልሰው ለመግባት ይሻሉ። አሜሪካ በ2050 ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ እንድትደርስ ይሰራሉ። 2 ትሪሊዮን ዶላር በአረንጓዴ ታዳሽ ኃይል ያወጣሉ። የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እንዲቆም ያደርጋሉ።

  16. ነገ ጠዋት ምን ዜና ልንሰማ እንችላለን?

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በስተመጨረሻም እንዳይደርሱት የለ ጊዜው ደርሷል። የመጨረሻው መጨረሻ። በጉጉት የተጠበቀው የአሜሪካ ምርጫ ቁርጡ ሊለይለት ነው።

    የዘንድሮው ምርጫ እንደሌሎቹ ጊዜዎች አይደለም። ግራ አጋቢ ዜናዎች የተሰሙበት፣ የሚጠብቁት ቀርቶ የማይጠብቁት የሚሆንበት ነው የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ።

    ታድያ ነገ ጥዋት ስንነሳ ምን ዓይነት ዜና ይጠብቀን ይሆን?

  17. የአሜሪካ ምርጫ 2020 በቀጥታ ገጻችን ላይ ይከታተሉ

    ድምጽ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አረፈዳችሁ?

    ቢቢሲ አማርኛ ከአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጋር የተያያዙ አሁናዊ መረጃዎችን በቀጥታ የዘገባ ገጹ ያደርሳችኋል። አብረን እንቆይ።

    መልካም ቀን!