በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን አልፏል። ከ 500 ሺህ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ነው።
ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃፀር ደቡብ አፍሪካ በተሻለ በኮቪድ-19 በቂ መረጃ አደራጅታለች በሚል ትሞገሳለች።
በአገሪቱም ትልቅ የተባለ የምርመራ ዘመቻ እያካሄደች ነው።
ግን አሁን ጥያቄ የሆነው በሌሎች የአፍሪካ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 500 ሺህ ብቻ ነው የሚለው ነው።
ባለሙያዎች ለዚህ መልሳቸው አጭርና ግልፅ ነው። አይደለም የሚል።
የሕክምና እና የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች አህጉሪቱ ያለውን አነስኛ ምርመራ የማድረግ ብቃት በማንሳት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን እንደሚልቅ ይናገራሉ።
ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች አክለው ሆስፒታሎች በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሕሙማን አለመጨናነቃቸውን በማንሳት የጉዳዩን አሳሳቢነት ይገልፃሉ።
ለዚህ ደግሞ በርካታ መላ ምት ይሰጣል። ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ፍርሃት፣ በበርካታ አገራት አስቀድሞ የተጀመረ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመላምቶቹ መካከል ናቸው።
እንደ ታንዛንያ ያሉ አገራት ደግሞ በአገራቸው ያለውን የኮቪድ-19 ስርጭት መጠን የሚገልጽ ምንም ዓይነት መረጃ ባለመስጠት የመከላከል ስራውን ፈታኝ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በአህጉሪቱ በአጠቃላይ 22 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ሲያጡ 690 ሺህ ያህሉ ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገግመዋል።
በአፍሪካ እስካሁን ድረስ ስምንት ሚሊዮን ያህል የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ብቻ የተደረጉ ሲሆን፤ ነገር ግን 13 ሚሊዮን ያህል መካሄድ ነበረበት ሲሉ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ኃላፊ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 የተያዘው ሰው የተገኘው በግብጽ የካቲት ወር ላይ ሲሆን ይህም በአውሮፓ ከተገኘ ሶስት ሳምንታት በኋላ ነበር።
በደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ በርካታ ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ፣ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጣር በቅርበት በአህጉሪቱ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት እየተከታተለ ያለው ደግሞ የናይጄሪያ፣ ጋና ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዛምብያ እና ዚምባብዌን የስርጭት መጠን በማየት መሆኑን ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።