በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ ተጠጋ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማሕበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በመቶዎች ይገኝ የነበረው ወደ ሺህ ተሻግሯል። በትናንትናው ዕለትም ከፍተኛ የተባለው 1ሺህ 652 እንዲሁም በዛሬው ዕለት 982 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩ ወደ 30 ሺህ ተጠግቷል። አገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 528 አድርሶታል። በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 359 መድረሱን የጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ አመላክቷል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ609 ሺህ 463ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ አከናውናለች። ሳይዘናጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሳችንንና ሌሎችን ከበሽታው እንጠብቅ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. “የአገራችን እድገት እንዲስተጓጎል ምክንያት አንሁን” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛን ለማስተዋወቅ በጀመረው ዘመቻ ኢትዮጵያ “ማስክ ኢትዮጵያ” በሚል መቀላቀሏን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው አስፍረዋል።

    “በዚህ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ዘመቻ የሁላችንም ተሳትፎ ጨምሮ፣ እውቀታችን አድጎ፣ ባህሪያችንም ተለውጦ፣ ወረርሽኙን በተሻለ አቅም መከላከል እንችላለን ብዬ አምናለሁ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ሁሉም ሰው ጭምብልን በትክክልበማድረግ፣ ሁልጊዜም በመጠቀም ከራሳችን አልፎ ወገኖቻችንም ከበሽታ እንጠብቅ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

    “አንድም ሰው በበሽታ እንዲያዝ፣ የማይተካ ሕይወት እንዲያልፍ፣ የአገራችን እድገት እንዲስተጓጎል ምክንያት አንሁን” ብለዋልፕሬዝዳንቷ።

    አክለውም “የሁላችንም ያልተቋረጠና የተባበረ ጥረት ወረርሽኙን ለማሸነፍ ይሁን”

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ውጤታማ ከሆኑት መከላከያዎች መካከል አካላዊ ርቀት መጠበቅና ጭምብል ማጥለቅ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ቆይቷል።

  2. በፍሎሪዳ የምትገኝ ከተማ የፖሊስ ኃላፊ ጭምብል ማድረግ ከለከሉ

    በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ አንድ የፖሊስ ኃላፊ በሥራቸው የሚገኙ ሁሉም የፖሊስ አባላት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዳያደርጉ መከልከላቸው ተሰምቷል።

    የማሪዮን ካውንቲ የፖሊስ ኃላፊው ቢሊ ዉድስ በተጨማሪም ሰዎች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲመጡ ማስክ ማድረግ እንደማይችሉ ገልጸዋል።

    አንድ የሕግ አስከባሪ ኃላፊ እንዲህ አይነት ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ በአሜሪካ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

    ኃላፊው ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ፖሊሶች ትዕዛዝ ሲሰጡ በትክክል እንዲሰሟቸውና ወደ ፖሊስ ጣቢያው የሚመጡ ሰዎችም ማንነታቸው እንዲታወቅ ነው ብለዋል።

    በፍሎሪዳ እስካሁን 550 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአሜሪካ ግዛቶች በበሽታው ክፉኛ የተመታች ያደርጋታል።

    እስካሁን በአጠቃላይ ደግሞ 8700 ሞት ተመዝግቧል።

  3. የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ አንቲቦዲ ምርመራ ሊጀምሩ ነው

  4. ቫይረሱን መቆጣጠር ፈተና የሆነባቸው የአውሮፓ አገራት

    በፈረንሳይ እየጨመረ የመጣው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ያሳሰባት ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ግዛቷ የሚገቡ ሰዎች ለ14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ የሚያስገድደውን ሕግ እንድታጠናክረው አድርጓታል።

    ልክ ዛሬ ጠዋት የፈረንሳይ ባለስልጣናት ዋና ከተማዋ ፓሪስና 'ቡሼ ዱ ሮን' የሚባለው ክልል ለኮቪድ-19 ከፍተኛ ተጋላጭ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል።

    ኦስትሪያ ደግሞ የለይቶ ማቆያ ሕጎችን የሚጥሱ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እወስዳለው ብላለች። አንዲት የ54 ዓመት ጀርመናዊትም በቫይረሱ መያዛቸው ከተነገራቸው ወዲህ ሕጉን በመጣሳቸው 10 ሺ 800 ዩሮ ወይንም ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

    ሴትዮዋ በቤታቸው ሆነው እራሳቸውን መለየት ሲገባቸው ሸርሸር ለማለት ወደ ፓርክ ሄደዋል፣ አስቤዛ ለመግዛት ተንቀሳቅሰዋል እንዲሁም ታክሲ ተጠቅመዋል በሚል ነው ቅጣቱ የተወሰነባቸው።

    ስፔን ደግሞ ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ ከፍተኛ የተባለው በቀን የሚያዙ ሰዎች እያስመዘገበች ነው። በቀን እስከ 2935 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እያገኘች ነው።

    ማድሪድ ደግሞ ከሁሉም ከተሞች በይበልጥ በቫይረሱ መጠቃቷ ተገልጿል።

    የጣልያኑ ከፍተኛ ተመራማሪ አውጉስቲኖ ሚዮዞ በበኩላቸው የምሽት መዝናኛ ቤቶች ይከፈቱ የሚለውን ሀሳብ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል። የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቁጥጥር ስር ማዋል ግን ይቻላል ሲሉም ተደምጠዋል።

    ዴንማርክ በያዝነው 2020 የፈረንጆቹ ዓመት የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳጋጠማት አስታውቃለች። በሩብ ዓመቱ የኢኮኖሚ ግምገማም አገሪቱ አይታው የማታውቀው 7.4 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቧል።

  5. የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት ፖለቲካዊ ጦርነት ያጋጥም ይሆን?

  6. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨማረ ነው

    በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መግባቱ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እያደገ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ፍጥነቱ ጨምሯል። በትናንትናው ዕለት ሐሙስም በአንድ ቀን ብቻ ከ1000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል።

    ይህ የተመዘገበው ቁጥር 1,086 እስከ ዛሬ ድረስ ከተመዘገቡት ቁጥሮች ሁሉ ከፍተኛው ሲሆን፤ አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙትንም 26 204 አድርሷቸዋል።

    ይህ ብቻም ሳይሆን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት ከፍ እያለ መሄዱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት መጋቢት ወር አካባቢ በአንድ አሃዝ ይመዘገብ የነበረው የሟች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት አሃዝ ተሸጋግሯል። አጠቃላይ የሟቾችም ቁጥር 479 ደርሷል።

    ዛሬም ትልልቅ ከተሞች የቫይረሱ ስርጭት በስፋት የሚታይባቸው መሆናቸው እየተገለፀ ሲሆን በአዲስ አበባ በትናንትናው ዕለት ብቻ 601 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ የ14 ሰዎች ሕይወትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማለፉን በከተማ አስተዳደሩ የኮሮናቫይረስ ዕለታዊ መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

    ዘወትር የሕክምና ባለሙያዎች በኅብረተሰቡ መካከል የሚታየው መዘናጋት ለስርጭቱ መስፋፋት አብይ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በማንሳት ይናገራሉ። አክለውም የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶች ላይ የሚታየው ቸልተኝነት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ይገልፃሉ።

  7. ''መድሀኒት አግኝቻለሁ'' የምትለው ማደጋስካር ቫይረሱን መቆጣጠር ለምን አቃታት?

    የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት አንድሬ ራሆሊና ምንም እንኳ ኮሮናቫይረስን የሚያድን መድሀኒት ተገኝቷል፤ ተጠቀሙት እያሉ ቢሆንም በማደጋስካር የሚገኙ ሆስፒታሎች እየጨመረ የመጣውን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቋቋም አቅቷቸዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ከእጽዋት የተሰራው 'መድሀኒት' ፈዋሽነቱ እና ደህንነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሰዎች እንዳይጠቀሙት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

    በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው ደሴቲቷ አገር ማደጋስካር ባለፈው ወር ብቻ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ የጨመረ ሲሆን፣ እስካሁን 13 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። 162 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንዳጡ የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል።

    የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ፕሬዝዳንቱ ግን ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ይፋ የተደረገውና 'ኮቪድ- ኦርጋኒክስ' ተብሎ የሚጠራውን የእጽዋት መድሃኒት ማሞካሸታቸውን ቀጥለዋል።

    በማደጋስካር የተግባራዊ ሳይንስ ምርምር ኢንስቲትዩት 'አርትሚዝያ' ተብሎ ከሚጠራው ተክል የተሰራው 'መድሀኒት' በፈሳሽ መልክ የሚወሰድ ነው። ለመድሃኒቱ በዋነኛነት እንደ ግብአት የሚጠቅመው ተክል ደግሞ የወባ በሽታን ለማከም በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላል።

  8. በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 1086 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 ተገኘ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በተካሄደ 14 ሺህ 688 የናሙና ምርመራ 1086 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱ ተገለጸ።

    የጤና ሚንስትር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 26 ሺህ 204 ደርሰዋል።

    ተጨማሪ 16 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ እስካሁን የሞቱ ሰዎች 479 ደርሰዋል።

    ዛሬ 394 ተጨማሪ ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች አጠላይ ቁጥርን 11 ሺህ 428 ደርሷል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን 550 ሺህ 119 የናሙና ምርመራ ተደርጓል።

  9. በአሜሪካ በአንድ ቀን 1,500 ሰዎች ሞቱ

    አሜሪካ- በአንድ ቀን 1,500 ሰዎች በኮቪድ-19 የሞቱ ሲሆን፤ ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው። በአገሪቱ ቢያንስ 166,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ኢንግላንድ- መምህራን ከገመቱት በላይ 36 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት አምጥተዋል። በወረርሽኙ ሳቢያ የፈተና ውጤት በተሰረዘባቸው አካባቢዎች ሦስት በመቶ የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ ሆኗል።

    ሕንድ- ከ47 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል። በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አራተኛ ሆናለች።

    ኒው ዚላንድ- 14 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ትልቁ ከተማ ኦክላንድ ውስጥ እንቅስቃሴ ተገድቧል።

    ስፔን- ጋሊሲያ የተባለች ግዛት የኮቪድ-19 ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ ማጨስ ከልክላለች።

  10. በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ750 ሺህ አለፈ

    በመላው ዓለም በኮቪድ-19 ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ750 ሺህ ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል።

    ወረርሽኙ በቻይና ከተገኘ ዘጠኝ ወራት ተቆጥረዋል። ባለፉት 17 ቀናት ብቻ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

    ከሞቱት ሰዎች ግማሹ የሚኖሩት በአራት አገራት ሲሆን፤ በአሜሪካ 166,083፣ በብራዚል 104,201፣ በሜክሲኮ 54,666 እና በሕንድ 47,033 ሰዎች ሞተዋል።

    አሁን ላይ በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳችው ላቲን አሜሪካ ናት። 228,000 ሰዎችሞተዋል።

  11. በደሴ ማረሚያ ቤት 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

  12. በደሴ ማረሚያ ቤት 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

    በደሴ ማረሚያ ቤት በተደረገ የኮቪድ-19 ምርመራ 13 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ማረጋገጡን የከተማው ጤና መምሪያ አስታወቀ።

    የመምሪያው ኃላፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር በተለይ ለቢቢሲ እንዳስታወቁት 12ቱ የህግ ታራሚዎች ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ የማረሚያ ቤቱ ባልደረባ ናቸው።

    እንደ አቶ አብዱልሃሚድ ገለጻ ከሆነ ከማረሚያ ቤቱ ጋር በመነጋገርም አዲስ የሚገቡ ታራሚዎች ለ14 ቀናት ለብቻቸው እንዲቆዩ ከማድረግ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ምርመራ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

    ከሐምሌ 20 በኋላ ማረሚያ ቤቱ የገቡ 46 ታራሚዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 10 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል።

    “ታራሚዎቹ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ናቸው። ከተለያዩ ከደቡብ ወሎ ወረዳዎች እና ከደሴ ከተማም የተገኙ ናቸው” ብለዋል።

    በሁለተኛ ዙር 60 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ሦስቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    በሁለተኛው ዙር ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል በመጀመሪያው ዙር እንዳለባቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው እና አንድ ማረሚያ ቤቱ ባልደረባ ይገኙበታል።

    የማረሚያ ቤቱን የሕግ ታራሚዎች እና ባልደረባዎችን በሙሉ ለመመርመር መቻሉንም አቶ አብዱልሃሚድ አስታውቀዋል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸው ቦሩ ሜዳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተላኩ ሲሆን፤ ተጓዳኝ ህመም ያለበት አንድ ታራሚ ካሳየው የህመም ምልክት ውጭ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

    በማረሚያ ቤቱ የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ አዲስ የሚገቡትን እና ነባር ታራሚዎችን ከመመርመር ባለፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ የኬሚካል ርጭት፣ ርቀትን ማስጠበቅ እና ንጽህና የማስጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

    ባለፉት ወራት በአማራ ክልል በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ 83 አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በክልሉ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካካል 23 የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገኙበትም ከአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

  13. ውሾች ኮቪድ-19ን አነፍንፈው መለየት ይችላሉ?

    በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ዱርሃም ዩኒቨርስቲ ውሾች ኮሮናቫይረስን ማሽተት ይችላሉ አይችሉም የሚለውን ለመፈተሽ ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ አቀረበ።

    ተመራማሪዎች በእንግሊዝ መለስተኛ የኮቪድ-19 ምልክት ያለባቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምርመራ ለማድረግ ወይንም ባለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ ያደረጉትን ለመመልመል ይፈልጋሉ።

    በጎ ፈቃደኞቹ በትንፋሻቸው እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለሶስት ሰዓት በማድረግ፣ ከናይለን የተሰራ ካልሲ እንዲሁም ቲ ሸርት ለ12 ሰዓት በማድረግ የአካላቸውን ጠረን ናሙና የሚሰጡ ይሆናል።

    ጥናቱ የሚደረገው በዱርሃም ዩኒቨርስቲና በለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂንስ እና ትሮፒካል ሜዲስን እንዲሁም በሕክምና ተግባራት ላይ በሚሰማሩ ውሾች ትብብር ነው።

    ምርምሩ ውጤታማ ከሆነ ውሾቹ በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በመሰማራት በሰዓት እስከ 250 ሰዎች ድረስ አሽትተው መለየት ይችላሉ ተብሏል።

  14. በስፔን አንድ ግዛት ሕዝብ በሚሰበሰብበት ስፍራ ሲጃራ ማጤስ ታገደ

  15. ሂዩማን ራይትስ ዎች፡ የየመን ታጣቂዎች ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ገድለዋል

  16. ከብራዚል ታሽገው የመጡ የዶሮ ክንፎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ቻይና አስታወቀች

    በደቡባዊ ቻይና የሸንዘን ከተማ ባለስልጣናት ቀዝቅዘውና ታሽገው ከብራዚል የመጡ የዶሮ ክንፎች ላይ ባደረጉት ምርመራ የኮሮናቫይረስ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

    የዶሮ ክንፎዎቹ የተመረመሩት በአካባቢው የጤና ባለስልጣናት ሲሆን ይህም ከውጭ ለሚገቡ ማንኛውም ምርቶች በሚደረገው አሰራር መሰረት ነው።

    ከምግቡ ጋር ድንገተኛ ንክኪ ይኖራቸዋል የተባሉ ግለሰቦችን እንዲሁም ከዶሮ ክንፎቹ ምርቶች አቅራቢያ የነበሩትንም ምርቶች ቢመረምሩም ነፃ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

    ከአንድ ቀን በፊት እንዲሁም በምስራቃዊቷ ግዛት ውሁ ቀዝቅዞ በመጣ የሽሪምፕ ማሸጊያዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱን የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል። የሽሪምፑ ምርት ከኢኳዶር የገባ እንደሆነ ዘገባው አስነብቧል።

    የተለያዩ የምግብ ምርቶች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ አዲስ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።

    የሸንዘን የጤና ኃላፊዎች ከውጭ በሚገቡ የስጋና የባህር ምግቦች በቫይረሱ ተጠቅተው ስለሚሆን ህዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

    ከዚህ ቀደምም በውሃን ከተማ በባህር ምግቦች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ይታወሳል።

  17. ''የእንግሊዝ 6 በመቶ ህዝብ በቫይረሱ ተይዟል'' አዲስ ጥናት

    በግምት እስከ 3.4 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ማለትም ከአጠቃላይ የእንግሊዝ ህዝብ 6 በመቶዎቹ ባለፈው ወር አጋማሽ ድረስ በኮሮረናቫይረስ መያዛቸውን አንድ ጥናት ጠቆመ።

    ቁጥሩ ከዚህ በፊት ተገምቶ ከነበረው በእጅጉ ከፍ ያለ እንደሆነም ተገልጿል። በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት በአጠቃላይ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 315 ሺ ደርሷል።

    ጥናቱ ያካሄደው 'ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን' መረጃውን ያገኘሁት ከ100 ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በመጠቀምና ብዙ ቦታ የሸፈነ የቤት ለቤት ምርመራ በማድረግ ነው ብሏል።

    ጥናቱን ካካሄዱት መካከል የሆኑት ፕሮፌሰር ግራሀም ኩክ እንደተናገሩት እስካሁን እየተመዘገበ ያለው የሞት መጠን ለምን ከፍተኛ እንደሆነ አሁን ማወቅ ይቻላል።

    '' የእንቅስቃሴ ገደቡ በተገቢ መልኩ ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ይችላል'' ብለዋል።

  18. የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት አማካሪ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተናገሩ

    የቬንዙዌላው ፕሬዚዳትን ኒኮላስ ማዱሮ የቅርብ አማካሪና ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተናግረዋል።

    የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት ጆርጅ ሮድሪገዝ ምንም እንኳን ውጤታቸው በቫይረሱ መያዛቸውን ቢያሳይም ምንም ህመም እንደማይሰማቸው አስታውቀዋል። ሆኖም ግን ራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ ገልጸዋል።

    "ጤንነቴ እንደ ቀድሞው ቢሆንም ህመም ባይሰማኝም፤ የአገሪቱን መመሪያ በማክበር ራሴን ለይቼ አቆያለሁ" ብለዋል።

    ሚኒስትሩ በቬንዙዌላ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ የመጀመሪያ ባለስልጣን ናቸውም ተብሏል።

    በላቲን አሜሪካ ካሉ አገራት ጋር ስትነፃፀር በቬንዙዌላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። እስካሁንም ባለው መረጃ 29 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 247 ዜጎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

  19. ወረርሽኙ በተስፋፋባት ሕንድ ሚኒስትሮች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተነገረ

    ሽሪፓድ ናይክ የተባሉት የሕንድ ሚኒስትር በኮሮናቫቨይረስ መያዛቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አሳተወቁ።

    ሽሪፓድ በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ካቢኔ ውስጥ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ሦስትኛው እንደሆኑ ተነግሯል።

    ቀደም ሲል የቤቶች ሚኒስትሩ አሚት ሻህና የፔትሮሊየም ሚኒስትሩ ዳርሜንድራ ፕራዳን በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ ነበር።

    ሕንድ በዓለም በሽታው ከተስፋፋባቸው ቀዳሚ አገራት ከአሜሪካና ከብራዚል ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በቫይረሱ በርካታ ሰዎችን ካጡ አገራት መካከልም አራተኛ ላይ ትገኛልች።

    ዛሬ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንድ ቀን 942 ሰዎች መሞታቸው በመመዝገቡ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 47 ሺህ 33 ከፍ ብሏል።

    በተጨማሪም ዛሬ 66 ሺህ 999 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ በመረጋገጡ በአንድ ቀን ከፍተኛው የህሙማን ቁጥር በአገሪቱ ተመዝግቧል። በዚህም እስካሁን 2.4 ሚኒዮን የሚጠጉ ሕንዳዊያን በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  20. የኬንያ ከፍተኛ የጤና ኃላፊ በኮቪድ-19 ሕይወታቸው አለፈ

    ኬንያ በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እና ሞት ለመቆጣጠር እየታገለች ባለችበት ወቅት አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን በኮቪድ-19 መሞታቸው ተሰምቷል።

    ካማዉ ሙጌንዳ ሀገሪቱን የኮቪድ -19 ክትባት የሙከራ መርሃ ግብር በበላይነት የሚቆጣጠረው የህክምና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ኃላፊ ነበሩ።

    አንዳንድ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት በኬንያ ጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከ450 በላይ ሰራተኞች በኮቪድ-19 ተይዘዋል።

    ባለስልጣናት እንደገለጹት ቢያንስ ሶስት የጤና ባለሙያዎች፤ አንድ ዶክተርና ሁለት ነርሶች እስካሁን በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ኬንያ ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ.እየጨመረ እንደመጣ ያስታወቀች ሲሆን የተጠቂዎች ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ ገልጻለች።

    እሰክኣሁን ከ28 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 450 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።