በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሲሻገር ሰባት ሰዎች ሞቱ

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 86 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ የህሙማኑን ቁጥር 2 ሺህ 20 አድርሶታል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በኤካ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለች በሰላም የተገላገለችው እናትን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል።በአጠቃላይም ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 27 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችን ጤና ይጠብቃል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሲሻገር ሰባት ሰዎች ሞቱ

  2. ኬንያ የለይቶ ማቆያ ማከሚያዎች በመሙላታቸው ህክምናው በቤት እንዲሰጥ ወሰነች

    በኬንያ የኮሮናቫይረስ ህክምና የሚሰጥባቸው የለይቶ ማቆያ ማከሚያ ማዕከላት መሙላታቸውን ተከትሎ ለህሙማኑ ህክምና በቤት እንዲሰጥ መወሰኑን የሃገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቀዋል።

    ሚኒስትሩ ሙታይ ካግዌ እንዳሉት በመጀመሪያ ደረጃ በቤት ውስጥ ለሚደረገው ህክምና የሚያገለግል መመሪያ እንደሚወጣና በመቀጠልም የጤና ማዕከላቱን ነፃ ለማድረግም ህሙማኑ ወደየቤታቸው የመላክ ስራ ይሰራል ብለዋል።

    በቤታቸው ሆነው ከኮሮናቫይረስ የሚያገግሙ ህሙማንም ላይ መገለልና አድልዎ እንዳይኖር ሚኒስትሩ ተማፅነዋል።

    በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ሁለት ለይቶ የማቆያ ህክምና መስጫ ማዕከል የሚገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም መሙላታቸው ተገልጿል።

    ሃገሪቷ በትናንትናው ዕለት 124 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መመዝገቧን ተከትሎ፤ አጠቃላይ ቁጥሩንም 2 ሺህ 340 አድርሶታል። ከነዚህም መካከል 592 ሲያገግሙ 78ቱ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    በቤታቸው ሆነው ከኮሮናቫይረስ የሚያገግሙ ህሙማን ከሰዎች ጋር መቀላቀልን ማስወገድ፣ የራሳቸው የመኝታ ክፍልም እንዲኖራቸውም የአለም አቀፍ ጤና ድርጅት መመሪያ ያዛል።

    ከህሙማኑ ጋር በጋራ እቃዎችን አለመጠቀም ወይም ፀረ- ተህዋሲያን (ዲስ ኢንፌክታንት) መርጨት እንዲሁም እንክብካቤ የሚሰጡ ግለሰቦችም መከላከያ ሊያደርጉ እንደሚገባም መመሪያው ያትታል።

  3. ከመቶ ቀናት በላይ ወደ አገራቸው መመለስ ያልቻሉት የራግቢ ተጫዋቾች

    ከማኑማ ሳሞአ ደሴቶች የመጡት የራግቢ ተጫዎቾች አውስትራሊያ የደረሱት የካቲት 15፣ 2012 ዓ.ም ውድድር ለማካሄድ ነበር።

    በኮሮናቫይረስ ጫና ምክንያት ግን ወደ አገራቸው መመለስ ሳይችሉ ከሶስት ወራት በላይ፣104 ቀናትን አስቆጥረው ነበር። ግጥሚያቸውን ጨርሰው ወደሃገራቸው ለመመለስ ከአውስትራሊያ ኒውዚላንድ የደረሱ ሲሆን ፤ በኒውዚላንድም በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ተነገራቸው።

    በለይቶ ማቆያ ባሉበትም ወቅት ሃገራቸው ድንበር የመዝጋት ውሳኔዋን አሳለፈች።

    መውጪያ መግቢያ በሌለበት ሁኔታም 20 የቡድኑ አባላት በኒውዚላንዷ ኦክላንድ ኑሯቸውን ከሶስት ወራት በላይ አድርገው ነበር።

    በቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥም 20ዎቹ በአንድ ክፍል በጋራ ለመኖርም መገደዳቸውንም አሳውቀዋል።

    በአሁኑ ሰዓት ወደ ሳሞአ የተመለሱ ቢሆንም ለሁለት ሳምንታት ያህል በለይቶ ማቆያ ውስጥ ገብተዋል፤ ቤተሰቦቻቸውንም እስካሁን አላዩም።

    "በኒውዚላንድ ስንደርስ ሞቃታማ ነበር፤ ያው አሁን ወደ ሃገራችን ልንመለስ ስንል ክረምት ገባ" በማለት የቡድኑ አባል ሃሪ ጁኒየር ናራያን ለቢቢሲ ገልጿል።

  4. በቻይና የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት መቆሙ ተነገረ

    የኮሮናቫይረስ መነሻ የሆነችውና የቫይረሱንም መዛመት ለመግታት ቀዳሚ ትግል ስታደርግ በነበረችው ቻይና የማህበረሰብ ስርጭት መቆሙ ተነግሯል።

    የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች እንዳስታወቁት በማህበረሰቡ ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት እንዳቆመና ህመምተኞችም እየመዘገቡ እንዳልሆነ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።

    ሆኖም ከሌላ ሃገራት የሚመጡ መንገደኞች በቫይረሱ መያዛቸውም ተገልጿል። በሻንግሃይ እንዲሁም በሲቹዋን ግዛቶችም አምስት ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው በትናንትናው ዕለት ሪፖርት ተደርጓል።

    በዚህ ሳምንት ረቡዕም እንዲሁ አንድ መንገደኛ የኮቪድ-19 የተገኘበት ሲሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ግን በተደረጉ ከፍተኛ ምርመራዎች ህሙማን ሳይገኙ ቀርቷል።

    በቻይና በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 83 ሺህ 27 ደርሷል።

  5. በሕንድ፣ በፓኪስታንና በባንግላዴሽ የኮቪድ-19 እየተስፋፋ ነው

    በሕንድ፣ ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ ነው።

    እነዚህ አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ካነሱ በኋላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።

    በእነዚህ ሶስት አገራት የሚኖረው ሕዝብ በአንድ ላይ ተደምሮ ከአለም ሕዝብ አንድ አምስተኛ እንደሚበልጥ ይገመታል።

    በፓኪስታን 86 ሺህ139 ሰዎች ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሲሆን ይህ ቁጥርም በቻይና ካለው ጋር ሲነፃፀር በልጦ ታይቷል።

    በባንግላዲሽ ከ57,500 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል። ሕንድ በበኩሏ በአንድ ቀን ብቻ 9 ሺህ ሰዎች መያዛቸውን የመዘገበች ሲሆን ይህም በአጠቃላይ በእነዚህ ሃገራት የተያዘውን ቁጥር ወደ 216 ሺህ 919 አድርሶታል።

    በእነዚህ አገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በንጽጽር ዝቅተኛ ሲሆን በሕንድ 6 ሺህ 75፣ በፓኪስታን፣ 1ሺህ 793፣ በባንግላዴሽ 781 ሰዎች መሞታቸውን ተገልጿል።

    ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአግባቡ ሳይመዘገብ ቀርቶ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አላቸው።

    • የኮቪድ-19 ክትባት ለድሃ አገራት እንዲደርስ የ2 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

    • ፖሊስ በአውስትራሊያ ሊካሄድ የታሰበው የፀረ-ዘረኝነት ሰልፍ እንዳይካሄድ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ

      ከሰሞኑ በነጭ ፖሊስ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊው ጆን ፍሎይድን ተከትሎ በበርካታ አገራት ተቃውሞዎች ቀጥለዋል። በአውስትራሊያም የብላክ ላይቭስ ማተር የተቃውሞ ሰልፍ በመጪው ቅዳሜና እሁድ መታቀዱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋታቸውን ገልፀዋል።

      ባለስልጣናቱም በሲድኒ ሊደረግ የታሰበው የፀረ-ዘረኝነት ሰልፍ እንዳይደረግ አጥብቀው የተቃወሙ ሲሆን፤ ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ሰልፍ እንዳይካሄድ የእግድ ትእዛዝ ጠይቋል።

      የደቡብ ዌልስ የፓርላማ አባል ግላዲስ ቤሬጂኪያን እንደተናገሩት በመጀመሪያ ደረጃ ለተቃውሞ ሰልፉ ፈቃድ የተሰጠው ቁጥሩ ትንሽ ነው በሚል ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አስር ሺህ ያህል ሰልፈኞች እንደሚሳተፉ ይፋ ሆኗል።

      የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች የኮሮናቫይረስ መመሪያዎች እንደሚጠበቁ ማስተማመኛ እንዳልሰጧቸው የምክር ቤት አባሏ ገልፀዋል።

      " ተቃዋሚዎቹ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ሰልፉን እንደሚያካሂዱ ማስተማመኛ ሊሰጡን አልቻሉም። ከዚህም በተጨማሪ ቁጥራቸውም በርካታ ሰዎችም መሰብሰባቸውም የጤና ስጋት ነው" ብለዋል።

      በግዛቷ በባለፉት ዘጠኝ ቀናት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ያልተመዘገበ ሲሆን ከሰሞኑ የተመዘገቡትም በለይቶ ማቆያ ባሉ መንገደኞች ነው ተብሏል።

    • ለጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ደማቅ ሽኝት ተደረገ

    • በብራዚል በኮሮናቫይረስ ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጣልያን በለጠ

      በብራዚል በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣልያን ከሞቱት መብለጡ ተገለፀ።

      ሐሙስ ዕለት ምሽት አገሪቱ 1ሺህ 473 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ያደረገች ሲሆን ይህም በመላ አገሪቱ እስካሁን የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 34 ሺህ አድርሶታል።

      በብራዚል ተመርምረው የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 580 ሺህ ደርሷል።

      በአገሪቱ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሞት ቁጥር የተመዘገበ ሲሆን መንግሥት እንደቀድሞው ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በተለመደው ሰዓትና መንገድ ይፋ ማድረጉን ትቷል።

      ከዚህ ቀደም ምንግዜም ከሰዓት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ዕለታዊ መረጃዎችን ያቀርብ የነበረ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በፊት ግን ይህ ቀርቶ ወደ ምሽት የዜና እወጃ ሰዓት ተላልፏል።

      ባለፉት ሁለት ሳምንታትም የምሽት ዜና በኋላ ካበቃ በኋላ መቅረብ መጀመሩን የብራዚልን የኮሮናቫይረስ ስርጭት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

      ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ እንደ ከዚህ ቀደሙ ያለ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት ባስተላለፉት መልዕክት ከዚህ ቀደም የክልል መንግሥታት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመኮነን የሰጡትን አስተያየት በማጠፍ የቫይረሱ አደጋ ሕይወታቸውን ካጡትም ሊልቅ እንደሚችል ተናግረዋል።

    • "የ13 ዓመት ልጄን በነጭ ፖሊስ ልትገደል ትችላለህ ማለት ልብን ይሰብራል" ሶማሊያዊቷ እናት በአሜሪካ

    • በቅርብ ሳምንታት የደቡብ አፍሪካ ሆስፒታሎች በሕሙማን ይጨናነቃሉ ተባለ

      የደቡብ አፍሪካ ሆስፒታሎች በሳምንታት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ሕሙማን ሊጨናነቁ እንደሚችሉ የአገሪቱ ከፍተኛ የክትባት ባለሙያ ተናገሩ።

      በአሁኑ ሰዓት በኬፕታውን የሚገኙ ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ መሙላታቸውን ገልፀው በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመላ አገሪቱ እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል።

      በኬፕታውን የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በቅርቡ ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ ታካሚዎችን በመቀበል እንደሚቸገሩ እያስጠነቀቁ ነው።

      በምስራቃዊ ኬፕታውን አሁን ያለው ሁኔታ ከሕክምና ተቋማቱ አቅም በላይ ሆኗል።

      የአገሪቱ የኮቪድ-19 ከፍተኛ ባለሙያ፣ ፕሮፌሰር ሻቢር ማዲሂ ሁኔታውን " አስደንጋጭ" ያሉት ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር አሁን መታየት መጀመሩን ገልፀዋል።

      ፕሮፌሰሩ አክለውም በምስራቃዊ ኬፕታውን የተከሰተው ለሌችም ትምህርት መሆን እንዳለበት እንዲሁም ቀሪው የአህጉሪቱ ክፍልም እንዲሁ ሊጠቃ እንደሚችል ግንዛቤ መውሰድ እንዳለበት አስረድተዋል።

      ማንኛውም ሰው አፍሪካ ወጣት ዜጎቿ በርካታ በመሆናቸው ከኮሮናቫይረስ ጠንካራ ክንድ ትተርፋለች ብሎ የሚያስብ ከሆነ ከንቱ ምኞት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

    • እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች

      ወደ ቢቢሲ አማርኛ የኮሮናቫይረስ የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንኳን ደህና መጡ!

      በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለፀዋል። ባለሙያዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰሩ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

      በአዲስ አበባ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 1,205 ደርሷል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከ ትናንትናው ድረስ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1636 ደርሷል። ከእነዚህም መካከል 18 ሰዎች ሞተዋል።የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት፣ ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችንም ጤና ይጠብቃል።

      ከመላው ዓለም የመራረጥናቸውን አበይት ዜናዎች እዚህ መከታተል ትችላላችሁ! እናንተም ጤና ወዳጆቻችሁም ደህና እንዲሆኑ ምኞታችን ነው!

      አብራችሁን ሁኑ!