ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሲሻገር ሰባት ሰዎች ሞቱ
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 86 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ የህሙማኑን ቁጥር 2 ሺህ 20 አድርሶታል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በኤካ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለች በሰላም የተገላገለችው እናትን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል።በአጠቃላይም ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 27 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችን ጤና ይጠብቃል።
የቀጥታ ሽፋን
የዓለም ጤና ድርጅት የጭንብል አጠቃቀም አዲስ መመሪያ አወጣ
የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ በፊት ስለአፍናጫና አፍ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም አውጥቶት የነበረውን መመሪያ መለወጡን አስታወቀ።
ድርጅቱ ቀደም ብሎ የህክምና ጭምብል መጠቀም ያለባቸው የጤና ሠራተኞች፣ የኮሮናቫይረስ ህሙማንና የህሙማኑ እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ ሊሆኑ እንደሚገባ መክሮ ነበር።
የተቀየረው ምንድን ነው?
• የዓለም ጤና ድርጅት አሁንም የህክምና ጭምብል በስፋት በሁሉም ሰው መጠቀም የለበትም ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ከተለያዩ ጨርቆች የሚዘጋጁና እጥረት የማይኖርባቸውን አስፈላጊ ከሆነም ቤት ውስጥ ማዘጋጀት የሚቻሉትን ጭንብሎት መጠቀም እንደሚቻል ገልጿል።
• ድርጅቱ እንዳለው የሕዝብ ትራንስፖርት ላይና የገበያ ቦታዎችን በመሳሰሉ አካላዊ ርቀትን በአግባቡ ለመጠበቅ በማይቻልባቸው ስፍራዎች ሁሉም ሰው ከጨርቅ የተሰሩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ማድረግ አለበት።
• ድርጅቱ የጭንብል አጠቃቀም መመሪያውን በማስፋት በቀጥታ ከኮሮናቫይረስ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ለምሳሌም በሆስፒታሎች የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ የጤና ሠራተኞች ጭምር ለህክማና ባለሙያዎች የተዘጋጁ ጭንብሎችን ማድረግ አለባቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው ከዚህ በፊት ያወጣውን የጭንብል አጠቃቀም መመሪያ ላይ ክለሳ ያደረገው በሽታው ያለባቸው ሰዎች ምልክት ከማሳየታቸው በፊት በሽታውን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየተገኙ በመሆናቸው ነው።
ድርጅቱ ቀደም ሲል ለቫይረሱ መሰራጨት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ አልታወቀም ሲል ነበር።
በከፋ ዞን በሞቱ ግለሰቦች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱ ስጋት ፈጥሯል
የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንዴት አደራችሁ!
በያላችሁበት ያማረ ቅዳሜ ጠዋት እያሳለፋችሁ እንደሆነ እምነታችን ነው።
ከአገር ቤትና ከተቀረው ዓለም የሰነድናቸውን ዜናና ታሪኮችን ይዘን በድረ-ገፃችንና በፌስቡክ አድራሻችን ተገኝተናል።
እንደተለመደው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ በትኩሱ በትኩስ ወደናንተ ዘገባ የምናደርስበት የቀጥታ ዘገባ ገፃችን በመረጃ ተሞልቶ ይጠብቃችኋል።
ሌሎችም ጊዜ የማይሽራቸው ታሪኮች ድረ ገጻችን ላይ ያገኛሉ። ራስዎንና ቤተሰብዎን ከገዳዩ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እብዲጠብቁ ማሳሰብ እንወዳለን።
ሰናይ ዕለተ ቅዳሜ!
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በለይቶ ማቆያ የነበሩ 86 የህክምና ሠራተኞች ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው ተነገረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በለይቶ ማቆያ የነበሩ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በሙሉ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ሁለት ጊዜ በምርመራ ተረጋግጦ ዛሬ ከማቆያው መውጣታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስታወቀ።
የጤና ባለሙያዎቹ በአጋጣሚ በተከሰተው ችግር ቢደናገጡም በዩኒቨርሲቲውና በሌሎች አካላት በተደረገላቸው የሥነ ልቦናና ሌሎች ድጋፎች መበርታታቸውን በለይቶ ማቆያ የነበሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪ የሆኑት ዶ/ር ወንድማገኝ ጥበቡ፤ "የመጀመሪያ የምርመራ ውጤታችንን እስከምናውቅ ተጨንቀን ነበር" ብለዋል።
እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ነርስ የሆኑት አቶ ጥሩዓለም እጅጉ "ይህ ችግር ከመከሰቱ በፊት የነበረው መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል ይችል እንደነበር ስለሚያመላክት ትልቅ ትምህርት ሆኗል" ማለታቸውን ዩኒቨርሲቲው በገጹ ላይ አስፍሯል።
በዩኒቨርሲቲው ከግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በድንገተኛ ሕሙማን ክፍል ከተገኘው የኮቪድ-19 ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸው 86 የህክምናና ሌሎች ባለሙያዎች ለተከታታይ 14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንደነበሩ ዩኒቨርሲቲው አስታውሷል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች የጨርቅ 'ማስኮች' ማድረግን አበረታታ
የዓለም ጤና ድርጅት ዜጎች በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ከጨርቅ የተሰሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ያድርጉ ሲል መንግሥታትን መከረ፡፡
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ከጨርቅ የተሰሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች በጤናማ ሰዎች መለበስ እንዳለባቸው የሚያሳይ በቂ መረጃ አለመኖሩን አስታውቆ ነበር፡፡
የህክምና ማስኮችም ቢሆኑ መለበስ ያለባቸው በታመሙ ሰዎች እና እነርሱን በሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች መሆን አለበት ማለቱ ይታወሳል፡፡
"አሁን ላይ ግን የጨርቅ ማስኮቹ በትክክል ከተጠቀምንባቸው ከታመመ ሰው በሳልና በንጥሻ የሚወጡ ነጠብጣቦችን ለመከላከል እንደሚያስችሉ መረጃዎች አሉን" ሲሉ ዶ/ር ማሪያ ቫን ኬርኮቬ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡
በቅርብ ሳምንታት በተካሄደው ጥናት ላይ ተመስርቶ አዲስ በወጣው በዚህ መመሪያ፤ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) የቫይረሱን ሥርጭት ከምንገታባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን በመግለጽ፤ ሰዎች እርሱ ብቻ ይጠብቀናል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወስዱ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
በናይጄሪያ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንዲቆም ተጠየቀ
በናይጀሪያ ከተሞች ሌጎስና አቡጃ የመብት አቀንቃኞች በታዳጊ ሴቶች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ አደባባይ በውጣት ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የኡዌላ ኦሞሱማ የተባለች የ22 ዓመት ተማሪ መደፈሯን ተከትሎ 'ፍትህ ለኡዋ' የሚል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተካሂዶ ነበር፡፡
ተማሪዋ የመደፈር ጥቃቱ የተፈጸመባት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን ከእሳት ማጥፊያ ጋር በተደጋጋሚ ስላጋጯት በደረሰባት ጉዳት ከሁለት ቀናት በኋላ ሕይወቷ አልፏል፡፡
በዚህ ተቃውሞ ላይም በርካታ ሴቶች፤ መንግሥት ሴቶችን ከዚህ ዓይነት እንዲጠብቅ የሚያሳስቡና ለሟቿ ፍትህ እንዲሰጥ የሚጠይቁ መልዕክቶች የተጻፈባቸው ፖስተሮች ይዘው ታይተዋል፡፡
የናይጄሪያ ፖሊስ ጾታን መሰረት ያደረጉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመመርመር በርካታ ሰዎችን እንዳሰማራ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስታውቆ ነበር፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየጨመሩ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
በተለይ ወረርሽኙን ለመግታት ሲባል ከቤት ያለመውጣት ገደብን በጣሉ አገራት የቤት ውስጥ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተዘግቧል፡፡
ከእነዚህ የአፍሪካ አገራት መካከል ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያና ዚምባብዌን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በኮቪድ-19 ምክንያት በክትባቶች ስለተስጓጎሉ በቀን 6 ሺህ ሕጻናት ይሞታሉ
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን ላይ የሚያደርገውን ምርምር አቋረጠ
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን ላይ የሚያደርገውን ምርምር ማቋረጡን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው መድኃኒቱ ላይ የሚያደርገውን ምርምር ለማቋረጥ የወሰነው ክኒኑ ኮቪድ-19ኝን ለማከም ምንም ዓይነት ጠቀሜታ እንደሌለው ስለተረጋገጠ ነው።
የአጥኚዎቹ ኃላፊ ሐሙስ ዕለት ምርምሩ እንዲቋረጥ አዘዋል። መድኃኒቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት እየሞቱ ያሉ ሰዎችን ይታደጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ጥናቶቹ ግን ምርምሩ ከንቱ መሆኑን አሳይቷል።
ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን ከወሰዱ ታካሚዎች መካከል 25 በመቶው ከ28 ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። ነገር ግን መደበኛ ሕክምና ከተሰጣቸው መካከል 25 በመቶው ናቸው ሕይወታቸውን ያጡት።
ዘ ላንሴት የተሰኘው የሕክምና መፅሔት ለወባና ሌሎች በሽታዎች የሚውለው ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን የኮቪድ-18 ታማሚዎችን ከማዳን ይልቅ ለሞት ይዳርጋል ማለቱን ተከትሎ በርካቶች ጥናታቸውን በማቋረጥ ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን ለኮቪድ-19 ፈውስ ነው ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።
በዩናይትድ ኪንግደም የሟቾች ቁጥር 40 ሺህ ተሻገረ
ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ ሆኗል።
ባለፉት 24 ሰዓታት በኮቪድ-19 ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ 357 መሞታቸውን ተከትሎ ነው ቁጥሩ 40 ሺህ የተሻገረው።
የሟቾች አሃዝ የተገኘው ከሆስፒታሎች ብቻ ሳይሆን ከአረጋውያን መንከባከቢያዎችና ከመኖሪያ ቤቶች ነው።
ኮሮናቫይረስ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ ወዲህ የሟቾች ቁጥር የዛሬውን ጨምሮ 40 ሺህ 261 ደርሷል። ይህም ቁጥር አገሪቱ ከአሜሪካ በመቀጠል በሟቾች ቁጥር ከዓለም ሁለተኛዋ ያደርጋታል።
ባለፈው መጋቢት የአገሪቱ ጉምቱ ሐኪሞች የዩናይትድ ኪንግደም ሟቾች ቁጥር ከ20 ሺህ ይልቃል ሲሉ ገምተው ነበር።
በአሜሪካ የሥራ አጦች ቁጥር መቀነስ ተስፋ ፈነጠቀ
የአሜሪካ የሰራተኛ ገበያ በግንቦት ወር ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱ በተለይ ለምጣኔ ሐብቱ ዘርፍ መልካም ዜና ሆኗል፡፡
አገሪቷ በወረርሽኙ ሳቢያ ያጋጠማት የኢኮኖሚ ውድቀት ከተሰጋው ያነሰ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ቢዝነሶች እንቅስቃሴ እየጀመሩ በመሆናቸውና የሰራተኛ ቅጥር በመጀመሩ የሥራ አጦች ቁጥር በፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር ከነበረው 14.7 በመቶ ወደ 13.3 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
ሆስፒታሎች፣ ኮንስትራክሽን እና የጤና ተቋማትም ሠራተኞችን ተቀብለዋል፡፡
በትምህርትና የንግድ ዘርፎችም በአጠቃላይ 2.5 ሚሊየን የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል፡፡
ይህ የሆነው አብዛኞቹ የአገሪቷ ግዛቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የጣሉትን ጥብቅ ገደቦች እያላሉ በመሆናቸው ሲሆን ቢዝነሶች እየተከፈቱ ሲሄዱም ድርጅቶች ሰራተኞች መቅጠር ጀምረዋል፡፡
በርካታ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች በአገሪቷ ያለው የሥራ አጦች ቁጥር ከ20 በመቶ ይበልጣል ሲሉ አስጠንቅቀው የነበረ ሲሆን አሁን የታየው ለውጥ አስደንቋቸዋል፡፡
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም በትዊተር ገጻቸው ላይ በታየው ተስፋ ሰጭ ለውጥ ራሳቸውን አድንቀዋል፡፡
በአሜሪካ ከሌሎች አገራት በበለጠ በቫይረሱ የተያዙም ሆነ የሞቱ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል፡፡
የጃካርታ መስጊዶች ከሦስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፈቱ
በኢንዶኔዥያ ዋና መዲና ጃካርታ ከሦስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መስጊዶችና ሌሎች የአምልኮ ሥፍራዎች መከፈታቸው ተገለጸ፡፡
ይሁን እንጅ ወደ መስጊድ የሚሄዱ አማኞች የራሳቸውን መስገጃ ምንጣፍ መያዝና አካላዊ ርቀታቸውን መጠበቅ አለባቸው ተብሏል፡፡ ወደ መስጊድ ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም የሙቀት ልኬት ይደረግላቸዋል፡፡
ከእዚህም በተጨማሪ አገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ጥላው የነበረውን እገዳ ማላላቷን ተከትሎ ቢሮዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የገበያ ቦታዎች እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሚከፈቱ የከተማዋ አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡
በኢንዶኔዥያ እስካሁን ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 1ሺህ 770 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 7ሺህ 766 በቫይረሱ የተያዙ እና 523 በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች የተመዘገቡት የቫይረሱ ማዕከል በሆነችው ጃካርታ ነው፡፡
በዩኬ 35 ቀናትን ራሳቸውን ስተው የነበሩት ግለሰብ አገገሙ
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በአብዛኛው የምንሰማቸው ዜናዎች የሚረብሹና የሚያስጨንቁ ናቸው፡፡ ነገር ግን በቫይረሱ ተይዘው ከሞት አፋፍ የተመለሱ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የ66 ዓመቱ ሪቻርድ ሃንሰን አንዱ ናቸው፡፡
ሪቻርድ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ 60 ቀናትን በሆስፒታል ያሳለፉ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 35ቱን ቀናት ያለፉት ራሳቸውን ስተው ነው፡፡
ሪቻርድ በስፔን በሚገኘው ተሬኒፌ ደሴት በመዝናናት ላይ ሳሉ በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ያምናሉ፡፡
በቫይረሱ ሳቢያ ለሳንባ ምች እና ለኩላሊት ሥራ ማቆም የተዳረጉት ሪቻርድ ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን ይህንን ሁሉ አስጨናቂ ጊዜ አልፈው ከሆስፒታል ሊወጡ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በእርግጥ ሪቻርድ እንዲህ ዓይነቱን መከራ ያሳለፉ ብቸኛው ሰው አይደሉም፡፡
ሌሎች ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችም የተስፋ መልዕክታቸውን አጋርተዋል፡፡ ከኮሮናቫይረስ እያገገሙ ያሉ ምን ይላሉ? የ2 ወጣት ሴቶች ታሪክ
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ 2.9 ሚሊየን ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡
ኡጋንዳ ሁሉንም ሚኒስትሮቿን መመርመር ጀመረች
በኡጋንዳ ሁሉም የመንግሥት ሚኒስትሮች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን፤ እንደ ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከሆነ ሚኒስትሮቹ በአገሪቷ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ በየሁለት ሳምንቱ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም 79 ባለሥልጣናት ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
ቀደም ሲል የኡጋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሃካና ሩጉንዳ፤ ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን ለ14 ቀናት እንዳገለሉ አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን እርሳቸው ባደረጉት ምርመራ ነፃ ቢባሉም የጤና ባለሙያዎች የሰጧቸውን አስተያየት በመስማት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን እንደሚያገሉ ተናግረዋል።
የብሔራዊ የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል መሪ ዶ/ር ሩጉንዳን ኃላፊነትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሰስ አሊ ተክተው እንዲሰሩ ተወክለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት ሰራተኞችም ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡
በኡጋንዳ እስካሁን 557 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ በአገሪቷ ያለው የቫይረሱ ሥርጭትም እየጨመረ ነው፡፡
ይሁን እንጅ የአገሪቷ መንግሥት ከሁለት ወራት በፊት ያሳለፈውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያላላ ነው፡፡
የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከድንበር አካባቢ በስተቀር በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
ሰበር, ኢትዮጵያ፡ ተጨማሪ 169 ሰዎች ኮቪድ-19 ተገኘባቸው
በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 5789 የላብራቶሪ ምርመራ 169 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አንድ የ35 ዓመት ኢትዮጵያዊት ሕይወት አልፏል። ሆስፒታል ውስጥ የአስከሬን ምርመራ ሲደረግ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባታል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 111 ወንዶች እና 58 ሴቶች መሆናቸውንም መግለጫው አመላክቷል። የዕድሜ ክልላቸውም ከ1 እስከ 78 መሆኑ ተገልጿል።
ከ169ኙ ግሰለቦች መካከል 138 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 11 ሰዎች ከኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች እያንዳንዳቸው 4 ሰዎች፣ 6 ሰዎች ከአማራ፣ 5 ሰዎች ከሶማሊ እና 1 ሰው ከሐረሪ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአጠቃላይ በሃገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 1805 የደረሰ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 262ዎቹ አገግመዋል። ሃገሪቱ በኮሮና ያጣቻቸው ዜጎችም ቁጥር 19 ደርሷል።
ኢትዮጵያ እስከዛሬ [አርብ] ሪፖርት ድረስ 131 ሺህ 368 ሰዎችን መርምራለች።
የኡጋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳቸውን አግልለው ተቀምጠዋል ተባለ
የኡጋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሃካና ሩጉንዳ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን አግልለው እንደተቀመጡ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከሳቸው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ነው።
ምንም እንኳን እርሳቸው ባደረጉት ምርመራ ነፃ ቢባሉም የጤና ባለሙያዎች የሰጧቸውን አስተያየት በመስማት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን እንደሚያገሉ ተናግረዋል።
የሃገሪቱ ጋዜጠኞች እንደዘገቡት በርካታ የፓርላማ አባለትም ምርመራ እያደረጉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ውሳኔያቸውን ያሳወቁት በትዊተር ገፃቸው ነው።
2.2 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ከረሜላ ለመግዛት ያቀዱት ሚኒስትር ከኃላፊነታቸው ተነሱ
የማዳጋስካር ትምህርት ሚኒስትር የ2.2 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ከረሜላ ለመግዛት አቅደው ነበር።
ሪያሶዓ አንድሪያማናና እንዳሉት ባለፈው ሳምንት ህጻናት የተዘጋጀውን ባህላዊ የኮቪድ-19 መከላከያ መጠጥ እንዲወስዱ ለመደለል በሚል ከረሜላዎችን ማዘዛቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የማዳጋስካር መንግሥት ያዘጋጀው ባህላዊ መጠጥ ኮቪድ-19 ይፈውሳል በሚል ሲተዋወቅ ነበር።
እንደ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ እያንዳንዱ በማዳጋስካር የሚገኝ ተማሪ ሶስት ሶስት ከረሜላ ይደርሰዋል ተብሏል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት የሚንስትሩ እቅድ ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆይሊና ውድቅ አድርገውታል።
ሚንስትሯ የተቋማቸውን ገንዘብ በመመዝበር ተወንጅለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሯ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው የተሰማው ትናንት ሲሆን በምትካቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትሩ ቦታቸውን ተክተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን ድረስ የኮሮናቫይረስን የሚፈውስ ምንም ዓይነት ክትባትም ሆነ መድሃኒት አለመገኘቱን አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ ጆርጅ ፍሎይድን ለማሰብ ዜጎች ጥቁር የሚለብሱበት ዘመቻ ሊጀምር ነው
ባለፈው ሳምንት በሚኒያፖሊስ እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ለአስር ደቂቃ ተጭኖት ህይወቱ ያለፈውን ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን ለመዘከር የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ በዛሬው እለት አንድ ዘመቻ እንደሚጀምር አስታውቋል።
ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ ጆርጅ ፍሎይድን ለመዘከር እንዲሁም ዘረኝነትንም ለመቃወም "ብላክ ፍራይደይ" (ጥቁሩ አርብ) የሚል ዘመቻ በዛሬው ዕለት ይጀምራል።
ዘመቻውም ደቡብ አፍሪካውያን በሙሉ በየሳምንቱ አርብ ጥቁር እንዲለብሱ ያለመ ሲሆን ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነም አልተገለፀም።
በአሜሪካ ውስጥ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ድጋፍ ለማሳየት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰፈነውን ዘረኝነትና የፖሊስ ጭካኔንም ለመታገል ኢላማ አድርጓል።
ዘመቻው በሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ይፋ እንደሚሆን ፓርቲው በትዊተር ገፁ አስፍሯል።
የኮሮናቫይረስ ክትባትን መቼ እንጠብቅ?
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለምን ተስፋፋ?