የሚኒስትሮች ም/ቤት በኮቪድ -19 ህክምና ላይ በቀጥታ ለሚሳተፉ የማበረታቻ ክፍያ ወሰነ
ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ውሳኔ ካሳለፈባቸው መካከል አንዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያ ሥራ ላይ እንዲውል ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡
ውሳኔውን ያሳለፈው የጤና ሚኒስቴር፤ ወረርሽኙን ለመከላከል ለጤና ዘርፉ ሰራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያ ለመወሰን ባዘጋጀው መመሪያ ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ የውሃና መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ለማሻሻል ባቀረበው አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ ውይይት አድርጎ ለሕዝብ ተወካዮች መርቷል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት በኢኮኖሚ ላይ የተከሰተውን ጫና ለመቋቋም እና የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የመካከለኛ ዘመን (የ2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ በመወያየትም፤ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ከጨመረ በኋላ አዋጁን እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች መርቶታል፡፡
ማዕቀፉም በሥራ ላይ ይዋል ብሏል፡፡
ለሕዝብ ጥቅም መሬት ሲለቀቅ ስለሚከፈል ካሳ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡