የዓለም ጤና ድርጅት ብራዚል በደቡብ አሜሪካ አዲሷ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ማዕከል ሆናለች አለ።
ድርጅቱ ትናንት ከደቡብ አሜሪካ አገራት ብራዚል ክፉኛ በቫይረሱ የተመታች አገር ናት ያለ ሲሆን፤ በአፍሪካም በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን በፍጥነት እየጨመረ ነው ብሏል።
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከ100 ሺህ ማለፉ ሪፖርት ተደርጓል።
ዛሬ [ቅዳሜ ጥዋት] አሃዞች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ባሉ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 103 ሺህ 875 ደርሷል። 3ሺህ 184 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከ20ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በመያዝ ቁጥር አንድ ስትሆን፤ ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ናይረጄሪያ ሌሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባቸው አገራት ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ በአፍሪካ ሪፖርት ከተደረገ ከ14 ሳምንት በኋላ በሁሉም የአህጉሪቱ አገራት ቫይረሱ መሰራጨቱን ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ አስታውቋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ማተሺዲሶ ማኦቲ የአፍሪካ አገራት የጤና ስርዓት ደካማ መሆኑን በማስታውስ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ቁጥር ቢጨምር መቆጣጠር እንደሚዳግት አስጠንቅቀዋል።
ከ50 በመቶ የሚሆኑት አገራት ደግሞ ባለፈው ሳምንት የ50 በመቶ ጭማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መዝግበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአደጋ ጊዜ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማይክ ራይን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ "ደቡብ አሜሪካ የቫይረሱ ስርጭት ማዕከል ሆናለች" ሲሉ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ብራዚል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት አገር ናት። የአገሪቱ ባለስልጣናት የጸረ-ወባ መድሃኒት የሆነውን ሃይደሮክሎሪኪን ለኮቪድ-19 ተማሚዎችን እንዲሰጥ መወሰናቸውን ተናግረው፤ ይህ መድሃኒት የዚህ በሽታ ፈወሽ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ እንዳሌለው ዳግም አስታውሰዋል።
ዶ/ር ማይክ ራይን ግማሽ በሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ቫይረሱ በማህብረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ በቫይረሱ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሊሞቱ ያልቻሉበት አንዱ ምክንያት ከጠቅላላው የአህጉሪቷ ህዝብ ገሚሱ 18 ዓመት እና ከዚያ በታች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል ብለዋል።