በአፍሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 104 ሺህ 279 ደረሰ
የአፍሪካ ህብረት የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በ55ቱ የአፍሪካ ሃገራት እስካሁን 104ሺህ 279 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ፤3ሺህ 185 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል፡፡ 41ሺህ 717 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡
- ደቡብ አፍሪካ፡ ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የጣለቻቸውን ገደቦች እያላላች ሲሆን በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ 3ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ወደ ማንሳት እንደምትሻገር አሳውቃለች፡፡ ውሳኔው ተግባራዊ ከሆነም የ7ኛ እና የ12 ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፡፡ አንዳንድ የንግድ ተቋማትም ወደ ስራ ይገባሉ፡፡
- ናይጄሪያ፡ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚኖሩባትት ናይጄሪያ፤የኢድ አልፈጥር በዓልን በቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ብቻ እንዲያሳልፉ አዝዛለች፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
- ሱዳን፡ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ፋይሰል ሞሃመድ ሳለህ፤ ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደቡን እየጣሱ ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ቃል አቀባዩ ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ከሌላቸው ሰዎች በስተቀር ከግዛት ወደ ግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴ አይፈቀድም፡፡
- ዛምቢያ፡ የዛምቢያ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን እንዳገለሉ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ "ሁሉንም ጥንቃቄዎች ካደረኩ በኋላ ትናንት በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ" በማለት እስካሁን ግን የበሽታው ምልክቶች እንዳልታየባቸው ጠቅሰው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አስፍረዋል።