በትሪፖሊ የኮሮናቫይረስ ሆስፒታል በተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት ሳቢያ ተዘጋ
በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው መንግሥት በተደጋጋሚ በሚሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ምክንያት ትሪፖሊ የሚገኘውን የኮሮናቫይረስ ሆስፒታል ለመዝጋት ተገደድኩ አለ።
የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት አል-ካሃደራ የተባለው ሆስፒታል ባሳለፍነው ሐሙስ ዕለትም የቦምብ ጥቃት አስተናግዷል። ይህም በጥቂቃት ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
ትሪፖሊን ተቆጣጥሮ የሚገኘው መንግሥት ሆስፒታሉ ላይ ለሚሰነዘሩት ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በተባባሩት መንግሥታት እና በጀነራል ሃፍታር ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ከሰሞኑ ጠንክሮ እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።
ጀነራል ሃፍታር የሚመሩት የሊቢያ ብሔራዊ ጦር፤ ምስራቃዊ የሊቢያ ክፍልን ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ሊቢያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ 19 ሰዎች ያገኘች ሲሆን እስካሁን የመረመረችው ሰው ቁጥር ግን ከ400 አይዘልም ተብሏል።