በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሦስት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ቁጥሩ 25 ደረሰ

በዚህ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከ720 ሺህ በላይ ሰዎችን ይዟል። 34 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ መካከል ደግሞ ጥቂትም ቢሆን ተስፋ የሚሰጡ ዜናዎች አይጠፉም። ይህ በእንዲህ እያለ ማንኛውም ሰው ራሱን ሌሎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የተረጋገጠው መከላከያ መንገድ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና በሚያስሉና በሚያስነጥሱበት ወቅት አፍን መሸፈን ናቸው። እናንተ ራሳችሁን ከቫይረሱ እየጠበቃችሁ በጤና ኑሩልን። ስለበሽታው ጠቃሚ ዘገባዎችን በቀጥታ ከዚህ ገጽ ታገኛላችሁ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኬንያ ፓርላማ 50 እንደራሴዎቹ የኮሮና ምረመራ እንዲያደርጉ ጠየቀ

    በኬንያ አንድ የምክር ቤት አባል ኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኬንያ አንድ የምክር ቤት አባል ኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል

    የኬንያ የታችኛው ምክር ቤት አባላት የሆኑ 50 እንደራሴዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ገለፀ።

    ምክር ቤቱ ይህንን ሊል የቻለው በቅርቡ አንድ የሥራ ባልደረባቸው ቫይረሱ ስለተገኘባቸውና እነዚህ እንደራሴዎቹም በነበራቸው ንክኪ የተነሳ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ነው።

    ምክር ቤቱ የ50ውን የምክር ቤት አባላት ስም ዝርዝር ለጤና ሚኒስቴር ማስገባቱ ታውቋል።

    አክሎም በአስገዳጅ ሁናቴ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚፈልግ ገልጿል።

    ከዚህ ቀደም በኮሮናቫይረስ የተያዙት የሕዝብ እንደራሴ ከጀርመን ከተመለሰ የኪሊፊ ምክትል አገረ ገዢ ጋር በነበራቸው ንክኪ በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

    በኬንያ እስካሁን ድረስ 42 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ ሁሉም አገሪቱም ድንበሯቿን በመዝጋት የሰዓት እላፊ ማወጇ ይታወሳል።

  2. በቅርቡ ከውጭ አገራት ወደ አማራ ክልል የመጡ ሰዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዙ

    የባህር ዳር ከተማ

    በኮሮናቫይረስ መያዘቸው በዛሬው ዕለት የተገለጹት ሁለት ሰዎች የተገኙት በአማራ ክልል ውስጥ እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የህሙማኑ ቁጥር 23 መደረሱን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ግለሰቦች የቅርብ ጊዜ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ የነበራቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል።

    አንደኛዋ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴት መጋቢት 10 ላይ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን ሌላኛው 32 ዓመት ወንድ ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪና መጋቢት 12 ቀን ከአሜሪካ የመጣ ጎልማሳ መሆኑ ተገልጿል።

    ሁለቱም ግለሰቦች የበሽታው ምልክቶች ስለታዩባቸው ምርመራ ተደርጎባቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋገጦ በክልሉ የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከግለሰቦቹ ጋር የቅርብ ንክኪ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን የመከታተልና የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

    በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ባለፉት ሦስት ሳምንታ ውስጥ ከውጭ አገራት ወደ ክልሉ የገቡ ዜጎች በየአካባቢያቸው ወደ ሚገኙ የመንግሥት የጤና ተቋማት በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርጉ አዘዘ።

    በክልሉ የገጠር አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችም የተከሰተው ወረርሽኝ አስቸጋሪ መሆኑን በመረዳት ለግብይትም ሆነ ለሌላ ማኅበራዊ ጉዳዮች ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ በማቆም ባሉበት ሆነው ራሳቸውን እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

    በተጨማሪም የክልሉ ነዋሪዎች አሁን ካለው የወረርሽኙ አሣሣቢነት አንፃር እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ በክልሉ ውስጥ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊቋረጥ ስለሚችል፤ ይኸንኑ በመረዳት በቋሚ የመኖሪያ ቦታቸው ላይ በመሆን ከመንግሥት የሚሠጠውን ትዕዛዝ እንዲጠባበቁ ኮሚቴው አሳስቧል።

  3. የኮቪድ-19 መዛመትን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ እመርታ ያሳዩ ስድስት ምርቶች

    የቡና ሻጭ

    የኮሮና ቫይረስ መዛመት እያሻቀበ ባለበት በአሁኑ ወቅት በንግዱ አለም ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳርፏል፤ ንግዶች አሽቆልቁለዋል፣ አንዳንዶችም ላያንሰራሩ ወድቀዋል። የአንዱ እርግማን ለአንዱ ምርቃን እንዲሉ የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ተከትሎ ንግዳቸው በከፍተኛ ሁኔታ እመርታ ያሳዩም ዘርፎች አሉ። የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

  4. ኬንያውያን 'ጉሊት ሻጮች' ኑሯችንን ለመደገፍ ረዘም ያለ ሰዓት መስራት አለብን በማለት የሰዓት እላፊ አዋጁን ጣሱ

    በምዕራብ ኬንያ የሚገኙ ነዋሪዎችና ፖሊስ በባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰዓት እላፊ አዋጁን በመጣስ ተጋጭተዋል።

    ላንጋስና ኤልዶሬት አካካቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ረዘም ያለ ሰዓት መስራት ግዴታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

    ነዋሪዎቹ ኢመደበኛ በሆነው የንግድ ስራ የሚተዳደሩና መንገድ ላይ የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ ምግብ እንዲሁም አትክልቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩናቸው።

    ነዋሪዎቹ ለሃገሪቱ ሚዲያ እንደተናገሩትም የንግድ ስራቸው እየጦፈ የሚሄደው ወደ ምሽት ሲሆን ይህም ሰው ወደ ቤቱ በሚመለስበት ሰአት ነው ብለዋል።

    ከቤታቸው ደጃፍም የሰዓት እላፊው ከሚያዘው ትእዛዝ ውጭ በመቆምም ቤት አንገባም በሚል ሲጮሁ ታይተዋል።

    ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በመጠቀም ነዋሪዎቹን ለመበተን የሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹንም እስር ይጠብቃችኋል በሚል አስጠንቅቋል። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ፖሊስ ያልተገባ ኃይል በመጠቀም ነዋሪዎችን ሲደበድብ ታይቷል።

    አንድ ቪዲዮም ነዋሪዎች ወደ ፖሊሶች ድንጋይ ሲወረውሩ አሳይቷል።

    ኬንያ የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመቀነስ የሰዓት እላፊ አዋጅ ያወጀች ሲሆን ይህም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥዋቱ አስራ አንድ ሰዓት አስፈላጊ ከሚባሉ አገልግሎቶች ውጭ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይቻልም ብላለች። እስካሁን ባለው መረጃ አርባ ሁለት ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የአንድ ግለሰብም ህይወት ተቀጥፏል።

    የ YouTube ይዘትን ይለፉት
    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም። YouTube] ማስታወቂያ ሊኖረው ይችላል።

    የ YouTube ይዘት መጨረሻ

  5. በደቡብ ክልል እንዲሁም በአሰላ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወሰነ

    የመለስተኛ የሕዝብ ማመላሻ መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር ሲባል ከዛሬ ዕኩለ ቀን ጀምሮ ወደ ደቡብ ክልል ማንኛውም የሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪት እንዲቋረጥ ተወሰነ።

    በተያያዘ ዜናም በአሰላ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ መወሰኑም ተሰምቷል።

    የደቡብ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ግብረ ኃይል እንዳለው አገር አቋራጭ ትራንስፖርትና ከክልል ወደ ክልል የሚደረግ የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ መወሰኑን አመልክቷል።

    የአሰላ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የባጃጆች እና ታክሲዎች እንቅስቃሴ እንዲቆም መወሰኑም ተነግሯል።

    የደቡብ ክልልን የሚያቋርጡ ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪን ሳያራግፉና ሳይጭኑ እንዲያልፉ የተፈቀደ ሲሆን በክልሉ ውስጥ በዞኖችና በወረዳዎች መካከል ያለው የትራንስፖርት ስምሪት ግን እንዲቋረጥ ተወስኗል።

    በአሰላ ከተማ ከገጠር ወደ ከተማ እና ከከተማዋ ወደ ገጠር በታክሲዎች ሲሰጥ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡ ነው የተገለፀው።

    የደቡብ ክልል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ግብረ ኃይል ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመለሱ ተማሪዎችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ግን በልዩ ሁኔታ የሚፈቀድላቸው እንደሚሆን ተገልጿል።

    ግብረ ኃይሉ በተጨማሪም የከተማ ታክሲዎችና ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች የሚያሳፍሩት ሰው መጠን ላይ ገደብ አስቀምጧል።

  6. ሰበር, በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 23 መድረሱን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናገሩ

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት አስቸኳይ መልዕክት እንደተናገሩት ከተመረመሩ ከ800 በላይ ሰዎች መካከል 23 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በከተሞች አካባቢ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና ንክኪን ማስወገድ በአመርቂ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አክለውም ዜጎች ንጽህናቸውን እንዲጠብቁና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን እንዲተገብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ባለፉት ሳምንታት የኮቪድ-19 ወረርሽንን ለመግታት የበኩላቸውን ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  7. የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን መልዕክት

    የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ምንም እንኳን አፍሪካ እንደ አህጉር ቫይረሱ ሲመጣ ቢዘገይም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መዛመቱን ለመታገል ምንም ዝግጅት ያላደረገችውን አህጉር ክፉኛእንደሚመታት ሳይታለም የተፈታነው ብለዋል።

    ኤለን ጆንሰን መዛመቱን ለመቀነስ አብረን፣ ተደጋግፈን ልንሰራ ይገባል በማለት፤ ለቫይረሱ መዛመት ያለው ምላሽ ከእስያ ወደ አውሮፓ እንዲሁም ወደ አሜሪካ ስህተቶች ተፈፅሟል ብለዋል።

    ጊዜ ባክኗል፣ መረጃ ተደብቋል እንዲሁም በማይሆን መንገድ ተላልፏል። እምነትም ተሰብሯል ብለዋል።

    የዚህን ዘገባ ዝርዝር ሙሉ ውን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :አለም ከኢቦላ እልህ አስጨራሽ ትግል ሊማር ይገባል

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ እስከ ሠኔ ድረስ ከኮሮና ታገገምላች አሉ

    ትራምፕ ዋይት ሐውስ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግብረ ኃይል ሥራዎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፌደራል የኮሮናቫይረስ መመሪያ መሰረት የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችሉት አካላዊ እርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉ እርምጃዎች እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ እንደሚቆዩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ እነዚህ እርምጃዎች በፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በሚከበረው የፋሲካ በዓል ሰሞን ሊላሉ እንደሚችሉ ገልጸው ነበር።

    ነገር ግን አሁን ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት "በሁለት ሳምንት ውስጥ በበሽታው ምክንያት የሚያጋጥመው ሞት ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችልበት እድል አለ" ብለዋል።

    ትራምፕ ትናንት ዋይት ሐውስ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግብረ ኃይል ሥራዎችን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ አካላዊ እርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉት በሽታውን የመከላከያ መንገዶች "በአሸናፊነት ለመውጣት ዘዴ ነው" ብለዋል።

    የዚህን ዜና ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ እስከ ሠኔ ድረስ ከኮሮና ታገገምላች አሉ

  9. ሊቢያና ሌሎች አገራት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት እስረኞችን ፈቱ

    በሊቢያ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ስምንት ሰዎች ይገኛሉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሊቢያ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ስምንት ሰዎች ይገኛሉ

    ሊቢያ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት በሚል በርካታ እስረኞችን መልቀቋ ተገለፀ።

    ዓለም አቀፍ መንግሥታት እውቅና ያለው የትሪፖሊው መንግሥት 400 እስረኞችን መልቀቁ ታውቋል።

    ሳኡዲ አረቢያም አነስተኛ የእስር ጊዜ ተፈርዶባቸው የነበሩ 250 እስረኞችን መልቀቋ ተነግሯል።

    ባህሬን፣ ግብጽና ሶሪያም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በኢራን እስረኞች ከሁለት ማረሚያ ቤቶች ሰብረው መውጣታቸው ቢገለፅም ተጨማሪ ታራሚዎችን መልቀቋ ታውቋል።

  10. በኤርትራ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች 12 ደረሱ

    ኤርትራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኤርትራ ስድስት ተጨማሪ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን በማሳወቋ በአገሯ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር 12 ደረሰ።

    የኤርትራ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀው ተጨማሪዎቹ ስድስት ሰዎች ወደ አገሪቱ የሚደረጉ በረራዎች ከመታገዳቸው ቀደም ብለው የገቡ ናቸው።

    ከስድስቱ አምስቱ ከ32 እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው ተብሏል።

    አራቱ ወደ ኤርትራ ሲገቡ የበሽታው ምልክት ስለታየባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገው የነበሩ ሲሆን ሁለቱ ግን በምርመራው ወቅት ምልክት ስላልታየባቸው ወደ ቤታቸው የሄዱ ሲሆን፤ ሁሉም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች አስፈላጊው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን መሆኑም ተገልጿል።

    ኤርትራ ስድስት በሽታው ያለባቸው ሰዎችን ባለፈው ሳምንት ማግኘቷን ተከትሎ ትምህርት ቤቶችና የሕዝብ ትራንስፖርት አገግሎቶችን በመዝጋት ዓለም አቀፍ በረራዎችን አግዳለች።

  11. ወደ አማራ ክልል ማንኛውም ተሽከርካሪ እንዳይገባ ታገደ

    የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ

    የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media

    ከትናንት ሌሊት ስድስት ሰዓት ጀምሮ ወደ አማራ ክልል የሚገቡ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደማይኖሩ የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

    የአማራ ክልል የኮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ኮማንድ ፖስት ከአገሪቱ ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚመጡ ማንኛውም አይነት የሕዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች መከልከላቸው የተገለፀው ትናንት አመሻሽ ላይ ነበር።

    ከተለያዩ ዩኒቪርስቲዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እየሄዱ የሚገኙ የክልሉ ተማሪዎች ግን በልዩ ሁኔታ እንደሚገቡ ኮማንድ ፖስቱ ማስታወቁ ተገልጿል።

    ይህንንም እንዲያስፈጽሙ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት ትዕዛዝ መሰጠቱ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

    ይህንን እርምጃ በተመለከተ ያነጋግርነው አንድ አሽከካሪ እንደገለጸው ባለፉት ቀናት ወደ ክልሉ የሚመጡ የተጓዦች ቁጥር መቀነሱን ጠቁሟል።

    ዛሬ ጠዋት ወደ ባህር ዳር ከሚያደርገው ጉዞ ቀድሞ የኮማንድ ፖስቱን ውሳኔ እንደሰማ የተናገረው አሽከርካሪው ከገንዘብ ይልቅ “ጤና ይበልጥብኛል፤ ከማን በሽታው እንደሚይዘኝ አላውቅም” ሲል ውሳኔው ተገቢ መሆኑን ገልጿል።

    በዚህም ሳቢያ ዛሬ ወደ ባህር ዳር ያለምንም ተሳፋሪ ተጉዞ መግባቱን አስታውቆ መኪናውን አሳጥቦ ለማቆም መወሰኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

    የተሳቢ የጭነት መኪና አሽርከርካሪ የሆነው አቶ ኃይሌ አትንኩት በበኩሉ አብዛኛውን ጊዜ የሚሰራው ባህር ዳር፣ ደሴ፣ መቀሌና ሽሬ መስመሮች ላይ መሆኑን ጠቅሶ፤ እስካሁን ሥራ አቁሙ እንዳላቆሙና ትግራይ ሲገበባ የሙቀት ልኬት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

  12. በኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁት አስሩ የዓለማችን አገራት እነማን ናቸው?

    ሁለት አውስትራሊያውያን የአፍና የአፍንጫ መሸፈና አድርገው

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    በመላው ዓለም 722,289 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተነግሯል። ከእነዚህም መካከል 151,901 ያህሉ ሙሉ በሙሉ መዳናቸው ታውቋል። በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተደራጀውን መረጃ እናካፍላችሁ።

    በአሜሪካ 142,106 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 4,767 ደግሞ ድነዋል። በጣሊያን ደግሞ 97,689 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ 13,030 ደግሞ መዳናቸው ታውቋል።

    • ቻይና 82,122 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 75,583 ደግሞ ድነዋል
    • ስፔን 80,110 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 14,709 ደግሞ ድነዋል
    • ጀርመን 62,095 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 9,211 ደግሞ ድነዋል
    • ፈረንሳይ 40,723 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 7,226 ደግሞ ድነዋል
    • ኢራን38,309 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 12,391 ደግሞ ድነዋል
    • ዩናይትድ ኪንግደም ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 19,784 151 ደግሞ ድነዋል
    • ስዊዘርላንድ 14,829 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 1,595 ደግሞ ድነዋል
    • ኔዘርላንድስ 10,930 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 253 ደግሞ ድነዋል
  13. ናይጄሪያ ዋና ዋና ከተሞቿን ለሁለት ሳምንታት እንዲዘጉ አወጀች

    የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ

    የፎቶው ባለመብት, Muhammadu Buhari twitter page

    የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ

    የኮሮናቫይረስ መዛመትን ተከትሎ የተለያዩ አገራት እርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን ናይጄሪያ ዋና ዋና ከተሞቿን ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉ አውጃለች። ይህም ያለውን የቫይረሱን መዛመት ይቀንሰዋልም ተብሎ ታስቧል።

    የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ እንደተናገሩት የቫይረሱን መዛመት ለመቀነስ ዋና መዲናዋን አቡጃን ጨምሮ ሌጎስ እንዲዘጉ ተወስነዋል።

    በዚህም መሰረት መግባትም ሆነ መውጣት የማይቻልባቸው ከተሞች ይሆናሉ።

    የከተሞቹ መዘጋት ዛሬ ረፋዱ ላይ የሚጀመር ሲሆን ሌጎስን የምታዋስናት የኦጉን ግዛትም ከሚዘጉ ከተሞች መካከል ተካትታለች።

    ይህም ያለ ሥራ ለአስራ አራት ቀናት እንሚደሚቆይ ፕሬዚዳንቱ በእወጃቸው አስታውቀዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡ በቤቱ እንዲቆይ፣ የንግድ ማዕከላትም ሆኑ መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት የሚከፈቱት አስፈላጊ አገልግሎት ተብለው የተወሰኑት ለምሳሌ የምግብ ሽያጭ የሚያቀርቡ፣ የህክምና ማዕከላት የመሳሰሉት ናቸው።

    ይህንንም ለማሳለጥ 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል።

    በናይጄሪያ 97 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን አንድ ሰውም ሞቷል። አፍሪካ እንደ አውሮፓና እንደተቀሩት አህጉራት በቫይረሱ ክፉኛ ባትጠቃም የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ሆነ የሟቾች ቁጥር መጨመር አሳሳቢ ነው ተብሏል።

  14. አካላዊ እርቀትን መጠበቅና ራስን ለይቶ ማቆየት በኢትዮጵያ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል?

    በኢትዮጵያ በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቫይረሱን መዛመትም ለመቀነስ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አካላዊ እርቀትን መጠበቅና ራስን ለይቶ ማቆየት ተግባራዊ እንዲደርጉ በመከረው መሰረት የተለያዩ መንግሥታትም ሆኑ ሕዝቦች እሱን እየተከተሉ ይገኛሉ።

    ምንም እንኳን በአውሮፓና በእስያ ይህ እውን ቢሆንም በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፈታኝ ነው እየተባለ ነው።

    የማህበራዊ ትስስሩ ጠንካራ በሆነበት፣ ብዙዎች የእለት ጉርስ ለማግኘት በሚዳክሩባት፣ የውሃ አቅርቦቱ ዝቅተኛ በሆነበት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በተጨናነቀበት እንዲሁም የመፀዳጃ ቦታን ብዙዎች የሚጋሩበት ወይም መፀዳጃ በሌለባቸው አገር ይህ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል እያሉም ነው?

    ሰዎች ተዳልበውና ተደራርበው በሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም፣ የቤት ኪራይ በማይቀመስባት አዲስ አበባ የተለየ ድጎማ ከሌለ እንዴት ሰው ሥራውን ሊያቋርጥ ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

    በተለይም ብዙው ሕዝብ ኢመደበኛ በሆነ ሥራ ከመሰማራቱ አንፃር ቤቱ መቀመጥ እንዴት ምርጫ ይሆናል? የሚመለከተውስ አካል ለዚህ መፍትሄ ለማበጀት ምን እያደረገ ነው? እናንተስ አካላዊ እርቀትን በመጠበቅ፣ ራስን ለይቶ በማቆየት፣ ቤት መቀመጥ የመሳሰሉት በኢትዮጵያ እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ አስተያቶቻችሁን አጋሩን።

  15. በኮቪድ-19 ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር ያስመዘገቡት 10 አገራት እነማን ናቸው?

    የስፔን የጤና ባለሙያዎች ተቃቅፈው ሲላቀሱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በዓለማችን ላይ እስካሁን ድረስ 33,984 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸው ተነግሯል።

    ይህንን ቁጥር በአገራት ዘርዝረን ካየነው በጣሊያን 10,779 ሰዎች ሲሞቱ በስፔን ደግሞ 6,803 መሞታቸው ተመዝግቧል።

    • ቻይና -3,308፣
    • ኢራን- 2,640
    • ፈረንሳይ- 2,611
    • አሜሪካ -2,493
    • ዩናይትድ ኪንግደም -1,231
    • ኔዘርላንድስ -772
    • ጀርመን- 541እና
    • ቤልጂየም -431ሞቶች ተመዝግበዋል።

    መረጃው የተጠናቀረው በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ነው።

  16. ኢትዮጵያ ውስት በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው መዳናቸው ተገለጸ

    በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ህክምናና ለይቶ ማቆያ ማዕከል የሚሰሩ ሕክምና ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, HAKIM FB

    ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ 21 ሰዎች መካከል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው መዳናቸው ተገለጸ።

    ወረርሽኙ በአገሪቱ ውስጥ መከሰቱ ታውቆ ይፋ ከተደረገ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የህሙማኑ ቁጥሩ 21 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ከእነዚህ ውስጥም ሁለት ሰዎች የሚሰጠውን ህክምና በአግባቡ ተከታትለው ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ የዳኑ መሆኑ ተገልጾ፤ ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጠቅሰዋል።

    የዚህን ዜና ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡ ሁለት ሰዎች ከኮቪድ-19 መዳናቸው ተገለፀ