
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, በቦሌ አየር ማረፊያ ለተጓዞች የጤና ምረመራ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎችበምሥራቅ አፍሪካ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ትናንት በሩዋንዳ 10 ሰዎች በቨይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 70 አድርሶታል።
ትናንት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል 6ቱ ከዱባይ፣ ሁለቱ ከደቡብ አፍሪካ፣ አንድ ከናይጀሪያ እና ሌላኛው በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገራት በቅርቡ ወደ አገሪቷ የገቡ መሆናቸውን የአገሪቷ የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቅሰው ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሩዋንዳ ለ14 ቀን በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች።
ኤርትራ ትናነት 6 ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን አስታውቃለች።
ስድስቱ ሰዎች አገሪቷ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከማገዷ አስቀድሞ ወደ አገሪቷ የገቡ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ከእነዚህ መካካል 5ቱ እድሜያቸው ከ32- 60 የሚሆኑ ሴቶች ሲሆኑ ሁሉም ሕሙማን የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።
አገሪቷ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች ማንኛውንም የሕዝብ የትራንስፖርት አግልግሎትን አግዳለች።
ከዚህም በተጨማሪ ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ላይ መሰብሰብን ከልክላለች።
ኢትዮጵያ ትናንት አምስት ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን አስታውቃለች፤ ዛሬም ሁለት ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም ቁጥሩን 23 አድርሶታል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ነው።
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ተግባራዊነቱን ለማስፈጸም ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድ ሰው መገደሉ ይታወሳል።
የአማራ፣ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል መንግሥታትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ወሳኔዎችን አሳልፈዋል።
ኬንያ ትናንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ38 ወደ 42 ከፍ ብሏል፤ ዛሬም ተጨማሪ 8 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች፡። በዚህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 50 ደርሷል።
ትንናት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች የኬንያ፣ አሜሪካ፣፣ ካሜሩን እና ቡርኪናፋሶ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ኡጋንዳ 33 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቃለች።
በታንዛኒያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ደርሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አለመኖራቸው ተገልጿል።