ጣሊያን ሪከርድ የሆነውን 969 የሟቾች ቁጥር በ24 ሰዓት አስመዘገበች

በዓለማችን ላይ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። እስካሁን ድረስ ባለው ይፋዊ መረጃ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጃችንን በሳሙናና በውሃ በሚገባ መታጠብ ቫይረሱ እንዳይዘን ከሚረዱ መከላከያዎች መካከል መሆናቸውን አሁንም ባለሙያዎች በአጽንኦት ይናገራሉ። ቢቢሲ አማርኛ ስለቫይረሱ በዓለማችን ላይ ያለውን ወቅታዊ መረጃ በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገፁ ላይ ያቀርባል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቻይና ለጃፓን 50ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ላከች

    የጃፓኗ ቶዮካዋ ከተማ በቻይና ለምትገኘው ዢንዉ እህት ከተማ ቻይና በኮሮናቫይረስ ተፈትራ ተይዛ በነበረችበረት ወቅት አለሁልሽ በማለት 4500 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ልካ ነበር።

    ነገር ግን ቶዮካዋ አሁን በጃፓን የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ሲመጣ እጅ አጠራት።

    ይኼኔ እህት ከተማዋ ዢንዉ የቶዮካዋን ብድር በአስር እጥፍ አድርጋ መልሳለች።

    50 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የላከች ሲሆን "የክፉ ቀን ደራሻችንን ብድር መክፈል እንፈልጋለን" ብለዋል የከተማዋ ባለስልጣን።

  2. በሶሪያ የስደተኞች ካምፕ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት አንዣቧል

    የሕክምና ባለሙያዎች፣ የእርዳታ ሰጭ ድርጅት ሠራተኞች፣ የተባበሩት መንግሥታት በሰሜናዊ ምዕራብ ሶሪያ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።

    እስካሁን ድረስ አንድም ሰው በቫይረሱ መያዙ ያልተረጋገጠ ሲሆን፣ ቢከሰት ግን እስከ 100ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

    አክለውም ለመጠለያ ጣብያው በፍጥነት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

  3. ሴንጋፖር አካላዊ እርቀትን የማይጠብቁ ሰዎችን በገንዘብና በእስር ልትቀጣ ነው

    ሴንጋፖር የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚመከሩት መንገዶች አንዱ የሆነውን በሰዎች መካከል መኖር ያለበትን አካላዊ እርቀት መጠበቅን ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎችን በገንዘብና በእስር ልትቀጣ ነው።

    ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ተግባራዊ በተደረገው በዚህ ውሳኔ መሰረት አካላዊ እርቀታቸውን ሳይጠብቁ የተገኙ ሰዎች እስከ 7 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት፣ አስከ ስድስት ወራት የሚደርስ እስር ወይም በሁለቱም ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል።

    መንግሥት ከዚህ በተጨማሪ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ እንደሚያደርግም እየተነገረ ነው፤ ይህም ከአንድ ሜትር ባነሰ እርቀት ላይ ሆነው፣ ሆነ ብለው የሚያስሉ ሰዎች ደንብ እንደጣሱ ተቆጥረው ሊቀጡ እንደሚችሉም ተነግሯል።

    የዚህን ዘገባ ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

  4. የካሜሮን አማጺያን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል የተኩስ አቁም አወጁ

    በካሜሮን የሚገኙ ተገንጣይ ቡድኖች ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ በሚል ለሁለት ሳምንት ያህል መሳሪያቸውን ለማስቀመጥ ተስማሙ።

    የምዕራባዊ ካሜሮን መከላከያ ኃይል የሚባለው የአማፂ ቡድን እንዳለው የተኩስ አቁሙ ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፤ ይህንንም ”የመልካም ፈቃድ ማሳያ” ብለውታል።

    በካሜሮን በእርስ በእርስ ጦርነቱ ምከንያት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎች የኮቪድ-19 ምርመራ ማግኘት አይችሉም የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

    ካሜሮን ውስጥ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ባሉበት አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ በርካታ አማፂያን መካከል ይህ ቡድን ብቻ ነው የተኩስ አቁም ለማድረግ የፈቀደው።

    እነዚህ ተዋጊዎች በአብዛኛው ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆነው አካባቢ ተገለናል ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።

    ተገንጣይ ቡድኖቹ ለሦስት ዓመታት ከካሜሮን መንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበረ ሲሆን ተገንጥለው የራሳቸውን “አምባዞኒያ” የተሰኘ ግዛት ለመመስረት ይፈልጋሉ።

    እስካሁን አምባዞኒያ መከላከያ ኃይል የተሰኘውና ትልቁ የአማፂ ቡድን የተኩስ አቁም ያድርግ አያድርግ የታወቀ ነገር የለም።

    በካሜሮን አማፂያኑን ወደ ውይይት እንዲመጡ የሚያግባባው ቡድን አባል የሆኑት አሌክሳንደር ሌቢስኪንድ ለቢቢሲ “ይህ ቡድን ብቻ ነው አሻፈረኝ ያለው” ሲሉ ተናግረዋል።

    አክለውም በቅርቡ የተኩስ አቁሙን ይቀላቀላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

    ይህ የተኩስ አቁም ዓመታት የፈጀውን የካሜሮናዊያን ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመው እንደሆን የተባለ ነገር የለም።

  5. የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ስለኮሮናቫይረስ ሙዚቃ ለቀቁ

    የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ የኮሮናቫይረስን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር ሙዚቃ አቀነቀኑ።

    የቀድሞው ኮከብ የእግር ኳስ ተጫዋች ፕሬዝዳንት ዊሃ በዋና ከተማዋ ፍሪታውን ውስጥ የራሳቸው የሆነ የቀረጻ ስቱዲዮ አላቸው።

    ፕሬዝዳንቱ አዲሱን ነጠላ ዜማቸውን መስራት የጀመሩት ወረርሽኙ ላይቤሪያ ውስጥ ከመከሰቱ ቀደም ብለው እንደሆነ ቃል አቀባያቸው ለጋርዲያን ተናግረዋል።

    ላይቤሪያ ውስጥ እስካሁን ሦስት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ብቻ ናቸው የተገኙት።

    በሙዚቃው ላይ ፕሬዝዳንት ዊሃ ከመዝፈን ይልቅ ንግግር የሚያደርጉ የሚመስል ሲሆን፤ የሙዚቃው ግጥምም የኮሮናቫይረስን ስለመከላከልና ስለምክቶቹ በሚገልጽ መልዕክት የተሞላ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ በሙዚቃቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተው የመከሩት ከበሽታው እራስን ለመከላከል ዋነኛው መንገድ እጅን መታጠብ እንደሆነ ነው።

    የፕሬዝዳንቱ ሙዚቃ ወደ ስድስት ደቂቃ የሚጠጋ ሲሆን የመንፈሳዊ ሕብረ ዝማሬ ቡድንም አጅቧቸዋል።

  6. አሜሪካ ኮቪድ-19 ባለባቸው ሰዎች ቁጥር ቻይናን በለጠች

    በአሁን ሰዓት አሜሪካ ከማንኛውም አገር በበለጠ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት አገር ሆናለች።

    በአገሪቱ በአጠቃላይ ከ85 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ ይህ ቁጥር የቻይናውን 81,782 እንዲሁም የጣሊያኑን 80,589 በልጦ ተገኝቷል።

    በአሜሪካ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ግን 1300 ብቻ ሲሆን በቻይና 3,291 እንዲሁም በጣሊያን 8,215 መሆኑ ይታወቃል።

    ከዚህ በፊት በፍጥነት ወደ ሥራ እንመለሳለን ሲሉ ተናግረው የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ቁጥሩ መጨመር ተጠይቀው ሲመልሱ “ይህ የሚያመለከተው በርካታ ምርመራ እያደረግን መሆኑን ነው” ሲሉ መልሰዋል።

    ትራምፕ አክለውም ቤይጂንግ ይፋ ያደረገቸችው የታማሚዎች ቁጥር ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ “በቻይና ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆኖ አይታወቅም” ሲሉ ገልፀዋል።

  7. በደቡብ አፍሪካ ለ3 ሳምንታት የሚቆየው ከቤት ያለመውጣት እገዳ ተጀመረ

    የደቡብ አፍሪካ የጸጥታ ኃይሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሦስት ሳምንታት በመላው አገሪቱ የተደነገገውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ።

    በደቡብ አፍሪካ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ካልሆነ በስተቀር መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ይህንንም እገዳ የአገሪቱ ጦር ኃይልና ፖሊስ ሠራዊት አባለት ተሰማርተው ተግባራዊ መደረጉን እየተቆጣጠሩ መሆናቸው ተነግሯል።

    ትናንት ዕኩለ ሌሊት ላይ እገዳው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ነዋሪዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለመሸመት ከመደብሮች ደጃፍ ላይ ረጃጅም ሰልፎች ሰርተው ታይተዋል።

    ደቡብ አፍሪካ እስካሁን 927 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ይህም በአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ነው። እስካሁን ግን በበሽታው የሞተ አንድም ሰው የለም።

    ሐሙስ አመሻሹ ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ ጦር ሰፈር ተገኝተው ወታደሮቹ ከመሰማራታቸው በፊት ጉብኝት አድርገው ነበር።

    "የማሰማራችሁ ሕዝባችንን ከኮሮናቫይረስ እንድትከላከሉት ነው” ሲሉ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ለወታደሮቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    በክልከላው ጊዜ የምግብ መሸጫ መደብሮች ክፍት የሚሆኑ ሲሆን የመጠጥ መሸጫዎች ግን ዝግ እንዲሆኑ ታዘዋል። የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴሌ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በእገዳው ጊዜ ተረጋግተው በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ መክረዋል።