ጣሊያን ሪከርድ የሆነውን 969 የሟቾች ቁጥር በ24 ሰዓት አስመዘገበች

በዓለማችን ላይ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። እስካሁን ድረስ ባለው ይፋዊ መረጃ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጃችንን በሳሙናና በውሃ በሚገባ መታጠብ ቫይረሱ እንዳይዘን ከሚረዱ መከላከያዎች መካከል መሆናቸውን አሁንም ባለሙያዎች በአጽንኦት ይናገራሉ። ቢቢሲ አማርኛ ስለቫይረሱ በዓለማችን ላይ ያለውን ወቅታዊ መረጃ በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገፁ ላይ ያቀርባል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሰበር, ጣሊያን ሪከርድ የሆነውን 969 የሟቾች ቁጥር አስመዘገበች።

    ጣሊያን ሪከርድ የሆነውን 969 የሟቾች ቁጥር አስመዘገበች።

    ባለፉት 24 ሰዓታት 969 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

    ከከፍተኛ የሟቾች ቁጥር በተጨማሪ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ 4,401 ሰዎች ተገኝተዋል።

    በአጠቃላይ በጣሊያን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 80,589 ሲሆን የሞቱት ሰዎች ደግሞ 9,134 ደርሷል።

  2. ሕንድ በአንድ ሰው ቸልተኝነት 40ሺህ ሕዝብ ለይታ ለማቆየት ተገደደች

    የሕንድ ባለስልጣናት በአንድ ሰው ቸልተኝነት ምክንያት 40 ሺህ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባት መገደዳቸውን ተናገሩ።

    ይህ የ70 ዓመት አዛውንት በኮቪድ-19 ህይወቱ አልፏል።

    ግለሰቡ ወደ ጣሊያ እና ጀርመን ተጉዞ ወደ ሕንድ ከተመለሰ በኋላ ምልክቱ ቢታይበትም የመንግሥት ምክርን በቸልተኝነት በመተላለፍ እራሱን ወደ ለይቶ ማቆያ ሳያስገባ ቆይቷል።

    በሕንዷ ፑንጃብ በተካሄደና 10 ሺህ ሰዎች በተሳተፉበት ፌስቲቫል ላይም ተገኝቶ ነበር ተብሏል።

    ከግለሰቡ ሞት አንድ ሳምንት በኋላ 19 የቤተሰብ አባላቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

    የአካባቢው ባለስልጣናት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት 40 ሺህ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባት መገደዳቸውን ለቢቢሲ ፑንጃብ አገልግሎት ተናግረዋል።

  3. ኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 መድሃኒት እያዘጋጀሁ ነው አለች

    ኢትዮጵያ የአገር በቀል የባህል ህክምና ከዘመናዊ ጋር በማጣመር ለኮቪድ-19 መድሃኒት እያዘጋጀው ነው አለች።

    የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስን ለማከም የአገር በቀል እውቀት ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር በማቀናጀት የተሰራው መድሃኒት ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሂደቶችን አልፏል ብሏል።

    የመድሃኒቱ ዝግጅት ሲጠናቀቅ በጤና ሚኒስቴርና በኢኖቬሽንና ቴክኖሌጅ ሚኒስቴር በኩል ይፋ ይሆናል ተብሏል።

  4. በኮቪድ-19 ስርጭት የኮንዶም እጥረት እንዳያጋጥም ተሰግቷል

    ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ የኮንዶም እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

    የሥጋቱ ምንጭም የዓለማችን ሁለቱ ግዙፍ ኮንዶም አምራቾች በወረርሽኙ ስርጭት ምክንያት ኮንዶም ማምረት በማቆማቸው ነው።

    በማሌዢያ የሚገኙት የካሬክስ ቤርሃድ ሁለት ፋብሪካዎች ምርት ካቆሙ 10 ቀናት ማለፋቸውን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ መከፋፈል የነበረባቸው 100 ሚሊዮን ኮንዶሞች ሳይመረቱ ቀርተዋል ሲሉ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጎህ ሚአህ ኪዓት ለሬውተርስ ተናግረዋል።

    የዓለም 20 በመቶ የኮንዶም ፍላጎት የሚያቀርበው ፋብሪክ የማሌዢያ መንግሥት ሥራውን እንዲያከናውን ልዩ ፍቃድ እንዲሰጠው እየጠየቀ መሆኑ ተነግሯል።

    ኮንዶም አምራቹ ካሬክስ፤ ምርቶቹን ለተባበሩት መንግሥታት ፖፑሌሽን ፈንድ እና ዱሬክስ ያቀርባል።

    የማሌዢያ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ መከልከሉ ይታወቃል።

  5. ሰበር, የብሪታኒያው የጤና ሚንስትርም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ

    የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው በኋላ የጤና ሚንስትሩም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጠ።

    ማት ሃንኮክ በቫይረሱ መያዛቸው እና እራሳቸውን በመኖሪያ ቤታቸው አግልለው እንደሚገኙ ተነግሯል።

    ቀደም ሲል የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ተነግሯል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጽህፈት ቤታቸው ነበር ዛሬ ያስታወቀው።

    ከዚህ ቀደም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዌልሱ ልዑል፤ የንግሥቷ የመጀመሪያ ልጅ ቻርለስ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።

    በአሁኑ ወቅት የ71 ዓመቱ ልዑል ቻርልስ ቀለል ያሉ የበሽታው ምልክቶች እየታዩባቸው ቢሆንም "በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ሲል ቃል አቀባያቸው አሳውቋል።

  6. የጠቅላይ ሚንስትሩ እርምጃ በሽታውንና ኢኮኖሚውን በተመለከተ

    * የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 72 መዳረሻዎች እንዲሰረዙ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

    * ጠቅላይ ሚንስትሩ በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የሚገኙት ሰዎች በቀን በአማካይ ከ50 ያነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

    * ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ተወስኗል።

    * ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ማኅበራዊ እርቀት በሚፈለገው መጠን እየተጠበቀ አይደለም ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያውን ኃላፊነት ስሜት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    * የሐይማኖት ተቋማትም ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በሕገ-መንግሥቱ መሠረት መንግሥት የሐይማኖት ተቋማትን የመዝጋት ስልጣን እንዳለው አስታውሰው፤ የኃይማኖት ተቋማት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መንግሥትን ወደ አስገዳጅ እርምጃ ከመውሰድ እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

    * ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁም ጥሪ ቀርቧል።

    * በአዲስ አበባ 134 ማቆያ ቦታዎች እና 44ሺህ አልጋ መያዝ የሚችሉ ቦታዎች መዝጋጀታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። ከተለዩት ቦታዎች መካከል የሚሊኒየም አዳራሽን አንዱ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል።

    * 5 ቢሊየን ብር ከገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚንስቴር ለእቃ ግዢ፣ ለቦታ እና ለምግብ አቅርቦት የሚሆን ገንዘብ ተዘጋጅቷል

    * ከብሔራዊ ባንክ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል። ባንኮቹም የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር የሚሰጡ ይሆናል።

  7. የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ራሳቸውን ለይተው ተቀመጡ

    የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኮሮናቫይረስ ስጋት ራሳቸውን ለይተው መቀመጣቸውን አስታወቁ።

    ዋና ጸሐፊው ከዚህ ውሳኔ የደረሱት የእርሳቸው ባልደረባ የሆኑት ግለሰብ በኮቪድ-19 መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

    የፈረንሳዩ የዜና ወኪል በበኩሉ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የዋና ጸሐፊው ባልደረባ ሞሪሼሲያዊው የ72 ዓመት ሰው መሆኑን ጠቅሷል።

    ዛሬ ረፋዱን የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር አዲስ በቫይረሱ የተያዙ አራት ሰዎችን ይፋ ሲያደርግ የ72 ዓመቱ ሞሪሼሲያዊ እንደሚገኝበት መጥቀሱ ይታወሳል።

  8. የአዲስ አበባ ፖሊስ ፔንሲዮኖችን ጨምሮ ሰዎች ተሰብሰበው የተገኙባቸውን የንግድ ቤቶችን መዝጋቱን አስታወቀ

    የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ፔንሲዮኖችን ጨምሮ ሰዎች በብዛት ተሰብሰበው የተገኙባቸውን ከ4ሺህ በላይ የንግድ ቤቶችን መዝጋቱን አስታወቀ።

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከመጋቢት 12 እስከ መጋቢት 15 ባሉት ቀናት በመዲናዋ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው የተገኙባቸውን የንግድ ቤቶች መዝጋቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በተለይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የመንግሥት ውሳኔ ተላልፈው የተገኙ 4318 የንግድ ቤቶች ዝግ ተደርገዋል።

    እንደ ኮማንደር ፋሲካ ከሆነ እንዲዘጉ የተደረጉት የንግድ ቤቶች ዝርዝር፡

    • 10 ፔንሲዮኖች
    • 344 ጭፈራ ቤቶች
    • 437 አረቄ ቤቶች
    • 2363 ግሪሰሪ
    • 799 ሆቴል ቤቶች
    • 142 ጠጅ ቤቶች
    • 162 ፑል መጫዎቻ ቤቶች
    • 40 ቪዲዮ እና ጫት ቤቶች
    • 21 ሺሻ ቤቶች
  9. ሰበር, የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮቪድ-19 ተያዙ

    የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀላል የሚባል ምልክት እንደታየባቸው የገለፀው መግለጫው መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይቆያሉ ተብሏል።

    የጽ/ቤታቸው ቃል አቀባይ አክለውም ራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።

    "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርመራ እንዲያደርጉ ከሐኪም በተሰጣቸው የግል ምክር መሰረት ነው የተመረመሩት" ሲል ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

    በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው የኮሮናቫይረስ የፈጠረውን ቀውስ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት በመምራት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቀለል ያሉ ምልክቶችን በማየቴ ባደረኩት ምርመራ ቫይረሱ ተገኝቶብኛል። አሁን እራሴን አግልዬ የምገኝ ቢሆንም ነገር ግን መንግሥት በሽታውን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት እየመራሁ እቀጥላለሁ።

    "በጋራ ይህንን በሽታ እናሸንፈዋለን" ብለዋል።

    በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እስካሁን ከ11,600 በላይ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ሲኖሩ 578 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዌልሱ ልዑል ቻርለስ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።

    በአሁኑ ወቅት የ71 ዓመቱ ልዑል ቻርልስ ቀለል ያሉ የበሽታው ምልክቶች እየታዩባቸው ቢሆንም "በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ሲል ቃል አቀባያቸው አሳውቋል።

  10. ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀረበ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 በመድረሱ እና ቫይረሱ የበለጠ እንዳይዛመት ለመግታት ተጨማሪ መመሪያዎችን ይፋ አደረጉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እነዚህን ውሳኔዎች ያሳለፉት ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ከተወያዩ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

    በዚህም መሰረት ዜጎች በየትኛውም ስፍራ የማኅበራዊ ርቀት መጠበቅን መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ በሚል ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

    የመግለጫውን ዝርዝር ለማንበብ ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለባንኮች ሊሰጥ ነው

  11. ስለኮሮናቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው - ፌደራል ፖሊስ

    ከዛሬ ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በማይተገብሩ ዜጎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ቫይረሱን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ ኮሚሽኑ እርምጃ እየወሰደ ነው።

    የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግሥት ዜጎች መጨባበጥ እንዲያቆሙ፣ እርቀትን እንዲያስጠብቁና ስብሰባ እንዲያቆሙ መመሪያ ቢያወጣም በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልፀዋል።

    የፌደራል ፖሊስ በቅድሚያ የመምከርና የማሳወቅ ሥራ ይሰራል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህም አልፎ ካልተተገበረ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

    ኮሚሽነሩ አክለውም ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ጦማሪያን ላይም እርምጃ ለመውሰድ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

  12. ሰበር, በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ አራት ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ አራት ተጨማሪ ሰዎች መገኛተቻውን ተከትሎ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ ስድስት መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከአራቱ ግለሰቦች መካከል አንዱ የ72 ዓመት ሞሪሸሳዊ ሲሆኑ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ከኮንጎ ብራዛቪል የተመለሱ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።

    ሌላ የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ61 ዓመት ኢትዮጵያዊ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ግለሰቡ ወደ ውጪ አገር ወጥተው ባያውቁም ከውጭ አገር ዜጋ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ተገልጿል።

    ሦስተኛዋ ታማሚ የ28 ዓመት ኢትዮጵያዊት ስትሆን በቅርቡ እስራኤል አገር ደርሳ የተመለሰች ናት ተብሏል።

    አራተኛዋ ታማሚ ምንም የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ የሌላት የ24 ዓመት ኢትዮጵያዊት መሆኗም ተገልጿል።

  13. የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት "ቫይረሱ ምርጫውን አያደናቅፍም" አሉ

    በታንዛኒያ በመጪው ጥቅምት ወር የሚደረገውንና ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ለሌላ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩበት አገር አቀፍ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደማይደናቀፍ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዜጎች ሥራ የሚያቆሙበት ምከንያት የለም ማለታቸው ተዘግቧል።

    "ስራ መቋረጥ የለበትም፤ ለዚህም ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእቅዱ መሰረት እየሄደ ያለው" ማለታቸው ሲቲዝን ጋዜጣ ላይ ተዘግቧል።

    ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ በቤተ እምነቶችና መስጂዶች መሰባሰብ አይከለከልም፤ ምክንያቱም "ትክክለኛ ፈውስ ያለው እዚያ ነው" ብለው ነበር።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን ቢሉም አገሪቱ ግን በኮቪድ-19 የተያዘ የመጀመሪያውን ሰው እንዳገኘች ትምህርት ቤቶችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለሰላሳ ቀናት አግዳለች።

    በታንዛኒያ እስካሁን ድረስ 13 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

  14. በደቡብ አፍሪካ ሁለት ሰዎች በኮሮና ምክንያት ሞቱ

    በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስትሩ ገለፁ።

    ዝዌልኒ ማክሄዚ እንዳሉት ሁለቱ ግለሰቦች የሞቱት በምዕራባዊ ኬፕታወን ሲሆን ግለሰቦቹ በሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ ነበር።

    በደቡብ አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ተጨማሪ ሰዎች መኖር አለመኖራቸውን መግለጫ እንደሚሰጡ የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ማክሄዚ ጨምረው አስታውቀዋል።

    በደቡብ አፍሪካ ለሶስት ሳምንት የሚቆይ የመንቀሳቀስ ገደብ የተጣለ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎች ይህንኑ እንዲያስፈጽሙ ተሰማርተዋል።

    እገዳውን ጥሶ የተገኘ የስድስት ወር እስራት ወይንም ከባድ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል።

  15. አሜሪካና ቻይና ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

    ዛሬ ማለዳ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዢንፒንግ የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ አስታውቀው ነበር።

    ትራምፕ ስለ ስልክ ምልልሳቸው ምንም ባይሉም የቻይና መገናኛ ብዙኀን ግን ቻይናና አሜሪካ "ቫይረሱን ለመዋጋት በአንድ ማበር እንዳለባቸው" መነጋገራቸውን ዘግበዋል።

    ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ፤ አገራቸው ቫይረሱን በመከላከል ረገድ አሜሪካንን ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን መናገራቸው ተዘግቧል።

    አክለውም አሜሪካ በቻይና የሚገኙ ቻይናውያንን ጤና ለመጠበቅ እንደምትሰራ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተደጋጋሚ ቤጂንግ የኮሮናቫይረስን በተመለከተ ግልጽነት ይጎድላታል ሲሉ ቢከሱም በዚህ የስልክ ምልልሳቸው ወቅት ቻይና ሁልጊዜም ስለወረርሽኙ ግልጽ መሆኗን መነጋገራቸው ተጠቅሷል።

    ቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተስፋፋባቸው በርካታ የአውሮፓ፣ የእስያና የአፍሪካ አገራት ድጋፏን መላኳ ይታወሳል።

  16. ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዴት ማስቆም አንችላለን?

    ስለኮሮናቫይረስ በማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ የማይነዛ ሐሰተኛ መረጃ የለም። የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች "የመረጃ ንጽህናችንን" እንድንጠብቅ ይመክራሉ።

    ግን እንዴት? ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲቆሙ ምን ማድረግ እንችላለን?

    • ቆም ብለው ያስቡ- ጥርጣሬ ከተሰማዎ እውነታውን ከሌላ ቦታ ያጣሩ
    • የመረጃውን ምንጭ ያጣሩ- ሐሰተኛ መረጃዎች እውነት እንዲመስሉ ተደርገው የሚቀርቡ በመሆናቸው የመረጃውን ምንጭ በደንብ ማጣራት ያስፈልጋል።
    • ስለመረጃው ምንጭ እርግጠኛ ካልሆኑ ለሌሎች አያጋሩ።
    • ስሜት ከተቀላቀለባቸው እና ወደ አንድ ወገን ካደሉ መልዕክቶች ይጠንቀቁ።
  17. ውሾች የኮሮናቫይረስን መለየት ይችሉ ይሆን?

    የኮሮናቫይረስን ለመለየትና ለመፈወስ ስለሚያችሉ ሙከራዎችና ምርምሮች ብዙ አንብበን ይሆናል።

    እንግሊዛዊያን የሰው ልጅ የቅርብ ጓደኛ የሆነው ውሻ ይረዳን ይሆን በሚል ምርምር እየሰሩ ነው።

    የብሪታኒያ በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመራማሪዎች ጋር በማበር ውሾች ቫይረሱን መለየት ይችሉ እንደሆን ለማወቅ እየሰራ ነው።

    ተመራማሪዎቹ የውሾች የማሽተት ብቃትን ተገን አድርገዋል።

    የምርምር ሥራው ላይ የሚሳተፉት የለንደኑና የዱርሃም ዩኒቨርስቲዎች ሲሆኑ ውሾች ከዚህ ቀደም ወባ አሽትተው መለየታቸውን በመጥቀስ ኮቪድ-19ንም ይለዩ እንደሆን እናያለን ብለዋል።

    የብሪታኒያ በጎ አድራጎት ድርጅት ከዚህ ቀደም ከካንሰር፣ ፓርኪንሰንና በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡ ኢንፌክሽኖች ታማሚዎችን ናሙና በመውሰድ ውሾቹ አነፍንፈው እንዲለዩ ማድረግ ችሏል ተብሏል።

    "ዓላማው ውሾች ማንኛውንም ሰው መለየት እንዲችሉ ነው። ምልክት የማያሳዩትን ሰዎችን ጨምሮ፤ መመርመር ያስፈልግ እንደሆን ይነግሩናል" ብለዋል የበጎ አድራጎቱ ድርጅት ኃላፊ ክሌር ገስት።

  18. በአሜሪካ የባህር ኃይል መርከብ ላይ ተጨማሪ ታማሚዎች ተገኙ

    በአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ላይ በተሰማሩ የባህር ኃይል አባላት ላይ የኮሮናቫይረስ በሽታ ክስተት ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ።

    አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ በውስጧ ካሉ አባላቷ መካከል ኮሮናቫይረስ መገኘቱን ይፋ በማድረግ የመጀመሪያዋ ስትሆን፤ አሁን የታማሚዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ሲኤንኤን የባህር ኃይል ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።

    በመጀመሪያ በሦስት መርከበኞች ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን አሁን ቁጥሩ 25 ደርሷል ተብሏል።

    በአሜሪካ ባህር ኃይል በኩል የወጣው መግለጫም ቁጥሩን ሳያመለክት “ዩኤስኤስ ቴዎዶር ሩዝቬልት በተባለችው መርከብ ላይ ተጨማሪ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል” ብሏል።

    በበሽታው የተያዙት ሰዎች ተለይተው የሚገኙ መሆኑንና መርከቧም እየተጸዳች መሆኑ ተነግሯል።

  19. ተማሪዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ መኪና ተገልብጦ የሰው ሕይወት አለፈ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን ለመግታት ትምህርት በመዘጋቱ ምክንያት ከዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ወደ ደቡብ ጎንደር ተማሪዎችን በምሽት ይዞ በመሄድ ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ የሰው ሕይወት አለፈ።

    አማራ መገናኛ ብዙኀን አንደዘገበው በአደጋው 2 ተማሪዎች ሲሞቱ 22 ተማሪዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

    አደጋው የደረሰው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ወረዳ ጢቅ የትኖራ ቀበሌ ላይ መሆኑም ተገልጿል።

    ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በደጀን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና እየተደረገላቸው ነው።

  20. ተመራማሪዎች ኮሮናቫይረስን በፍጥነት ለይቶ ማወቅ የሚያስችል መመርመሪያ ላይ እየሰሩ ነው

    ኮቪድ-19ን በፍጥነት መርምሮ ማወቅ የሚቻልበትን መንገድ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ተጀምሯል።

    በሲንጋፖር የሚገኙ ተመራማሪዎች አንድ ሰው በኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ከተያዘ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መለየት የሚያስችል መመርመሪያ ሰርተናል እያሉ ነው።

    ይህንን የምርምር ውጤት ለማረጋገጥ በአንድ ወር ውስጥ ለሚመለከተው አካል እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።

    ነገር ግን ይህ የምርምር ሥራቸው ከዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያ ፉክክር ገጥሞታል።

    ሞሎጂክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለቤተሙከራዎች የላከው የመጀመሪያ የሙከራ መሳሪያው፤ መመርመሪያው በሽታውን በአስር ደቂቃ ውስጥ መለየት የሚያስችል ነው ተብሏል።

    አክለውም የአንዱ መመርመሪያ ዋጋ አንድ ዶላር (32 በር ገደማ) መሆኑን ገልፀው የሙከራ ጊዜውን ካለፈ ሰኔ ላይ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

    የጀርመን ኩባንያው ቦሽ ደግሞ ከሁለት ሰዓት ከግማሽ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መመርመር የሚያስችል መሳሪያ ሰርቻለሁ እያለ ነው። ይህ መሳሪያ በጀርመን በሚያዚያ ወር ለአገልግሎት ይበቃል ሲል ቃል ገብቷል።