የዓለማችን 1/4ኛ የሚሆነው ሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ተደርጓል

የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። እስካሁን ድረስ ከ400ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 17ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። በአፍሪካም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዕለት በዕለት እያደገ ነው። እራስዎን ከቫይረሱ ወረርሽኝ ለመከላከል የትኛዎቹን የጤና ባለሙያዎች ምክርን እየተገበሩ ነው። ከዓለማችን የምንሰበስባቸውን ትኩስ መረጃዎች እዚህ በቀጥታ እናደርሳችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ደቡብ ኮሪያ ለአሜሪካ የመመርመሪያ ኪቶች ልትልክ ነው

    የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሙን ዤ-ኢን አሜሪካ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ኪቶች እንድትሰጣቸው መጠየቃቸውን ተናገሩ።

    ይህንን ያሉት በዋና ከተማዋ ሴኡል የመመርመሪያ ኪት አቅራቢን በጎበኙበት ወቅት ነበር።

    አክለውም ለዓለም የመመመርመሪያ ኪት ለመላክ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

    "ትናንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፍጥነት የመመርመሪያ ኪት እና የለይቶ ማቆያ ምርቶችን አንድንልክላቸው ጠይቀውናል" ብለዋል ፕሬዝዳንት ሙን።

    የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት አክሎም ደቡብ ኮሪያ ትርፍ ቁሳቁስ ካለ ለመላክ ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቋል።

  2. ኮሮናቫይረስ ዓለምን እንዴት ነው የቀየራት?

    የኮሮናቫይረስ በመላው ዓለም መሰራጨቱን ተከትሎ በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶች እየታዩ ነው። መላው ዓለም በሚባል ደረጃ ትምህርት ተቋርጧል፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል፣ አገራት ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴያቸውን እየዘጉ ነው። በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችም ጭር ብለዋል።

  3. ደቡብ አፍሪካውያን የመሰረታዊ ፍጆታ እቃ ሸመታ ላይ ናቸው

    በደቡብ አፍሪካ የመንቀሳቀስ ገደቡ ሐሙስ ዕለት ከመጀመሩ በፊት ዜጎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ሸመታ አጧጡፈዋል።

    ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቷ ከፍተኛ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ያሉባት አገር ናት።

    በደቡብ አፍሪካ እስካሁን ድረስ 554 ሰዎች ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሲሆን እስካሁን የሞተ የለም።

    በአፍሪካ የቫይረሱ ወረርሽኝ እየጨመረ ሲሆን መንግሥታት ስርጭቱን ለመግታት የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ሰዓት እላፊ እንዲሁም የአየርና የየብስ ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል።

    በናይጄሪያ የንግድ ከተማ በሆነችው ሌጎስ ሱቆች ተዘግተዋል፥፤ የገበያ ስፍራዎች ጭር ብለዋል። ምግብና መድሃኒት ከሚሸጡ ውጪ ማንም ሰው እንዲንቀሳቀስ አልተፈቀደም

    ፈረንሳእ ለበርካታ በቫይረሱ ለተጠቁ አገራት ልዩ እርዳታ እንደምትልክ ያስታወቀች ሲሆን ከእነዚህ አገራት መካከል በርካታዎቹ አፍሪካ ውስጥ ይሆናሉ ተብሏል።

  4. የአርቲስት ደበበ እሸቱ መልዕክት

    እጅን በአግባቡ አዘውትሮ መታጠብና ማኅበራዊ እርቀትን በመጠበቅ ሰዎች እራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲጠብቁ የጤና ባለሙያዎች በስፋት እየመከሩ ነው።

    ከዚህ ባሻገርም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይህንኑ መልዕክት በተለያዩ መንገዶች እያስተላለፉ ነው።

    ከእነዚህም መካከል አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ "ለምንወዳቸው ስንል እንጠንቀቅ" ሲል ጥሪውን ያስተላልፏል።

  5. ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በአንድ ወር ውስጥ የኮሮናቫይረስን አራግፋ ትጥላለች ሲሉ ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ እስከ ፈረንጆቹ ፋሲካ ድረስ ከኮሮና ነጻ ትሆናለች ብለው ቢናገሩም የኒዮርኩ አገረ ገዢ ግን ወረርሽኙ በግዛታቸው "እንደ ፈጣን ባቡር በፍጥነት እየተምዘገዘገ" መሆኑን ገልፀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የሚቀጥለው ወር መጀመሪያ "መልካምጊዜ" ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ ተስፋ የተሞላበት ንግግር የተሰማው የዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ ቀጣይዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል ትሆናለች ብሎ ስጋቱን ካስቀመጠ በኋላ ነው።

    አሜሪካ እስካሁን ድረስ 55 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 800 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  6. የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ወደ ሌላ ጊዜ ተዘዋወረ

    ኬንያ በመጪው ሐምሌ ወር ላይ ልታስተናግደው የነበረው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታወቀች።

    የአገሪቱ ስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳለው እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የኮሮናቫይረስ ስርጭት በዓለም ዙሪያ በፈጠረው ስጋት ሳቢያ ሲሆን፤ የኬንያ መንግሥት ከዓለም አትሌቲክስና ከኬንያ አትሌቲክስ ፌዴረሽን ጋር በመሆን ውድድሩ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ወስነዋል።

    ለዚህ ውሳኔም የዓለም አትሌቲክስ የህክምና ቡድን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ባደረገው ምክክር በሽታው በበርካታ አገራት ውስጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱና በርካታ ሕዝብ የሚገኝባቸው ዝግጅቶች እንዲሰረዙ በተነገረው መሰረት መሆኑን ገልጿል።

    በተጨማሪም ይህ ውድድር ለኬንያ መንግሥትና ለተሳታፊ አትሌቶች አመቺ አማራጮችንና ጊዜን ለመለየት በርካታ አማራጮች ቀርበው እየተገመገሙ መሆናቸውን ገልጿል።

    ነገር ግን የኬንያ ውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ተለዋጭ ቀኑ እስኪታወቅ ድረስ የሚያደርገውን ዝግጅት የሚቀጥል ሲሆን ተለዋጭ ጊዜውም በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግም ተስፋውን ገልጿል።

  7. ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከዋና ከተማዋ መውጣትም ሆነ መግባት ከለከለች

    ዲሞክራቲክ ኮንጎ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳን ደግሞ መውጣትን መግባት የተከለከለባት ስፍራ አደረገች።

    እርምጃውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቴሼኬዲ ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን ላይ ቀርበው እንዳስታወቁት የድንበር መግቢያዎች ተዘግተዋል፣ ወደዋና ከተማዋ መውጣትና መግባት አይቻልም፣ የአየርና የምድር ትራንስፖርት እንዲቆም ተደርጓል።

    እስካሁን ድረስ ዴሞክራቲክ ኮንጎ 45 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና ሦስት ሰዎች ደግሞ በበሽታው መሞታቸውን አሳውቃለች።

    የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ሉሙምባሺ ውስጥ ሰኞ እለት በበሽታው የተያዙ ሁለት ሰዎች ከተገኙ በኋላ የነዋሪውን እንቅስቃሴ ገድባለች።

  8. በሊቢያ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ተገኘ

    የሊቢያ ብሔራዊ በሽታ መቆጣጠሪያ በትሪፖሊ አንድ በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ማግኘቱን አስታወቀ።

    ይህ የተሰማው የትሪፖሊው መንግሥትና አማፂያን ከዓለም አቀፍ መንግሥታት የቀረበላቸውን የተኩስ አቁም ጥሪ አሻፈረን ብለው በሚታኮሱበት ወቅት ነው።

    የተኩስ አቁም ጥሪው ቀርቦ የነበረው ዓለም ላይ ላጋጠመው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሊቢያ የጤና ባለሙያዎች እንዲዘጋጁ ለማስቻል ነበር።

    በርካታ ሊቢያውያን የጤና አገልግሎቶችን የሚያገኙት በጎረቤት ቱኒዚያ ነው።

    ሊቢያ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በበቂ ሁኔታ ያልተዘጋጀች ሲሆን የጤና ሥርዓቷም ክፉኛ የተጎዳ ነው ተብሏል።

    ሊቢያና ቱኒዚያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በሚል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአየርና የየብስ ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸው ይታወሳል።

  9. ኮሮናቫይረስ በኒውዮርክ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ነው

    የኒውዮርክ አገረ ገዢ አንድሪው ኩሞ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበው በግዛቲቱ የኮሮናቫይረስ "እንደ ባቡር በከፍተኛ ፍጥነት እየተምዘገዘገ" bመስፋፋት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

    "ቁጥሩ ከጠበቅነው በላይ ከፍ ብሏል። የቁጥሩ ከፍ ማለትም ከገመትነው ጊዜ ቀድሞ ደርሷል" ብለዋል ለጋዜጠኞች ትናንትና በሰጡት መግለጫ።

    የፌደራል መንግሥቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለተጎዱ የሕይወት መታደጊያ ቁሳቁሶችን አለመላኩን በማንሳትም ወቅሰዋል።

    በኒውዮርክ 25 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን እስካሁን ድረስ 210 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል።

    የዓለም ጤና ድርጀት በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቀው አሜሪካ ቀጣይዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል ትሆናለች ሲል ስጋቱን ገልጿል።

    ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ስጋት ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕን ብዙም ያሳሰባቸው አይመስልም።

    ፕሬዝዳንቱ የተዘጉ ንግዶች በሚቀጥለው ወር የፋሲካ በዓል ሰሞን ይከፈታሉ ሲሉ ተናግረዋል።

  10. ህንድ ከቤት ውጪ ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አገደች

    የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በመላዋ አገሪቱ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ነማገድ ሕዝቡ ቤቱ እንዲቀመጥ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

    የእንቅስቃሴ እገዳው ተግባራዊ የሆነ ሲሆን ለቀጣዮቹ 21 ቀናት ይቆያል ተብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ “ማንኛውም አይነት ከቤት ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴዎች ተከልክለዋል።”

    ሞዲ ሕዝቡ በውሳኔው እንዳይሸበር ቢመክሩም፤ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚያስፈልጉትን ሸቀጦች ለመግዛት በዋና ከተማዋ ዴልሂና በሌሎችም ከተሞች የሚገኙ መደብሮችን አጨናንቋቸዋል።

    በክልከላ ውሳኔው ላይ ምግብና አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ከቤት መውጣት ይቻል እንደሆነ በግልጽ ስላልተቀመጠ ግራ መጋባትን ፈጥሯል።

    የህንድ መንግሥት ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው ባለፉት ቀናት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ነው። በመላዋ አገሪቱ እስካሁን 519 በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሲገኙ 10 ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ተነግሯል።

    1.3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ህንድ ከዕለት ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ካሉት እንቅስቃሴን የሚገድብ ተመሳሳይ እርምጃን ከወሰዱ አገራት ዝርዝር ውስጥ ገብታለች።

  11. የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ይከታተሉ

    የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። እስካሁን ድረስ ከ400ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 17ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

    የቫይረሱ ወረርሽኝ ከቻይናዋ ዉሃን ግዛት ቢጀምርም እስያን ተሻገሮ፣ አውሮፓ አሁን ደግሞ አሜሪካን ክፉኛ አስግቷል። በአፍሪካም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዕለት በዕለት እያደገ ነው።

    እራስዎን ከቫይረሱ ወረርሽኝ ለመከላከል የትኛዎቹን የጤና ባለሙያዎች ምክርን እየተገበሩ ነው። ከዓለማችን የምንሰበስባቸውን ትኩስ መረጃዎች እዚህ በቀጥታ እናደርሳችኋለን።