በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ400 ሺህ አለፈ

በትናንትናው ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ገልጾ አስጠንቅቋል። እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300ሺህ በላይ መሆኑም ተረጋግጧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱን ለመከላከል መንግሥታት ከሚወስዷቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የግለሰቦች ውሳኔም ቁልፍ ሚና እንዳለው ያስታውሳሉ። ስለኮሮናቫይረስ ማንኛውንም ማወቅ ያለብዎን ትኩስ መረጃዎች እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በናይጄሪያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 40 ደረሰ

    በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ ሦስት፣ በአቡጃ ደግሞ አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን የናይጄሪያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ይህም በናይጄሪያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 40 አደርሷል።

    እንደ ናይጄሪያ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል መግለጫ ከሆነ አዲስ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል ሁለቱ ከባህር ማዶ በቅርቡ የመጡ ናቸው።

    በናይጄሪያ ከትናንትና ምሽት ጀምሮ ዓለም አቀፍ በረራዎች የተቋረጡ ሲሆን የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት በሚልም የየብስ ድንበሮቿን ጨምራ ዘግታለች።

    በሌጎስና በአቡጃ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው እንዲሰሩ ታዝዟል።

  2. በሩዋንዳ ኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አደገ

    የሩዋንዳ ጤና ሚኒስቴር 17 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አሳወቀ። በአገሪቱ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    በአሁኑ ሰዓት በሩዋንዳ 36 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ቁጥር ነው ተብሏል።

    አዲስ ከተገኙት በበሽታው የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ ከታማሚዎች ጋር በነበረው ንክኪ የተያዘ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ከኬንያ፣ ከህንድና ከኳታር የመጡ መሆናቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ አሳውቋል።።

    ሩዋንዳ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ማንኛውንም እንቅስቃሴን ገድባለች።

  3. በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 ደረሰ

    በኢትዮጵያ አንድ የ34 ዓመት ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መያዙን ተከትሎ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 ደረሰ።

    ይህ ኢትዮጵያዊ ከዱባይ መጋቢት 10/2012 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የገባ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።

    ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 15 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን መግለጫው አክሎ ገልጿል።

    በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቫይረሱ ያለበት ሰው የተገኘው መጋቢት 3/2012 ዓ ነበር።

  4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በወሎ ሠፈር አካባቢ የፀሎትና የማዕጠንት ስርዓት ሲያከናውኑ

    ዛሬ ማለዳ ከወሎ ሠፈር እስከ ወንጌላዊት ባለው መስመር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችና ምዕመናን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ የፀሎት የማዕጠንት ስርዓት አካሂደዋል።

  5. ኢትዮጵያ የ150 ቢሊየን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ጠየቀች

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ለቡድን ሃያ አገራት በጻፉት ደብዳቤ ከኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የ150 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለአፍሪካ ጠይቀዋል።

    ይህ ድጋፍ የአፍሪካን የድንገተኛ ጊዜ ጤና አገልግሎትን፣ ለበጀት ድጎማ፣ የውጪ ምንዛሬ ክምችትን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዱ ንግድና ኩባንያዎችን ለመደገፍ ይውላል ብለዋል።

    በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት ለወሰዱት ብድር የሚጠየቁት ወለድ እንዲሰረዝና ዝቅተኛ ገቢ ላለቸው አገራት እዳ በከፊል እንዲሰረዝም ጥያቄ ቀርቧል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቡድን ሃያ አገራት በጻፉት በዚህ ደብዳቤ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ለሚያካሂደው የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የድንገተኛ ጊዜ ዝግጁነት ድጋፍ እንዲደርግለትም ይጠይቃል። የቡድን 20 አገራት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በቀትታ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእዳ ቅነሳና ስረዛ በጠየቁበት በዚህ ደብዳቤያቸው ላይ አፍሪካ ወረርሽኙ ካደረሰባት ጫና ኩባንያዎቿንና ሠራተኞቿን ለመታደግ ያለባት እዳ ጫና ፈጥሮባታል ብለዋል።

    " ኢትዮጵያ የአገራት ብድር ወለድ እንዲሰረዝ፣ በተጨማሪም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት እዳ እንዲሰረዝ ትጠይቃለች" ይላል ጠቅላእ ሚኒስትሩ ደብዳቤ።

  6. "ይህ ወረርሽኝ የማያልፍና የማናሸንፈው አይደለም" ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ

    ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጠበቅ እንዲችሉ "የጽዱ እጆች" ጥሪን ተቀብላ መልዕክት አስተላልፋለች።

    በትዊተር ገጿ ላይ ባስተላለፈችው መልዕክት እጃችንን ከተለመደው ጊዜ ይልቅ በሚገባ መታጠብ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፤ ይህንን የጽዱ እጆች ጥሪ ለጃኖ ባንድ አባላት አቅርባለች።

    አክላም "ይህ ወረርሽኝ የማያልፍና የማናሸንፈው አይደለም፤ ብዙ ሳያከስረን እንዲያልፍ ግን ከፀሎታችን ጋር አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እናድርግ" ብላለች።

  7. የብራዚል የወሮበላ ቡድኖች ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር ሰዓት እላፊ ጣሉ, የብራዚል ወንበዴዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሰዓት እላፊ ጣሉ

    በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ የሚገኙ የወሮበላ ቡድኖች የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት የሰዓት እላፊ ማወጃቸው ተሰምቷል።

    መንግሥት እርምጃ አልወስድም በማለቱ እነርሱ መውሰዳቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።

    በድሆች መንደር የሚኖሩ በርካታ የሪዮ ዴጄኔሮ ነዋሪዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ከመሸ መንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀሱ የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

    “ለማኅበረሰባችን ምርጡን ነገር ነው የምንመኘው። መንግሥት [ስለኮሮናቫይረስ] አንድ ነገር ለማድረግ አቅም ከሌለው፤ የተደራጀ የወንጀል ቡድን እርምጃ ይወስዳል” ሲል አንድ የዜና ድረ ገጽ ዘግቧል።

    የብራዚል ፕሬዝዳንት የሆኑት ቦልሶናሮ ለወረርሽኙ የሰጡት ምላሽ ከሚገባው በታች ነው በሚል ይተቻሉ። በዚህም የተነሳ በሳኦ ፖሎ እና ሪዮ ዴጄኔሮ የተለያዩ ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።

  8. ብሪታኒያ ዜጎቿ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዘች

    የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ያስችላል ያሉትን የዜጎችን አኗኗር የሚቀይሩ ጥብቅ እርምጃዎች ይፋ አደረጉ።

    በዚህም መሰረት ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ የተከለከሉ ሲሆን፤ መውጣት የሚቻለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ፣ “የግድ አስፈላጊ” ለሆኑ ሥራዎችና ጉዞዎች፣ መሰረታዊ ነገሮችን ለመግዛትና የህክምና ክትትልና ድጋፍ ለማግኘት ብቻ ይሆናል።

    መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን የሚሸጡ መደብሮች እንዲዘጉ የተነገራቸው ሲሆን አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ውጪ በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ከሁለት በላይ ሆኖ መገኘትም ተከልክሏል።

    በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እስካሁን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 335 ደርሷል።

    ዜጎች በመንግሥት የወጣውን ግዴታ ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ የመቅጣትና የተሰበሰቡ ሰዎችን የመበትን ስልጣን ፖሊስ ተሰጥቶታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ከጽህፈት ቤታቸው በቴሌቪዥን ቀርበው አስታውቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አገራቸው “ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ” እንደተጋረጠባትና ዜጎች ከቤት ባለመውጣት ጤናቸውንና የወገኖቻቸውን ህይወት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።

    የተጣለው እገዳም በመላዋ አገሪቱ ቢያንስ ለሦስት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን በየጊዜውም እየታየ ክለሳ ይደረግበታል ብለዋል።

    የብሪታኒያ መንግሥት እንዳስጠነቀቀው ከቤት መውጣት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሰዎች ከቤታቸው ውጪ በሚሆኑባቸው ወቅት ቆይታቸውን በጣም አጭር ማድረግና ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርበትም ከሁለት ሜትሮች ያነሰ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለባቸው ተመክሯል።

    በተጨማሪም መንግሥት ሠርግን፣ ክርስትናንና ሌሎች ማኅበራዊ ሥነ ሥርዓቶች እንዳይካሄዱ የከለከለ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ግን እንደሚፈቀዱ ገልጿል።

  9. "ለወረርሽኙ እስያዊ አሜሪካውያን መወቀስ የለባቸውም" ትራምፕ

    በአሜሪካ በእስያውያን ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰኞ እለት ባደረጉት ንግግር ለወረርሽኙ እስያዊ አሜሪካውያን መወቀስ የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኮቪድ-19ን “የቻይና ቫይረስ” እና “የቻይናውያን ቫይረስ” በሚል ከፈረጁ በኋላ በርካታ ትችቶች ቀርቦባቸው ነበር።

    ትራምፕ “ጠንካራ ሕዝቦች” በማለት ካንቆለጳጳሷቸው በኋላ ለእስያዊ አሜሪካውያን “ከለላ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

    በአሜሪካ እስካሁን ድረስ 43 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 533 ደግሞ ሞተዋል።

    ትራምፕ ትናንትና በዋይት ሐውስ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “እስያዊ አሜሪካውያን ማኅበረሰቦችን በአሜሪካም ሆነ በመላው ዓለም ከለላና ጥበቃ ልናደርግላቸው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

    “በጣም ጠንካራ ሕዝብ ናቸው። የቫይረሱ ስርጭት በምንም መልኩ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የለውም” በማለት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አብረው እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

  10. ደቡብ አፍሪካ ለ21 ቀናት የሚቆይ የእንቅስቀሴ ገደብ ጣለች

    ደቡብ አፍሪካ ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ የሚፀናና ለ21 ቀናት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀመጠች።

    ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለሕዝባቸው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዳስታወቁት “አስፈላጊ ከሆነ እንቅስቃሴ በስተቀር ቤታችሁ ተቀመጡ” ብለዋል።

    ለቤት አልባዎች ጊዜያዊ መጠለያ ይዘጋጃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የጸጥታ አካላትና የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ገደቡ እንደማይመለከታቸው ተገልጿል።

    በደቡብ አፍሪካ እስካሁን ድረስ 402 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸወ ሲሆን ይህም በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር ያለባት አገር አድርጓታል።

    እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ሞት ባይመዘገብም ደቡብ አፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፋለች።

  11. ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ ማድረግ የሚጠበቅብንን እናድርግ

    በትናንትናው ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ገልጾ አስጠንቅቋል።

    እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300ሺህ በላይ መሆኑም ተረጋግጧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱን ለመከላከል መንግሥታት ከሚወስዷቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የግለሰቦች ውሳኔም ቁልፍ ሚና እንዳለው ያስታውሳሉ።

    ማኅበራዊ እርቀትን መጠበቅና እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና ውሃ መታጠብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ወሳኝ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል።

    ዛሬስ ዓለማችን እንዴት ትውል ይሆን? ስለኮሮናቫይረስ ማንኛውንም ማወቅ ያለብዎን ትኩስ መረጃዎች እዚህ ሰዓት ጀምሮ እዚህ ገጽ ላይ ያገኛሉ።