በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ400 ሺህ አለፈ

በትናንትናው ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ገልጾ አስጠንቅቋል። እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300ሺህ በላይ መሆኑም ተረጋግጧል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱን ለመከላከል መንግሥታት ከሚወስዷቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የግለሰቦች ውሳኔም ቁልፍ ሚና እንዳለው ያስታውሳሉ። ስለኮሮናቫይረስ ማንኛውንም ማወቅ ያለብዎን ትኩስ መረጃዎች እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጀርመን በኬንያ የጠፋባትን 6 ሚሊዮን ማስክ እያፈላለገች ነው

    የጀርመን ባለስልጣናት በኬንያ አየር ማረፊያ የጠፋውን 6 ሚሊዮን የፊት ማስክ እያፈላለጉ መሆኑ ተነገረ።

    የጀርመን መንግሥት የፊት ማስኩን የህክምና ባለሙያዎቹ እንዲጠቀሙበት ከውጪ አገር በማዘዝ ወደ ጀርመን እያጓጓዛ ሳለ በኬንያ አየር ማረፊያ የገባበት አልታወቀም ተብሏል።

    የጀርመኑ ዴር ስፒግል የተሰኘው ጋዜጣ የፊት ማስኩ ከአራት ቀናት በፊት ጀርመን መድረስ ነበረበት ሲል ዘግቧል።

    የፊት ማስኩ ወደ ኬንያ አየር ማረፊያ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ግልጽ አልሆነም።

    የጀርመን ጦር ቃል አቀባይ ለሬውተርስ "የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት የተፈጠረውን ለመረዳት እየሞከሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

    ሬውተርስ ጨምሮም የኬንያ ኤርፖርቶች ኃላፊ ጉዳዩን እያጣሩ ነው ሲል ዘግቧል።

  2. ሰበር, ሰበር, በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ400 ሺህ አለፈ

    በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 407,485 ደረሰ።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 300 ሺን የተሻገረው ባሳለፍነው ዕሁድ ነበር። በሦስት ቀናት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ጨምሮ ዛሬ 400 ሺህ ማለፉን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሁናዊ አሃዝ ጠቁሟል።

    በጆን ሆፕኪንስ መረጃ መሠረት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 407,485 ሲሆን የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 18,227 ደርሷል።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንደየ ቅደም ተከተላቸው በቻይና፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ጀርመን እና ኢራን ተቀምጠዋል።

    በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸው አገራት ደግሞ ጣሊያን፣ ቻይና፣ ስፔን፣ ኢራን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።

  3. ሰበር, ጣሊያን ዳግም ከፍተኛ የሟቾች ቁጥርን አስመዘገበች

    በጣሊያን በአንድ ቀን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 743 መድረሱን የአገሪቱ መንግሥት ይፋ አድርጓል።

    ምንም እንኳ አሃዙ ከፍተኛ ቢሆንም ጣሊያን ባለፉት ተከታታይ ቀናት የሟቾች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ታይተው ነበር።

    ዛሬ 743 መሞታቸውን ተከትሎ በጣሊያን የሟቾች ቁጥር በአጠቃላይ 6820 ደርሷል።

  4. አሜሪካ በቀጣይ ኮሮናቫይስ በስፋት የሚሰራጭባት አገር ትሆናለች ተባለ

    የዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ በቀጣይ ኮሮናቫይስ በስፋት የሚሰራጭባት አገር ትሆናለች ሲል አስጠነቀቀ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስ እንዳሉት በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።

    እስካሁን በአሜሪካ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 46 ሺህ ያለፈ ሲሆን 593 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል።

    በአሁኑ ሰዓት አውሮፓ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ማዕከል ሆናለች።

  5. ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ሠራተኞች 64% ከቤት ሆነው ይሰራሉ ተባለ

    የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ቤት ሆነው እንዲሰሩ የሚንስትሮች ምክር ቤት ቀደም ሲሉ መወሰኑ ይታወሳል።

    ከቤት ሆነው የሚሰሩ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች በእያንዳንዱ የሚንስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት እንደሚለዩ ና ማን ከቤት ሆኖ እንደሚሰራ ያስታውቃሉም ተብሎ ነበር።

    በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚንሰትሩ ጽ/ቤት፣ ትምህርት ሚንስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤት ሆነው የሚሰሩ ሠራተኞችን ለይተናል ብለዋል።

    የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ካሉኝ 289 ሠራተኞች 184 ከቤት ይሰራሉ ያለ ሲሆን፤ የትምህርት ሚንስቴርም የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞችን ጨምሮ ካሉት 1544 ሠራተኞች መካከል 87.3 በመቶው በቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተወስኗል ብሏል።

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ከወሳኝ የሥራ ሂደት ውጪ ላልተወሰነ ጊዜ ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ተወስኗል ብሏል።

    የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ የመብራት አገልግሎት፣ የውሀ፣ የትራንስፖርት ዘርፍ፣ መንገዶችና ኮንስትራክሽን፣ የጤና ባለሙያዎች እና የፖሊስ አባላትን አያካትትም ተብሏል።

  6. ትራምፕ ደቡብ ኮሪያ ለአሜሪካ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እንድታደርግ ጠየቁ

    ፕሬዝደንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ ለአሜሪካ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እንድታደርግ መጠየቃቸው ተነገረ።

    ትራምፕ ይህን ጥያቄ ለደቡብ ኮሪያ መሪ ዛሬ በስልክ ማቅረባቸውን የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ቢሮ አስታውቋል።

    ደቡብ ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን የተቆጣጠረችበት መንግድ እጅጉን አስወድሷታል። ቴክኖሎጂን አብዝታ በመጠቀም በርካቶችን መርምራለች እንዲሁም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ለይታለች።

    ትራምፕ የጠየቁት የሕክምና ቁሳቁስ ዝርዝር ይፋ ባይሆንም የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሙን ግን ለአሜሪካ አቅም በፈቀደ መልኩ “ከፍተኛ ድጋፍ” ይደረጋል ብለዋል።

  7. “ዋናው መፍትሄ መከላከል እና መከላከል ብቻ ነው” - የአማራ ሀኪሞች ማኅበር

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት፤ መንግሥት የመመርመሪያ መሳሪያዎችን እና የህክምና ባለሙያዎች አልባሳትን በተቻለው አቅም እንዲያቀርብ የአማራ ሀኪሞች ማኅበር ጠየቀ።

    ማህበሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት የሚያበረታታ ነው ብሏል።

    በመግለጫው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ታደሠ "በሽታው አዲስ እንደመሆኑ ከሙከራ ያለፈ የተረጋገጠ መድሀኒት ስለሌለው ዋናው መፍትሄ መከላከልና መከላከል ብቻ ነው" ብለዋል።

    የጤና ባለሙያዎች በሽታው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ለሕዝቡ ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ያሳዩትን ዝግጁነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያስመሰግን ነው ብሏል ማኅበሩ።

    በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለይም የህክምና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከመንግሥት እና ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጠይቆ ማህበሩም ግዴታውን እንደሚወጣ አስታውቋል።

  8. ሰበር, ሕንድ ሙሉ ለሙሉ የዜጎችን እንቅስቃሴ ልታግድ ነው

    ሕንድ የዜጎችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ልታግድ ነው።

    ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ሕንድ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከዛሬ እኩለ ሌሊት ጀምሮ በአገሪቱ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ይታገዳሉ ብለዋል።

    ናሬንድራ ሞዲ 1̀.2 ቢሊዮን ዜጎች ለ21 ቀናት በቤት ውስጥ እንዲቆዩ አውጀዋል።

    ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ከአራት ሰዓታት በኋላ እንደማለት ነው።

    ከሕንድ ትላልቅ ከተሞች መካከል እንደ ዴልሂ እና ሙምባይ ያሉ ከተሞች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ እንቅስቃሴ አልባ ሆነው ሰንብተዋል።

  9. በኮሮናቫይረስ ከተያዙት 8ቱ የጤና መሻሻል እያሳዩ ነው ተባለ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱ ይታወቃል።

    ከእነዚህም መካከል የ 8ቱ ሰዎች ጤና መሻሻል እየታየበት መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ዶ/ር ተገኔ በቫይረሱ የተያዙት ሁለቱ ጃፓናውያን የጤና መሻሻል ካሳዩ በኋላ በእራሳቸው ጥያቄ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።

    ከውጪ አገር መጥተው በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የ 85 ዓመት እናት የጤና ሁኔታ አስጊ እንደነበረ አስታውሰው፤ የቅርብ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

  10. ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች የሚቆዩባቸው ተጨማሪ 6 ሆቴሎች ተለዩ

    የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች በራሳቸው ወጪ ለ14 ቀናት በሆቴል እንዲቆዩ መወሰኑ ይታወሳል።

    ይህም የመንግሥት ውሳኔ ከትናንት በስቲያ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ በስካይላይት እና ግዮን ሆቴሎች ተፈጻሚ ሲሆን ቆይቷል።

    ይሁን እንጂ የሆቴሎች ቁጥር በቂ ስላልሆነ ተጨማሪ 6 ሆቴሎች እንዲለዩ መደረጉን በጤና ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በዚህም መሠረት፤ ጁፒተር፣ ኤሊያና፣ ማግኖሊያ፣ አዜማን፣ ቤስት ዌስተርን እና ቦን ፕላዛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኖች የሚቆዩባቸው ሆቴሎች ይሆናሉ ተብሏል።

  11. ሰበር, ኬንያ በኮሮና የተያዙ አዲስ 9 ሰዎች ማግኘቷን ተከትሎ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 ደርሷል

    ኬንያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 9 ሰዎች ማግኘቷን ዛሬ ይፋ አድርጋለች። ከእነዚህ መካከል ሰባቱ ኬንያውን መሆናቸውን እና ሁለቱ ደግሞ የውጪ አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ አስታውቀዋል።

    ይህን ተከትሎ ኬንያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 ደርሷል።

    በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ናይሮቢ፣ ኪዋሌ፣ ኪሊፊ እና ሞምባሳ በሚባሉ አራት የኬንያ ግዛቶች ውስጥ ይገኛሉ።

  12. አሽከርካሪው እና ረዳቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል

    በአዳማ ከተማ “በኮሮናቫይረስ ምክንያት ረዳቱን መልስ አይጠይቁ” የሚል መልዕክት ለጥፈው የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት አሽከርካሪ እና ረዳት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስተወቀ።

    የምዕራብ ሸዋ ዞን የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር እስማኤል አባድር “አሽከርካሪው ከተሳፋሪዎች በሕገ-ወጥ መንግድ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት አድርጓል” ብለዋል።

    “መልስ አጥጠይቁ ማለት ዘረፋ ነው” ያሉት ኢንስፔክተሩ፤ ረዳቱ እና አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ምረመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢንስፔክተሩ ጨምረውም ማህብረሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲጠቀም እራሱን ለቫይረሱ እንዳያጋልጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት አስታውሰዋል።

  13. ሰበር, የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ተወሰነ

    የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ሥራቸውን ከቤት እንዲያከናውኑ ተወሰነ

    የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት እንዳስታወቀው የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ 17ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

    በዚህም የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከነገ መጋቢት 16 ጀምሮ ተጨማሪ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ ሥራቸውን ከቤት ሆነው እንዲያከናውኑ ተወስኗል።

    ከቤት ሆነው የሚሰሩ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች በእያንዳንዱ የሚንስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት እንደሚለዩ እና ማን ከቤት ሆኖ እንደሚሰራ ያስታውቃሉ ተብሏል።

    ይህ ውሳኔ የተላለፈው በአዲስ አበባ የሚካሄድ እንቅስቃሴን እና የትራንስፖርት ዘርፉን መጨናነቅ ለመቀነስ ታስቦ ነው።

  14. ሰበር, የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ተወሰነ

    በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት የዘንድሮው ኦሎምፒክ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ተወሰነ።

    የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ውድድሩ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ጋር ተስማምተናል ብለዋል።

    የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የጃፓንን ጥያቄ ተቀብሎ የዘንድሮ ኦሎምፒክ በአንድ ዓመት ተራዝሞ እአአ 2021 እንደሚካሄድ ተነግሯል።

    የቢቢሲው የስፖርት አርታኢ ዳን ሮዓን እንደዘገበው ኦሊምፒክ በታሪኩ ተራዝሞ አያውቅም። በጦርነት ወቅትም ውድድሩ ተሰርዞ ነበር እንጂ ተራዝሞ አያውቅም።

  15. በስፔን በኮሮና ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ514 ጨመረ

    በስፔን በኮሮናቫይረስ ምከንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ24 ሰዓት ውስጥ በ514 ጨመረ።

    እንደ ስፔን ጤና ሚኒስቴር ከሆነ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 39,637 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 2,696 ደግሞ ሞተዋል።

    የስፔን ወታደሮች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚያደርገው ድጋፍ ወቅት በእድሜ የገፉ ሰዎች መጠለያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙና ያለ ተንከባካቢ የቀሩ እንዲሁም በአልጋቸው ላይ የሞቱ ሰዎችን ማግኘታቸውን ተናግሮ ነበር።

    የስፔን አቃቤ ሕግ ጉዳዩን እየመረመረው መሆኑን አስታውቋል።

    በተያያዘ ዜና በጣሊያን የዜጎች ደኅንነት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሰረት ከሆነ 600 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ አልቀሩም።

    ይህ ቁጥር ከመንግሥት ይፋዊ አሃዝ በአስር እጥፍ የላቀ ነው ተብሏል።

  16. የቶኪዮ ኦሊምፒክ ወደ ሌላ ጊዜ የማስተላለፍ ውሳኔ ዛሬ ሊሰጥ ይችላል

    በጃፓን አስተናጋጅነት በቶክዮ ሐምሌ ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የ2020ው ኦሊምፒክ ዛሬ ወደ ሌላ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችል ቢቢሲ ስፖርት ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለማወቅ ችሏል።

    የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ "ኮሚቴው ከጃፓን ባለሰልጣናት ጋር እየተነጋገረ ነው፤ የስፖርቱ አዘጋጅ ኮሚቴና ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቦርድ አባላት ወደ ሌላ ጊዜ ስለመተላለፉ ጨምሮ ያሉ እቅዶች ላይ እየተነጋገረ ነው፤ እንደጨረሱ እናሳውቃለን" ብለዋል።

    በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ካናዳ እራሷን ከጃፓኑ የኦሊምፒክ ውድድር ማግለሏ ይታወሳል።

  17. ኢራን ለ85ሺህ እስረኞቿ ተጨማሪ የአንድ ወር ፈቃድ ሰጠች

    በኢራን እስካሁን ድረስ 1,812 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሲሆን በአጠቃላይ ከ23ሺህ በላይ ኢራናውያን በቫይረሱ ተይዘዋል።

    የኢራን ባለስልጣናት የቫይረሱን ስርችት ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ወደቤተሰቦቻቸው ፈቃድ ተሰትቷቸው ሄደው ለነበሩ 85ሺህ እስረኞች ለተጨማሪ አንድ ወር ባሉበት እንዲቆዩ ፈቃድ መስጠታቸው ተዘግቧል።

  18. ታዋቂው ሙዚቀኛ ማኑ ዲባንጎ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወቱ አለፈ

    ታዋቂው ካሜሩናዊ የአፍሮ ጃዝ ሙዚቃ ኮከብ ማኑ ዲባንጎ በኮሮናቫይረስ ህመም ምክንያት ማረፉን ቤተሰቦቹ አስታወቁ።

    "የማኑ ዲባንጎ (ፓፒ ግሩቭ) ህልፈትን ይፋ ስናደርግ በታላቅ ሃዘን ውስጥ ሆነን ነው” ቤተሰቦቹ ያሉ ሲሆን፤ የዲባንጎ ህይወት ዛሬ ያለፈው ዓለምን እያስጨነቀ ባለው የኮቪድ-19 ቫይረስ ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል።

    ቤተሰቡ ጨምሮም የማኑ ዲባንጎ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከቤተሰቡ ውጪ ፈጽሞ ማንም እንዳይገኝ የሚፈልጉ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ወደፊት የሚታወስበትን ሥነ ሥርዓት እንደሚያዘጋጁ አሳውቀዋል።

    ማኑ ዲባንጎ የአገሩን ባህላዊ ሙዚቃ ከሌሎች ጋር በማዋሃድ አፍሮ ጃዝ የተሰኘውን የሙዚቃ ስልት በመጀመር በኩል ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገርለታል።

    የ86 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የነበረው የታዋቂው ሳክስፎን ተጫዋች ሞት ሲሰማ በአድናቂዎቹ ዘንድ ከባድ ድንጋጤን ፈጥሯል።

  19. በኡጋንዳ ስምንት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኙ

    ኡጋንዳ ስምንት አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እንዳገኘች አስታወቀች። በዚህም በአገሪቱ በሽታው የተገኘባቸው ቁጥር 9 ደርሷል።

    ሁሉም አዲስ የተገኙት ታማሚዎች በቅርቡ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ተጉዘው እንደነበረም ተገልጿል። ነገር የኤምሬቶች መንግሥት ከፍተኛ ስጋት ያለባት አገር እንዳልሆነች ነው የሚገልጸው።

    ከቀናት በፊት የኡጋንዳ መንግሥት ዜጎቹ የኮረናቫይረስ ወደ ተከሰተባቸው አገራት እንደይጓዙ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።

    ከስምንቱ ህሙማን ውስጥ ስድስቱ በኢንቴቤ አየር ማረፊያ ላይ በተደረገ ምርመራ የታወቁ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በበሽታው ተጠርጥረው ተለይተው በቆዩበት ቦታ መያዛቸው መታወቁን የአገሪቱ ጤና ሚኒሰቴር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    በተጨማሪም መንግሥት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ ዱባይ ተጉዘው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ለምርመራ እንዲቀርቡ ጥሪ አድርጓል።

    ይህ በእንዲህ እያለ መንግሥት በመላው አገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ያወጣውን ትዕዛዝ የጣሱ በዋና ከተማዋ ካምፓላ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ ፖሊስ ድንገተኛ አሰሳ አድርጓል።

    በዚህም አምስት ተማሪዎችና 23 መምህራን ከአንደኛው ትምህርት ቤት ሲያዙ በሁለተኛው ውስጥ ደግሞ 53 መምህራን ተገኝተዋል።

    ፖሊስ እንዳለው ከመምህራኑ መካከል የተወሰኑት ወደ ትምህርት ቤቶቹ መጥተው ለተማሪዎቻቸው ኢሜይል እንዲልኩ መጠራታቸውን፣ ሌሎቹ ደግሞ ደሞዛቸውን ለመውሰድ እንደመጡ ተናገረዋል።

  20. በጋና በኮሮናቫይረስ ተይዞ ነበረ ግለሰብ መሞቱ ተሰማ

    በጋና በኮሮናቫይረስ ተይዞ የነበረ ግለሰብ መሞቱ ተነገረ። በአገሪቱ በኮሮና ምክንያት ሰዎች ሲሞቱ ይህ ሁለተኛው ነው ተብሏል።

    በጋና ሌሎች ሁለት ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸው የተገለፀ ሲሆን ይሀም በአገሪቱ በኮቪድ -19 የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 27 አድርሶታል።

    በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 20ዎቹ ጋናውያን ሲሆኑ፣ ሰባቱ ደግሞ የኖርዌይ፣ የሊባኖስ፣ የቻይና፣ የፈረንሳይ እና የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።

    ሁሉም በቫይረሱ የተያዙ ጋናውያን በቫይረሱ ወደተገኘባቸው አገራት ሄደው የነበሩ መሆኑ ተገልጿል።

    ጋና ድንበሯን ሙሉ በሙሉ የዘጋች ሲሆን የአገሪቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ሁሉንም የባህር ዳርቻዎቿን ዘግቷል።