በጣሊያን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በለጠ

በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእሲያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ በርካታ የዓለማችን አገራት የተለያዩ እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ ይገኝበታል። ዛሬስ በአገራችንና በዓለማችን ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉ? ቢቢሲ አማርኛ በዚህ የቀጥታ ዘገባው ወደ እናንተ ያደርሳል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ይቋጫል።

    የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ተቋጭቷል።

    ወደ እናንተ ስናደርሳቸው የነበሩትን ዘገባዎች ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ።

    ነገ ጠዋት በሌላ የቀጥታ ዘገባ እንመለሳለን።

    መልካም ምሽት

  2. ሰበር, በጣሊያን በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በለጠ

    ጣሊያን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 427 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገች።

    ይህም የሟቾችን ቁጥር 3,405 በማድረስ ቻይና ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከሞቱት በላይ አድርሶታል።

    ቫይረሱ የተከሰተባት ቻይና የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,242 ነው።

  3. በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምልክት ከታየባቸው አራቱ ነፃ ሆነው መገኘታቸው ተነገረ

    በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው ከነበሩ ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ ነፃ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

    የተቀሩት የሁለቱ ሰዎች ውጤት እንደታወቀ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።

    ወረርሽኙ ወደ ክልሉ እንዳይገባ ጠንካራ እርምጃዎች እየወስድኩ ነው ያለው የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ከአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር በተጨማሪ የክልሉ መግቢያ በሆኑት በደጀን፣ ደብረ ብርሃን እና ባቲ የሙቀት መለካት ሥራ ተግበራዊ ማድረግ ይጀመራል ብሏል።

    ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪይ ይጫኑ።

  4. የደኅንነቶች ክትትል በኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪዎች ላይ

    የእስራኤል የደኅንነት ሰራተኞች በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን በጥብቅ እየተከታተሉ ሲሆን እራሳቸውን ለመሰወር የሚሞክሩትን ደግሞ አድነው እየያዙ ነው።

  5. ፕሪሚየር ሊጉ ቢያንስ እስከ ሚያዚያ 22 ድረስ አይካሄድም

    በእንግሊዝ የሚካሄዱ ሊጎች በጠቅላላ እየጨመረ በመጣው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቢያንስ እስከ ሚያዚያ 22 ድረስ እንደማይካሄድ ተገለጸ።

    ይህን ውሳኔ የተላለፈው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የእንግሊዝ ቻምፒንሺፕ እና ኤፍኤ ካፕ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።

    የእግር ኳስ ማህበሩ ሊጎቹ አሁንም ቢሆን “ላልተወሰነ ጊዜ ሊራዘሙ ይችላሉ” ብሏል።

    ሰኔ ሊካሄድ የነበረው የአውሮፓ ዋንጫ እንዲራዘም መደረጉ፤ የእንግሊዝ እና በአውሮፓ የሚገኙ ሊጎች ወድድሮቻቸውን ሰኔ ላይ እንዲያጠናቅቁ ይረዳል ተብሏል።

  6. በወረርሽኙ ምክንያት በዶ/ር ካትሪን ስንብት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ወስን እንደሚሆን ተነገረ

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ስንብት ላይ የሚገኙ የሰዎች ቁጥር ውስን እንደሚሆን ተነገረ።

    የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ታፈሰ እንዳሉት ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አድናቂዎች፣ ደጋፊዎችና ከየማዕከላቱ የመጡ ሠራተኞች እየተገኙ ስንብት ይደረጋል ብለዋል።

    ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጨምረውም የዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ ከቀኑ 7፡00 በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን አንደሚፈፀም ገልጸዋል።

    ለሦስት ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለ61 ዓመታት ስለመኖሩት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የህይወት ታሪክ ለማንበብ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ • ካትሪን ሐምሊን ማናቸው?

  7. ኮሮናቫይረስ “ዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት የለውም”

    የጤና ሚንስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የኮሮናቫይረስ በሽታ ዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት የለውም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ሊያ ጨምረውም በሽታው ከየትኛውም አገር እና ዜግነት ጋር አይገናኝም ብለዋል።

    ትናንት በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኮቪድ-19 [ከኮሮናቫይረስ] ክስተት ጋር በተያያዘ ጸረ የውጪ ዜጋ የሆኑ ስሜቶች እየተንጸባረቁ እና ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑን ማመልከቱ ይታወሳል።

    ዶ/ር ሊያ በትዊተር ገጻቸው "በሽታው በሁላችንም ላይ የመጣ የጋራ ፈተና ነውና ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በመተባበርና በመረዳዳት በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ልናሳልፈው ይገባል" ብለዋል።

  8. በስፔን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥረ ጨመረ

    የስፔን ጤና ጥበቃ ሚንስቴር በኮሮናቫይረስ አዲስ 209 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገ።

    ይህም በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ወደ 767 ከፍ አድርጎታል።

    በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ13,716 ወደ17,147 አድጓል።

    ስፔን ከቻይና፣ ጣሊያን እና ኢራን በመቀጠል በዓለማችን በርካታ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች የሚገኙባት አገር ሆናለች።

    የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ፤ በአሁኑ ወቅት 939 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ማከሚያ ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ እና 1,107 ከበሽታው መዳናቸውን ጨምሮ አስታውቋል።

  9. ሩዋንዳ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት በረራዎችን አገደች

    ሩዋንዳ ወደ ግዛቷ የሚገቡም ሆነ ከግዛቷ የሚወጡ በረራዎችን አገደች።

    በሩዋንዳ ሦስት ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ይህም በአገሪቱ ያለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 11 አድርሶታል።

    አዲስ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል አንድ የ26 ዓመት ሩዋንዳዊ የሚገኝበት ሲሆን ግለሰቡ በቅርብ ጊዜ ወዴትም አገር ለመሄድ በረራ ተጠቅሞ አያውቅም ተብሏል።

    ሁለቱ ግን አንዲት ሕንዳዊት በቅርቡ ቫይረሱ የተገኘበትን ሰው ያገባችና አንድ የ45 ዓመት ጎልማሳ ከቤልጂያም በአዲስ አበባ በኩል አድርጎ የመጣ መሆኑ ተገልጿል።

    የሩዋንዳ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ በረራቸውን ወደሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ካልሆነም ገንዘባቸውን እንደሚመልስ ተናግሯል።

  10. ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ወቅትን በተመለከተ መርሃ-ግብሩን ወደፊት እንደሚገልጽ አስታወቀ

    የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ዛሬ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መርሃግብር ወደፊት እንገልፃለን ብለዋል።

    ሚኒስትሩ አክለውም ተፈታኞች በተዘጉት የትምህርት ቀናት በቤታቸው ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

    ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እስከ መጋቢት 21/2012 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውሰው በዚህ ወቅት ሳይሰጥ የቀረውን ትምህርት በተመለከተ ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

  11. በኢትዮጵያ ለ15 ቀናት እስረኞችን መጠየቅ ተከለከለ

    የኮሮናቫይረስ የፈጠረውን ስጋት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እስረኞች ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ እግድ ጥሏል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በእገዳው ጊዜ ከፍተኛ የጤና ችግር ካልገጠመ በስተቀር እስረኞቹ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ ወደ ሚገኙ ሆስፒታሎች እንዲሄዱ አይደረግም።

    ኢትዮጵያ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በርካታ ሰው የሚገኝባቸው ስብሰባዎችና ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ከማገዷ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለ15 ቀናት እንዲዘጉ አድርጋ ተጨማሪ የበሽታውን መስፋፋት መከላከያ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን አሳውቃለች።

  12. አውስትራሊያ የውጪ አገር ተጓዦች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ ከለከለች

    አውስትራሊያ ከአርብ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ባለችው ውሳኔዋ የውጪ አገር ተጓዦች ሙሉ በሙሉ ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጥላለች።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ይህንን ውሳኔያቸውን ኮቪድ-19ን ለመከላከል ወሳኝ ነው ሲሉ ገልፀውታል።

    ከዚህ እገዳ ቀደም ብሎ ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት የሚመጡ ግለሰቦችን ወደለይቶ ማከሚያ ማስገባት በራሱ ወደ ግዛቷ የሚመጡ ዜጎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶት ነበር ተብሏል።

    በዚህ አዲስ ውሳኔ ደግሞ ከአውስትራሊያንና የአውስትራሊያ የመኖሪያ ፍቃድ ካላቸው ውጪ ማንም ወደ አውስትራሊያ እንዲገባ አይፈቀድለትም።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን እንደተናገሩት ከሆነ በአውስትራሊያ በቫይረሱ ከተያዙ 80 በመቶ ያህሉ ከሌላ አገር የመጡ ወይም ከእነዚህ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ናቸው ብለዋል።

  13. በሴራሊዮን በኮሮናቫይረስ ፍራቻ አራት ቱሪስቶች እንዳይገቡ ተከለከሉ

    በትናንትናው ዕለት የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ወደሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱ አራት ጃፓናዊ አገር ጎብኚዎች በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት መግባት ተከለከሉ።

    አገር ጎብኚዎቹ የኬኒያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የተሳፈሩት ከላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ነበር ተብሏል።

    የሴራሊዮን ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው የአውሮፕላን ማረፊያው ባለስልጣናት በአውሮፕላኑ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚያሳዩ መንገደኞች እንዳሉ አስቀድሞ ተነግሯቸው ነበር።

    አራቱ አገር ጎብኚዎች "ለሕዝብ ደህንነት ሲባል" እንዳይገቡ ተደርገዋል ካለ በኋላ፤ ይዟቸው የመጣው አውሮፕላን ለጊዜው የት እንደሆነ ወዳልተገለፀ ስፍራ እንዲወስዳቸው ተደርጓል ይላል።

    በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች ለይቶ በማከሚያ ስፍራ እንዲቆዩ መደረጉም ተገልጿል።

    በሴራሊዮን እንስካሁን ድረስ አንድም በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው አልተገኘም።

  14. ትራምፕ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አሜሪካ ወደጦርነት እንደምትገባ ያህል እንደተዘጋጀች ተናገሩ

    እራሳቸውን "የጦርነት ጊዜ መሪ" በማለት የጠሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ "ሙሉ በሙሉ ድል" እንደምታስመዘግብ ተናግረዋል።

    አሜሪካ የወታደራዊ ኃይሏን የሕክምና ቡድን ዝግጁ እያደረገች ሲሆን አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶችንም በፍጥነት በማምረት ላይ ትገኛለች።

    ሁለት የባህር ኃይል መርከብ ሆስፒታሎች ለህሙማን የአልጋ እጥረት ከተፈጠረ በሚል ዝግጁ መደረጋቸው ተገልጿል።

    ሌሎችም የወታደራዊ ኃይሉ የሕክምና ቡድን አባላት በተጠንቀቅ ሆነው እንዲጠብቁ ትዕዛዝ መተላለፉ ተነግሯል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ ሁለት የምክር ቤት አባላት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በአሜሪካ እስካሁን ድረስ 9 ሺህ 300 ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን 150 ሰዎች ሳይሞቱ አልቀሩም ተብሏል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ዝግጁ መሆን አለመሆኗን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ "ያለንበት ሁኔታ ጦርነት ነው" ካሉ በኋላ "ራሴን የማየው የጦርነት ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጌ ነው" ሲሉ አክለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አክለውም የኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ከዓለም ሕዝብ ጋር በጋራ መሆናቸውን ገልፀው "የማይታይ ጠላታችን ነው። ያ ደግሞ ምንጊዜም ጠንካራው ጠላት ነው" ብለዋል።

    አክለውም "ነገርግን ይህንን የማይታይ ጠላት እናሸንፈዋለን። እንደማስበው ካሰብነው ጊዜ በፈጠነ ሁኔታ እናሸንፈዋለን። ሙሉ በሙሉ ድል፤ የተረጋገጠ ድል ይኖረናል" ብለዋል።

  15. እራሳችንንና ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?

    እነዚህን መልካም ልምዶች ይከተሉ

    • እጅዎ በሚታይ ሁኔታ ሲቆሽሽ ዘወትር በሳሙናና በውሃ በደንብ አድርገው ይታጠቡ።
    • በእጅዎ ላይ የሚታይ ቆሻሻ ከሌለ ከአልኮል በተዘጋጁ የእጅ ማጽጃ እጅዎን ያጽዱ ወይም በሳሙናና በውሃ ይታጠቡ።
    • በሚያስነጥሱ ወይም በሚያስሉ ጊዜ ተጠቅመው በሚጣሉ ስስ ወረቀቶች አፍና አፍንጫዎን ይሸፍኑ።የተጠቀሙበትንም ወረቀት ወዲያው ያስወግዱ።
    • በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት የመጡ ከሆነና ትኩሳት፣ሳል፣የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።
    • ሲያስሉና ሲያስነጥሱ በስስ ወረቀት ወይም በክርንዎ አፍና አፍንጫዎን ይሸፍኑ።

    ማድረግ የሌለብዎነገሮች

    • በህይወት ካሉ የግብርናና የዱር እንስሳት ጋር ወይም እነሱ ከነኳቸው ነገሮች ጋር መከላከያ ሳያደርጉ የቅርብ ንክኪን ያስወግዱ።
    • በበሽታ የሞቱ እንስሳትን ሥጋ ከመመገብ ይቆጠቡ።
    • የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው አገራት ከመጡ ወይም የጉንፋን ምልክቶች ከሚታይባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪን ያስወግዱ።
    • ጥሬ ሥጋን፣ እንቁላልንና ወተትን ጨምሮ ያልበሰሉ የእንስሳ ተዋጽኦዎችን ከመመገብና ከመጠጣት ይቆጠቡ።
  16. በኬንያ በመስጂድና አብያተክርስትያናት የሚደረግ አምልኮ ተከለከለ

    ኬንያ በአገሯ ሰባት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ካገኘች በኋላ በአንዳንድ መስጂዶችና አብያተክርስትያኖች የሚደረግ የአምልኮ ስነስርዓትን ከለከለች።

    ይህንን እገዳ ተከትሎ አምስት ትልልቅ አብያተክርስትያናት ምዕመኖቻቸውን በቀጥታ የኢንተርኔት ስርጭት እንደሚያስመልኩ ገልፀዋል።

    ፕሬስፔቴሪያን እና አንግሊካን አብያተክርስትያኖች የጋብቻ ስነስርዓታቸውን ለመፈፀም መርሃ ግብር አስይዘው የነበሩ አባላቶቻቸውን ወደሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ ካልሆነም አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰው ብቻ እንዲገኝ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    በኬንያ መዲና የሚገኘው ጃሚያ መስጂድም የጋራ ፀሎት ስነስርዓት እንደማይኖር ገልጿል።

    የመስጂዱ ኃላፊዎች ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጽ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለውን ሁኔታ በተከታታይ እንደሚያስታውቁ ገልፀዋል።

  17. የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካን ለከፋ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንድትዘጋጅ አሳሰበ

    የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ አፍሪካ ለከፋ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንድትዘጋጅ ተናገሩ።

    በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 16 በኮሮና የተያዙ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ስድስቱ በግብጽ፣ ስድስቱ በአልጄሪያ፣ ሁለት በሞሮኮ አንድ በሱዳንና በቡርኪናፋሶ መሆናቸው ታውቋል።

    እስካሁን ድረስ በአፍሪካ አነስተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ የተመዘገበ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች ግን ቫይረሱ በድንገት በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰረራጭና ያለውን የጤና ስርዓት ፈተና ውስጥ ሊጥለው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

    የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የዓለም ጤና ድርጅቱ ሃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጠቅሶ " አፍሪካ ልትነቃ ይገባል፤...በሌሎች አገራት ቫይረሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዴት እንደሚጨምር አይተናል" ማለታቸውን ዘግቧል።

    በትናንትናው ዕለት በደቡብ አፍሪካ 116 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአንዴ ሲመዘገቡ ከእነዚህ መካከል ቫይረሱ ከያዛቸው ጋር ንክኪ የነበራቸው 14 ደቡብ አፍሪካውያን እንደሚገኙበት ባለስልጣናት ገልፀዋል።

  18. ልጆችዎ ከሌሎች ልጆች ጋር እንዲጫወቱ ይፈቅዳሉ?

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ልጆች ቤት ውለዋል። ወላጆች በዚህ የእረፍት ወቅት ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ለመወሰን ከራሳቸው ትግል የሚገጥሙበት ወቅት ነው።

    ልጅዎ ከሌሎች ልጆች ጋር እንዲጫወት ይፈቅዳሉ? ወይስ ከሌሎች ልጆች ጋር አትቀላቀል ሲሉ ይከለክላሉ?

    የጤና ባለሙያዎች ማንኛውም ሰው ከሚያስል ወይንም ከሚያስነጥስ ሰው ቢያንስ ሁለት ሜትር መራቅ አለበት ሲሉ ይመክራሉ? እርስዎስ ለልጅዎ ምን ብለው ነግረውት ይሆን?

  19. የእስያ አገራት በሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ እየተጠቁ ነው

    ደቡብ ኮሪያ ፣ ሴንጋፖርና ቻይና ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ እያጠቃቸው ካሉ የእስያ አገራት መካከል ናቸው። ይህ በአገራቱ እየታየ ያለው ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ ከውጭ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።

    የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ቻይና እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ የመዘገበችው ምንም ዓይነት አዲስ የኮሮናቫይረስ ታማሚ የለም። ነገር ግን በቅርቡ ከውጭ ወደ ቻይና የገቡ 34 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

    ደቡብ ኮሪያም ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ 152 አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙባት ሲሆን ከእነዚህ ምን ያህሉ ከውጭ የመጡ ናቸው የሚለው አልታወቀም።

    በትናንትናው እለት ሴንጋፖር ደግሞ 47 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ከእነዚህ 33 የሚሆኑት ከውጭ የመጡ ናቸው ተብሏል።

    በሌላ በኩል በቻይና ስምንት ሞት የተመዘገበ ሲሆን ሁሉም ኮሮናቫይረስ በተቀሰቀሰባት ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ የተመዘገቡ ናቸው።

  20. በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ምክንያት 475 ሰዎች በአንድ ቀን ብቻ ሞቱ, በጣሊያን እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት መካከል 3ሺህ ሰዎች ሞተዋል

    በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 475 ሰዎች በአንድ ቀን ብቻ መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።

    ይህ ቁጥር ቫይረሱ ከተከሰተ ትልቁ ነው የተባለ ሲሆን በአገሪቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርንም ወደ 3ሺህ አድርሶታል።

    በጣሊያን በአሁኑ ሰአት 35,713 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከበሽታቸው ያገገሙት 4ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው።

    ሎምባርዲ በምትሰኘውና ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ግዛት በአንድ ቀን የሞቱ 319 ሰዎች መመዝገባቸው ይታወሳል።

    ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃች አገር ጣሊያን ናት። በዓለማችን ላይ 8ሺህ 758 ያህል ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኛው ሞት የተመዘገበው በቻይና ነው።

    በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእስያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።