ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ ከአሁን በኋላ በአዲሱ ስሟ እንደምትጠራ አስታወቀች
በቀሪው ዓለም 'ተርኪ' ተብላ የምትታወቀው ቱርክ በሰሟ ላይ ማሻሻያ ማድረጓን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቅርባ ተቀባይነት በማግኘቱ ከአሁን በኋላ ‘ተርኪዬ’ በሚል እንደምትጠራ አሳወቀች።
እራሷን በዓለም ዙሪያ በአዲስ ገጽታ ለማስተወወቅ የተነሳችው ቱርክ፣ በፕሬዝዳንቷ አማካይነት ባስተዋወቀችው ዘመቻ በስሟ ላይ ያደረገችውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ።
ባለፈው ኅዳር ወር ላይ "ተርኪዬ የሚለው ስያሜ የቱርክን ሕዝብ ባህል፣ ሥልጣኔ እና ዕሴቶችን በበለጠ የሚወክል አገላለጽ ነው” በማለት ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ተናግረው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስያሜ ለውጡን ጥያቄ በዚህ ሳምንት ከተቀበለ በኋላ፣ ወዲያውኑ ለውጥ ማድረጉን አሳውቋል።
አብዛኞቹ ቱርካውያን አገራቸውን 'ተርኪዬ' ብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው 'ተርኪ' የሚለው ስያሜ በዓለም ዙሪያ በስፋት ይታወቃል።
የስያሜ ለውጡ ይፋ ከተደረገ በኋላ የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋም የሆነው 'ቲአርቲ' ወዲያውኑ ነበር ለውጥ ያደረገው።
ለለውጡ ምክንያት ብሎ ካስቀመጣቸው ነገሮች መካከል ‘ተርኪ’ የሚለው ስያሜ ምዕራባውያን በገና እና በአዲስ በዓል ወቅት ለምግብ ከምትቀርበው የዶሮ ዝርያ ጋር መያያዙ እንደሆነ፣ በተጨማሪም በኬምብሪጅ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ላይ ለቃሉ ተሰጠው ትርጉም እንደሆነም አመልክቷል።
መንግሥት ቱርክን በአዲስ ስያሜ ለማስተዋወቅ በጀመረው ዘመቻ በአገሪቱ ተመርተው ወደ ውጪ የሚላኩ ሁሉም ምርቶች ላይ አዲሱ ስያሜ እንዲሰፍር የተደረገ ሲሆን፣ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮም "ሄሎ ተርኪዬ" የሚል የቱሪዝም ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
ይህ እርምጃም በበይነመረብ መድረኮች ላይ የተደበላለቀ ምላሽ እያስተናገደ ነው።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ድጋፋቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ አገሪቱ በምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ሆና በመጪው ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ ፕሬዝዳንቱ እየተዘጋጁበት ባሉበት ወቅት ለውጡ መደረጉ ትኩረትን ወደሌላ አቅጣጫ ለመሳብ የተደረገ ነው ሲሉ ይተቻሉ።
በዓለም ላይ አገራት ስማቸውን መቀየራቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም።
ከሁለት ዓመት በፊት ኔዘርላንድ ሆላንድ የሚለውን ስያሜዋን የተወች ሲሆን፣ ከእሷ በፊት ደግሞ ከግሪክ ጋር በተከሰተ ፖለቲካዊ ውዝግብ የተነሳ መቂዶኒያ ስሟን ወደ ሰሜን መቂዶኒያ ቀይራለች።
በተጨማሪም አፍሪካዊቷ ስዋዚላንድም ከአራት ዓመት በፊት ስያሜዋን ኢ-ስዋቲኒ ብላለች።
በታሪክ ውስጥም ፐርሺያ ወደ ኢራን፣ ሲአም ወደ ታይላንድ እንዲሁም ሮዴዢያ ወደ ዚምባብዌ ስማቸውን ቀይረዋል።