ኤሎን መስክ እና ልዑል አንድሪው በወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ኤፕስታይን ሰነድ ውስጥ ስማቸው ተገኘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ቢሊዮነሩ ኤሎን መስክ እና የንጉሥ ቻርለስ ታናሽ ወንድም ልዑል አንድሪው በወሲብ ንግድ ወንጀል የተፈረደበትን ጄፍሪ ኤፕስታይንን በተመለከተ እና በዲሞክራት የኮንግረስ አባላት በተለቀቀ አዲስ ሰነድ ውስጥ ስማቸው ተጠቅሶ ተገኘ።

የጄፍሪ ኤፕስታይን ወራሾች ለኮንግረስ የቁጥጥር ኮሚቴ የሰጧቸው ሰነዶች፤ ኤሎን መስክ በአውሮፓውያኑ 2014 በታህሳስ ወር ወደ ኤፕስታይን ደሴት ተጋብዞ እንደነበር አመልክተዋል።

በተናጠል በግንቦት ወር 2000 ከኒው ጀርሲ ወደ ፍሎሪዳ በረራ በተደረገው የበረራ ዝርዝር ውስጥ ልዑል አንድሪው ከተሳፋሪዎቹ መካከል ይጠቀሳል።

እ.አ.አ በግንቦት 2000 ከኒው ጀርዚ ወደ ፍሎሪዳ በተደረገ በረራ ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎችን ዝርዝር የያዘ ሌላ ሰነድ ደግሞ ልዑል አንድሪው ከተጓዦቹ መካከል እንደነበሩ አሳይቷል።

መስክ እና ልዑል አንድሪው ስለ መዝገቡ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ልዑል አንደሪው ከዚህ ቀደም የትኛውንም ዓይነት ጥፋት 'ፈጽመዋል' መባሉን ውድቅ አድርገዋል። መስክ ደግሞ ኤፕስታይን ወደ ደሴቱ ጋብዞት እንደነበረ ነገር ግን ግብዣውን ውድቅ ማድረጉን ከዚህ ቀደም ተናግሯል።

የጄፍሪ ኤፕስታይን ወራሾች ይህንን ዓይነቱን ሰነድ ሲያቀርቡ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

በኮንግረስ የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑ ዲሞክራቶች እንደገለጹት አዲሶቹ ሰነዶች የስልክ መልዕክት ልውውጦችን፣ የበረራ መዝገቦች እና የተሳፋሪዎች ዝርዝርን፣ የፋይናንስ ዝውውር መዝገቦችን እንዲሁም የኤፕስታይንን ዕለታዊ መርሃ ግብሮችን የያዙ ናቸው።

ለሕዝብ ይፋ የተደረጉት መዝገቦች ከመስክ እና ልዑል አንድሪው በተጨማሪ ሌሎች ስመ ጥር ሰዎችንም ጠቅሰዋል።

የቀድሞ የዶናልድ ትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ባነን እና የኢንተርኔት ሥራ ፈጣሪው ፒተር ቲል በሰነዶቹ ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።

በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 2014 የተመዘገበ አንድ ሰነድ፤ "ማስታወሻ፤ ኤሎን መስክ ታህሳስ 6 ወደ ደሴት (ይመጣል?)" የሚል ንግግርን አስፍሯል።

አንድሪው የተጠቀሱበት የበረራ መዝገብ ደግሞ ልዑሉ በግንቦት 2000 ከኤፕስታይን እና ከባልደረባው ጊዝላኔ ማክስዌል ጋር ከኒው ጀርዚ ተነስተው ፍሎሪያ ወደሚገኘው ዌስት ፓልም የባሕር ዳርቻ መጓዛቸውን ያመለክታል።

ማክስዌል ታዳጊ ሴቶችን ለወሲብ በማዘዋወር ወንጀል ከኤፕስታይን ጋር በመተባበሯ በ2021 ተፈርዶባታል።

ብዙ ስርዞች የተደረጉበት አንድ የፋይናንስ መዝገብ በ2000 የካቲት እና ግንቦት ወራት 'አንድሪው' ለተጠቀማቸው የማሳጅ አገልግሎቶች ክፍያ መፈጸሙን ያሳያል።

የቤተ መንግሥት መዝገቦች፣ ፎቶግራፎች እና የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ልዑል አንድሪው ሰነዱ ላይ በተጠቀሱትት ቀናት አካባቢ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ነበር።

ይሁን እንጂ በኤፕስታይን የፋይናንስ መዝገብ ላይ 'አንድሪው' በሚል የተጠቀሰው ልዑሉን ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም።