በክፍያ ምክንያት አኩርፎ የነበረው የካናዳ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ልምምድ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካናዳ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከፓናማ አቻው ጋር የነበረውን የወዳጅነት ጨዋታ ሰርዟል።
በዚህም ሳያበቃ "እንደውም ልምምድ አናደርግም" ሲል አምጿል።
ነገሩ ወዲህ ነው።
የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ለዓለም ዋንጫ በመድረሳቸው የሚሰጣቸው ገንዘብ እንዴት ነው የሚከፈለን በሚለው ከእግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል ጋር ሊስማሙ አልቻሉም።
አሁን ግን "ጥያቄዎቻችን ባይመለሱም" ወደ ልምምድ እንመለሳለን ብለዋል።
ተጫዋቾቹ የካናዳ እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ካናዳ ሶከር "አራክሶናል" ይላሉ።
ብሔራዊ ቡድኑ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከእግር ኳስ ማኅበሩ ኃላፊዎች ጋር ብንወያይም "ከስምምነት አልደረስንም" ብሏል።
መግለጫው አክሎ ከስምምነት ለመድረስ "ተጨማሪ ድርድሮች ይኖራሉ" ሲል ገልጧል።
ካናዳ ሶከር በበኩሉ "ከስምምነት ለመድረስ ስብሰባ አመቻችተናል" ሲል በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ላይ አሳውቋል።
ካናዳ፤ ኳታር በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላትን ነጥብ አምጥታለች።
ካናዳ በዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ስትሳተፍ ይህ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ሜክሲኮ ባዘጋጀችው የ1986ቱ ዓለም ዋንጫ ነበር።
ካናዳ ሶከር ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ በማለፉ ስላበረከተው ሽልማት የሚጋጩ ዘገባዎች ሲወጡ ነበር።
ቲኤስኤን የተባለው የዜና አውታር እንደዘገበው ካናዳ ሶከር ከፊፋ ከሚያገኘው ገንዘብ 10 በመቶውን ለተጫዋቾች ለመስጠት ቃል ገብቷል።
ይህ መቶኛ ወደ ገንዘብ ሲቀየር 10 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ነው።
ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት ካናዳ ሶከር እኔ ቃል የገባሁት 60 በመቶ ነው ሲል ለቲኤስኤን ተናግሯል።
ይህ 60 በመቶ ገንዘብ ለሴቶችና ወንዶች ብሔራዊ ቡድን እኩል የሚከፋፈል ነው።
ነገር ግን ተጫዋቾቹ ከ75 አስከ 100 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ይሰጠን ሲሉ ይጠይቃሉ።
የካናዳ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ሌላኛው ተጫዋቾቹን ያስቆጣው ነገር ለእያንዳንዱ የብሔራዊ ቡድን አባል ሁለት የቤተሰብ አባል ብቻ የዓለም ዋንጫ ቲኬት መሰጠቱ ነው።
ተጫዋቾቹ "ገቢውን እኛ እያመጣነው ተጠቃሚ ግን አልሆንንም" የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ይነሳል።
ካናዳ በኮንካፍ ኔሽንስ ሊግ ውድድር ሐሙስ ዕለት ከኩራዎሳ ፍልሚያ ይጠብቃታል።












