በፈረንሳይ ሰርግ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሙሸራዋ ተገደለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡብ ምስራቃዊ ፈረንሳይ በምትገኘው አቪንዮን ከተማ አንድ መንደር ውስጥ በተዘጋጀ የምሽት የሰርግ ድግስ ላይ ጭንብል ያደረገ ሰው በከፈተው ተኩስ ሙሽራዋ በጥይት ተመትታ እንደሞተች ባለስልጣናት ተናገሩ።

ጉልት በተባለው መንደር በተፈጠረው በዚህ ክስተት ጥቃት ፈጻሚ እንደሆነ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብም በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገድሏል።

ሙሽራው እና አንድ የ13 ዓመት ልጅም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በደርዘን የሚቆጠሩ የፖሊስ መኮንኖች እና አንድ ሄሊኮፕተር በድርጊቱ የተሳተፉ እና ያመለጡ ቁጥራቸው ያልታወቀ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፍለጋ እያካሄዱ ነው።

እንደ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ጥቃቱ ከአደንዛዥ እፅ ጋር የተያያዘ የበቀል እርምጃ ሊሆን ይችላል። ባለስልጣናቱ በግድያ እና በግድያ ሙከራ ወንጀሎች ምርመራ ጀምረዋል።

እሁድ ሌሊት አስር ሰዓት ተኩል አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ጥቃት አድራሾች ተኩስ የከፈቱት የ27 ዓመቷ ሙሽራ እና የ25 ዓመቱ ሙሽራ ከድግሱ አዳራሽ እየወጡ በነበረበት ሰዓት እንደሆነ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ በሙሽሮቹ መኪና ተገጭቷል። የአቪንዮን አቃቤ ህግ ፍሎረንስ ገልቲር የገለጹት ግን ተጠርጣሪው "በተኩስ ልውውጥ" ወቅት እንደተመታ ነው።

በተሽከርካሪ ከመጡ በኋላ በህይወት የተረፉት ጥቃት ፈጻሚዎች፤ ከተኩሱ በኋላ ከአካባቢው የሸሹት በእግር እንደሆነ አቃቤ ህግ ተናግሯል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት በአዳራሹ ውስጥ 28 ሰዎች እንደነበሩ ፖሊስ ገልጿል። አንዲት ግለሰብ አነስተኛ ጉዳት ደርሶባታል።

ከንቲባ ዲዲየር ፔሬሎ እንደተናገሩት፤ መጋቢት ላይ አዳራሹ "ለሰርግ የተያዘው በአካባቢው ነዋሪ ባልሆኑ ሰዎች" ነው።

"ተበሳጭቻለሁ" ያሉት ከንቲባው፤ "ከተማዋ ቅርብ ነበርን፤ የት እንደሆነ መናገር አልችምን ነገር ግን ከዚህ ቀደምም እንደዚህ አይነት ነገር ተመልክተናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

በአካባቢው የሚገኝ እና 50 ዓመት ያስቆጠረ ሬስቶራንት ባለቤት፤ የተፈጸመው ጥቃት አንድ ሺህ ገደማ ነዋሪዎችን ለያዘው መንደር "መጥፎ ስም" ያሰጠዋል ብለዋል።

ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፤ "የመጨረሻው ትልቅ የሚባል ክስተት በመንደሩ ተፈጠረው ከ125 ዓመታት በፊት ነበር" ሲሉ መናገራቸውን ኤኤፍቢ ዘግቧል።