“አሁንም ጉንጬን ያመኛል”፡ ክሪስ ሮክ በአዲሱ ሥራው ስለዊል ስሚዝ ጥፊ ከተናገረው

ክሪስ ሮክ በዊል ስሚዝ በጥፊ ሲመታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ኮሜዲያን ክሪስ ሮክ ስለዝነኛው የዊል ስሚዝ ጥፊ ይህን ብሏል፡ “በጣም ያማል እንጂ።”

የ58 ዓመቱ ክሪስ ሮክ አዲስ ሥራውን ኔትፍሊክስ በተሰኘው የፊልም ማሰራጫ ጣቢያ ለቋል።

ክሪስ ሮክ በዚህ ሥራው በፈረንጆቹ 2022 በታላቁ የፊልም ሽልማት ሥነ-ሥርዓት መድረክ ላይ ከዊል ስሚዝ ስለቀመሰው ጥፊ በዝርዝር ያወራል።

“ሰዎች ቃል ከተግባር በላይ ያማል ይላሉ። እኚህ ሰዎች ጥፊ ያልቀመሱ መሆን አለባቸው” ሲል ቀልዷል።

ዝነኛው የሆሊውድ ኮከብ ዊል ስሚዝ የሙያ አጋሩ ክሪስ ሮክን በጥፊ እንዲመታ ያደረገው “ውስጤ ሲብላላ የቆየ ንዴት” ማለቱ ይታወሳል።

ዊል ስሚዝ ሊያስታውሳት በማይፈልጋት ምሽት ክሪስ ሮክን በጥፊ ከለጋው በኋላ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ተብሎ የኦስካር ሽልማት ማንሳቱ አይዘነጋም።

በወቅቱ የተፈጠረው ክስተት አሜሪካዊያን አመፅ ይወዳሉ ወደሚል የውይይት ርዕስ ተሻግሮ ነበር።

ክሪስ ሮክ በታዋቂ የሆሊውድ ሰዎች እና በዓለም ሕዝብ ፊት ፊት እስኪቀላ የቀመሰውን ጥፊ ተከትሎ ከዊል ስሚዝ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ አለመግባቱ በብዙዎች አስሞግሶታል።

ሮክ፤ ከጥፊው በኋላ ኔትፍሊክስ ላይ በለቀቀው የኮመዲ ሥራ የዊል ስሚዝን መዳፍ፣ ፖሊቲካና ሜጋን መርኽልን አንስቶ አስተያየቱን በቀልድ አስተላልፏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ይህን ሥራዬን ማንንም ሳላስከፋ ማጠናቀቅ ነው የምፈልገው። ምክንያቱም ማንን ላስቀይም እንደምችል አላውቅም” ሲል ስለጥፊው ዊል ስሚዝን በነገር ወጋ አድርጓል።

ክሪስ ሮክ በሥራው አሜሪካዊያን ምን ያህል እንደተከፋፈሉም አውግቷል።

“አሁን ያለችው አሜሪካ ቅጥ አምባሯ ጠፍቷል። ሩሲያዊያን ቢመጡ እስቲ የሚሉትን እንስማቸው ማለታችን አይቀርም።”

ኮመዲያኑ ብዙ ርዕስ ከዳሰሰ በኋላ ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን የዊል ስሚዝ ጥፊ በተመለከተ ቀልድና ቁም ነገር አጋርቷል።

“ሰዎች 'ጥፊው አመመህ ወይ?' ሲሉ ይጠይቁኛል። እስካሁን ጉንጬን ያመኛል። ሰመርታይም የተባለው ሙዚቃ አሁንም ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል።”

ሰመርታይም በፈረንጆቹ 1991 ዊል ስሚዝ የለቀቀው ነጠላ ዜማ ነው።

“ጥፊውን እንደ ማኒ ፓኪያዎ [ፊሊፒኖ ቦክሰኛ] ነው የተቀበልኩት” ሲል በሥፍራው የነበረው ታዳሚ በሳቅና ጭብጨባ አጅቦታል።

ክሪስ ሮክ እንደሚለው ዊል ስሚዝ በወቅቱ ያሳየው ባሕሪ እሱ ስለሚስቱ ስለቀለደ ሳይሆን ዊልና የሚስቱ ጃዳ ትዳራቸው የተረጋጋ አለመሆኑን የሚያመላክት ነው።

ዊልና ጃዳ ስሚዝ ስለትዳራቸው በግልፅ በማውራት ይታወቃሉ። ጃዳ፤ ፌስቡክ ላይ በምታሰራጨው ሬድ ቴብል ቶክ የተሰኘው ፕሮግራም ስለትዳራቸው ወጣ ገባ ብዙ ታወራለች።

“ሁላችንም ተማግጦብናል። እዚህ ያለ ሰው ሁሉም ተማግጦበታል። ነገር ግን ማንም በተማገጠበት ሰው ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ አላወራም” ሲል ክሪስ ሮክ ተናግሯል።

“እሱን እኔን ከጎዳኝ በላይ እሷ እሱን ጎድታዋለች።”

ሮክ በአዲሱ ሥራው ስለዊል ስሚዝ ጥፊ ማውጋቱን ተከትሎ ማኅበራዊ ሚድያው አስተያየቱን እየሰጠ ይገኛል።

እንደ ክሪስ ሮክ ያሉ ኮሜዲያን ምን ያክል ስቃይ ላይ ቢሆኑ ስቀው ያልፋሉ ሲሉ ብዙዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አንዳንዶች ደግሞ ክሪስ ሮክ ኢማኒሲፔሽን ስለተሰኘው አዲሱ የዊል ስሚዝ ፊልም የቀለደው ከልክ ያለፈ ነው ብለዋል።

ክሪስ ሮክ ሥራውን ሲያጠናቅቅ ለምን ጥፊውን በፀጋ እንደተቀበለ ይህን ብሏል።

“ቤተሰብ አለኝ። በሥርዓት ነው ያደግኩት። ቤተሰቦቼ ምን እንዳስተማሩኝ ታውቃላችሁ? 'ምንም ቢመጣ በነጮች ፊት አትደባደብ' ብለው ነው የመከሩኝ።”