ሊቨርፑል ከዩናይትድ፡ የዛሬ ፍልሚያ ከቴን ሃግ ይለቅ ለክሎፕ ወሳኝ የሆነው ለምንድነው?

ዘንድሮ ለሊቨርፑል አራተኛ ሆኖ መጨረስ ትልቅ ውጤት ነው። ለዚህ ነው እሑድ ዕለት አንፊልድ ላይ የሚደረገው ፍልሚያ ከዩናይትድ ይልቅ ለሊቨርፑል የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ይላል ዳኒ መርፊ።
ማንችስተር ዩናይትድ እስከ አራተኛ ለመጨረስ የሚያስችል ሥፍራ ላይ ነው ያሉት። አሁን ያላቸው አቋም ጥሩ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሶስተኛ ደረጃ ያለከልካይ መቆናጠጣቸውም ነው።
ቀያዮቹ ሰይጣኖቹ በዚህ ዓመት አንድ ዋንጫ አንስተዋል። ሌላ ዋንጫ ለመጨመር ደግሞ አቅደዋል።
ዛሬ ምሽት የሚያመጡት ውጤት መጥፎ ቢሆን እንኳ፤ ደጋፊዎቻቸው እንደ ሌላው ጊዜ የሚከፉ አይመስለኝም ይላል መርፊ።
ነገር ግን እውነታው ለሊቨርፑል ሌላ ነው።
የዩርገን ክሎፕ ሊቨርፑል በዘንድሮው የውድድር ዘመን አቋም እጅግ እየዋዠቀ ነው። በተለይ ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊግ በሪያል ማድሪድ የደረሰባቸው ከባድ ሽንፈት፤ ያላቸው ብቸኛ ተስፋ በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አራተኛ መጨረስ ብቻ መሆኑን አሳይቷል።
ሊቨርፑሎች እስካ አራት ባለው ደረጃ ያጠናቅቃሉ ወይስ አያጠናቅቁም የሚለው መጪውን ጊዜ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚወስን ነው።
ሊቨርፑል በሚቀጥለው ክረምት ከፍተኛ መልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው ይመስላል። አምስትና ስድስት ተጫዋቾች ለቀው አዳዲስ ፊት መምጠት አለበት።
ማንንም ያምጡ ማን በቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፋቸው የሚፈልጉትን ተጫዋች ለማምጣት ጥሩ ምክንያት ይሆናቸዋል።
ለዚህ ነው በሚቀጥለው ዓመት በቻምፒየንስ ሊግ መሳተፍ አለመሳተፋቸው ለሊቨርፑል የወደፊት ዕጣ ፈንታም አስፈላጊ የሚሆነው።
ሊቨርፑል ባለፈው ዓመት ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በመድረሱ 100 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ማግኘት ችሏል። በዚህኛው ዓመት ደግሞ ለጥሎ ማለፍ በመድረሳቸው 40 ሚሊዮን ዩሮ አፍሰዋል።
ይህ ገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነው። በአውሮፓ ሊግ መጫወት ይህን የመሰለ ገንዘብ አያመጣም።
የቤሊንግሃም ዕጣ ፈንታ
ሊቨርፑል በሚቀጥለው ዓመት ቻምፒየንስ ሊግ መጫወት የማይችሉ ከሆነ ትላልቅ ተጫዋቾችን የመሳብ ዕድላቸው ጠባብ ይሆናል።
ለረዥም ጊዜ ከሊቨርፑል ጋር ስሙ ሲያያዝ የቆየው እንግሊዛዊው የቦሩሲያ ዶርትመንድ ተጫዋች ጁድ ቤሊንግሃም በዚህ የሚመዘን አይመስለኝም ይላል መርፊ።
ጁድ ቤሊንግሃም ወደ ሊቨርፑል መምጣቱ ለውጥ ይፈጥራል ብሎ የሚያስብ ከሆነ ቀያዮቹ ምንም ቢገጥማቸው ሊመጣ ይችላል።
ባለፈው ሰኔ 20ኛ ዓመቱን ያከበረው ቤሊንግሃም ወጣት በመሆኑ ለአንድ ዓመት ቻምፒዮንስ ሊግ ቢያመልጠው የሚቆጭ አይሆንም ሲል መርፊ ይገምታል።
ክሎፕ፤ ቤሊንግሃምን አሊያም ሌላ ትልቅ ተጫዋች ማምጣት ቢያቅተው እንኳ እስካሁን በሊቨርፑል በሠራው ሊኮራ ይገባል።
ዩርገን ክሎፕ በፈረንጆቹ 2015 ሊቨርፑልን ከያዙ በኋላ ቀያዮቹ በሁሉም የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ተሳትፈዋል።
እሑድ ዕለት አንፊልድ ላይ የሚፈጠረውም ምንም ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ምክንያቱም ገና ሊጉ ሊጠናቀቅ 13 ጨዋታዎች ይቀሩታል።
ከሊርፑል ጋር አራተኛ ደረጃን ለመያዝ የሚታገሉት ቶተንሃምና ኒውካስትልም የዋዠቀ አቋም እያሳዩ ነው።
ሊቨርፑል ዛሬ ቢሸነፍ የአራተኛ ደረጃ ተስፋው ጨለመ ማለት አይቻልም። ከቶተንሃም ጋር አንፊልድ ላይ ያላቸው ጨዋታም ወሳኝ ነው።
ነገር ግን ማንችስተር ዩናይትድን ማሸነፍ ከቻሉ ትልቅ የሞራል መነቃቃት ይሆናቸዋል ብዬ እገምታለሁ።
ዩናይትድ በሁሉም ውድድሮች ባለፉት 22 ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ነው ያስተናገዱት። እሱም ከሊግ መሪዎቹ አርሰናል ጋር በኤሜሬትርስ በተደረገው ፍልሚያ።
ዩናይትድ አቋማቸው ደክሟል በተባለበት ጨዋታ እንኳ ከመመራት ተነስተው የአሸናፊነት መንፈስ ሲያሳዩ ተስተውለዋል።
ማርከስ ራሽፈርድና ካዜሚሮ ለክለቡ በጣም አስፈላጊ ተጫዋቾች ሆነዋል።
ሊቨርፑል በያዝነው የውድድር ዘመን አንፊልድ ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት። ባለፈው ጥቅምት በሊድስ ዩናይትድ።
የእሑዱን ፍልሚያ ማን ይረታው ይሆናል የሚለው ተጠባቂ ነው።












