ልዑል ቻርለስ ‘አንድ ሚሊዮን ዩሮ በሻንጣ መቀበላቸውን’ አንድ ዘገባ ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዌልሱ ልዑል አንድ ሚሊዮን ዩሮ ከቀድሞው የኳታር ጠቅላይ ሚንስትር በሻንጣ መቀበላቸውን ሰንደይ ታይምስ ዘገበ።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ ይህ ሻንጣ፣ በሼኽ ሐሚድ ቢን ጃሲም ከተሰጡት ሦስት ሻንጣዎች አንዱ ነው። አጠቃላይ ገንዘቡም ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ይደርሳል ተብሏል።
የንጉሣዊያኑ ቤተሰብ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ ከሼኹ የተሰጡት ልገሳዎች በቀጥታ ወደ ልዑሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች መተላለፋቸውን ገልጿል። አካሄዱም ተገቢ ነበር ሲል ተካላክሏል።
ክፍያው ሕገ ወጥ ስለመሆኑ ምንም የተገለጸ ነገር የለም።
እንደ ሰንደይ ታይምስ ከሆነ፣ ልዑል ቻርለስ እአአ ከ2011 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ ሦስት ጊዜ ገንዘቡን በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።
አንደኛው ክፍያ በክላረንስ ሃውስ (የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሣዊያን ቤተሰብ መኖሪያ) መፈጸሙንም ዘግቧል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በፎርትነም እና በማሰን በገንዘብ የሞሉ ሻንጣዎች መሰጠታቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።
ክላረንስ ሃውስ ባወጣው መግለጫ “ከሼኽ ሐሚድ ቢን ጃሲም የተሰጡ ልገሳዎች የልዑሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከሆኑት ወደ አንዱ በቀጥታ ተላልፏል። ትክክለኛውን አስተዳደራዊ ሂደትም ተከትሏል” ብሏል።
ገንዘቡን የተቀበለው የዌልስ ልዑል የበጎ አድራጎት ነው።
ደርጅቱ “ሕይወትን መቀየር እና ዘላቂ ማኅበረሰብን መፍጠር” የሚል ዓላማ ያለው ነው። በአካባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ይሠራል።
ለጋሹ ሕጋዊ ነው ሲል ድርጅቱ ለሰንደይ ታይምስ ምላሽ ሰጥቷል። ኦዲተሮችም ክፍያውን አጽድቀውታል ሲል አክሏል።
ለልዑል ቻርለስ የሚደረጉ ድጋፎች በቅርብ ጊዜያት ትችት እያስተናገዱ ይገኛሉ።
ለአንድ የሳዑዲ እርዳታ ሰጪ የዩኬ ዜግነት እና የክብር ሽልማት ለማሰጠት ተሠርቷል በሚል ነው ትችቱ የተጀመረው።
ሜትሮፖሊታንት ፖሊስ ከልዑሉ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በተያያዘ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን በቅርቡ አስታውቋል።
ድርጅቱ ለምርመራው ተገቢውን ትብብር በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።
ክላረንስ ሃውስ በበኩሉ ልዑል ቻርለስ ከድጋፉ ጋር በተያዘያ ስለተነሳው የዜግነት ጉዳይ እንደማያውቁ አስታውቋል።
የልዑሉ ድርጅት የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ማይክል ፋውሴት በዚሁ ዙሪያ ምርመራ መከናወኑን ተከትሎ ሥራቸውን ለቀዋል።
“ከግብረ አበሮች” ጋር በመሆን ለቢሊየነሩ የንግድ ሰው ማሕፉዝ ማሪ ሙባራክ ቢን ማሕፉዝ የክብር ሽልማት ለማሰጠት መንቀሳቀሳቸው በምርመራ ተረጋግጧል።
የድርጅቱ የበላይ አካላት ጉዳዩን እንደሚያውቁ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም ሲል ድምዳሜውን አስቀምጧል።












