ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኪራይ አህያ ንግድ ጀምረው ቢሊየነር የሆኑት ኢትዮጵያዊ
ቶኩማ ፊጤ እባላለሁ፣ ተወልጄ ያደግኩት በምዕራብ ሸዋ ዞን በባኮ ትቤ ወረዳ፣ ቦኖ በሚባል ገጠር ውስጥ ነው።
እዚያም ለቤተሰቦቼ ከብት ስጠብቅ ቆይቼ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ተላኩኝ።
ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ በአእምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰው ነገር ቢኖር የንግድ ሥራ ነው።
የንግድ ሥራን በደንብ የጀመርኩትም የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው።
በዚያን ጊዜ አህያ ተከራይቼ፣ ከገጠር ወደ ከተማ እህል በማመላለስ እሸጥ ነበር።
ከከተማ ስመለስ ደግሞ እንደ ጋዝ፣ ዘይት፣ ጨው፣ ቡና የመሳሰሉትን ነገሮች በመግዛት አምጥቼ እሸጥ ነበር።
በውስጤ ትልቅ ራዕይ ነበረኝ። ጠንክሬ ከሠራሁ አንደምለወጥ አምን ነበር።
ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ወረዳ ከተማ በመጣሁበት ጊዜ የበለጠውኑ እየተጠናከርኩ ራሴን መቻል ጀመርኩ።
የሚያስፈልጉኝን ወጪዎች ከመሸፈን አልፌ ቤተሰቦቼን መደጎም የቻልኩት በዚህ ጊዜ ነው።
ፈቃድ ያለው ንግድ
ከዚህ በፊት ከአንድ ገበያ ወደ ሌላ ገበያ በመሄድ ያገኘሁትን ነገር ሁሉ እሸጥ ነበር።
በኋላ ላይ ገን አንድ አዲስ ሃሳብ በአእምሮዬ ሽው አለ።
እርሱም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ መስራት የሚል ነበር። በዚህም መሰረት ወደ አምቦ ሄጄ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መጻሕፍት ለመግዛት የሚያስችለኝን የንግድ ፈቃድ አወጣሁ።
በዚህም መሠረት ያገለገሉትን ወረቀቶችን ሰብስቦ ለፋብሪካ ማቅረብ የሚያስችለኝን ንግድ የጀመርኩት በዚሁ ነበር።
ያገለገሉ መጽሐፍትን በየትምህርት ቤቱ እየዞርኩ መግዛት ጀመርኩ።
ይህንን ፈቃድ በማወጣበት ሰዓት በባንክ የቁጠባ ሂሳብ ደብተሬ ላይ የነበረኝ 72 ብር ብቻ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜም እነዚያን መጽሐፍት ገዝቼ የጫንኩት ኖኖ ቁንባ ከሚባል ወረዳ ነበር።
የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መጽሐፍት ከተጣሉበት እና ከተከማቹበት በማሰባሰብ በመኪና ጭኜ ወሰድኩኝ።
በዚያን ቀን ለረዱኝ ሰዎች፣ ለጨረታ ኮሚቴዎች፣ ለመኪና ማስጫኛ የሚሆን የክፍያ ገንዘብ አልነበረኝም።
እሁን እንጂ ሸጬ እከፍላችኋለሁ ብዬ ለምኜ አሳመንኳቸው።
ከዚያ በኋላ መጽሐፍ የተባለ፣ አልያም ያገለገለ ወረቀት ከያለበት ዞሬ ያላሰባሰብኩበት የኦሮሚያ ዞን የለም ማለት ይቻላል።
ይህንን የማሰባስበውን ወረቀት ደግሞ ለወረቀት ፋብሪካዎች አስረክባለሁ።
ለእኔ ትልቅ ሥራ ነው ብዬ የጀመርኩት እንግዲህ እርሱን ነበር።
ያገለገሉ ብረታ ብረቶች የመሰብሰብ ሥራ
ያገለገሉ መጽሐፍትን ሰብስቦ መሸጡ ጥሩ ገቢ ባገኝበትም ቀጣይነት ያለው ሥራ ስላልነበረ ሌላ ንግድ ሃሳብ ማሰላሰል ጀመርኩ።
በዚህም መሰረት ቀጥሎ የከጀመርኩት ሥራ ያገለገሉ ብረታ ብረቶችን መሰብሰብ ነው።
በገጠር አካባቢዎች በመዞር ከገበሬዎች ላይ አሮጌ በርሜሎችን፣ የተሰባበሩ መጥረብያዎችን እና የመሳሰሉትን ማሰባሰብ ጀመርኩ።
እነዚህን የማሰባስባቸውን ብረታ ብረቶች የማቀርበው ደግሞ ለአቢሲኒያ ብረታ ብረት ፋብሪካ ነበር።
ይህ የወዳደቁ ብረታ ብረቶችን የማሰባሰብ ሥራ ከሌሎች የተሻለ ስለነበር ጥሩ ገቢ ማግኘት ጀመርኩ።
ይሁን እንጂ አንደ እርሱን እየሰራሁ፣ እንደለመደብኝ ቀጥሎ ምን መሥራት እንዳለብኝ ወደ ማሰላሰል ገባሁ።
የኤጀንሲ ሥራ
ሦስተኛውን የንግድ ፈቃድ ያወጣሁበት ሥራ የኤጀንሲ ፈቃድ ነበር።
ይህንንም ያሰብኩት ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች ሥራ ይፈጥራል በሚል አስተሳሰብ ነበር።
በመጀመሪያ ስለ ኤጀንሲ ብዙ እውቀት አልነበረኝም።
ስለሆነም በደንብ አጥንቼ አንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ እና ፈቀድ ለማውጣት ሦስት ዓመታት ወስዶብኛል።
እንዲህ ዓይነቱን የኤጀንሲ ሥራ የማውቃቸው ሰዎች እየሰሩ ስላልነበረ ለመልመድ ትንሽ ተቸግሬ ነበር።
በመጨረሻ ግን ተሳክቶልኝ በአዲስ አበባ ውስጥ በዚህ የኤጀንሲ ሥራ ፈቃድ አገኘሁ።
በዚህን ሰዓት ነበር በሁለት ነገሮች ስኬታማ መሆን እንደምችል የተረዳሁት።
አንደኛው የቢዝነስ ሥራዬን ማሳደግ እንደምችል ሁለተኛው ደግሞ ለሌላቸው ዜጎች ሥራ መፍጠር እንደምችል አመንኩ።
ይህ የኤጀንሲ ሥራ በወኪልነት ለድርጅቶች ሠራተኛ መቅጠር ነበር።
ለምሳሌ እንደ ጥበቃ፣ የጽዳት ሥራ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በዚህም መሠረት እኛም ከተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን ለሥራ እንመለምል ነበር።
እነዚህንም ሰዎች አውቶብስ ተራ ድረስ ሄዶ በመቀበል፣ ወዳዘጋጀንላቸው መጠለያ በመውሰድ፣ ሥልጠና በመስጠት ወደ ተቀጠሩበት ስፍራ እናደርሳለን።
በመሆኑም ይህ ሥራ ውስብስብ እና ከባድ ነበር።
በተለይም ከገጠር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች አንዳንዶቹ ቋንቋ ስለማይችሉ ይቸገራሉ።
ከተማም ለመልመድ የሚቸገሩም ሰዎች ነበሩ።
ይሁን እንጂ ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ ቦታ ለመጡ ለ32000 ሰዎች የሥራ እድል እንዲያገኙ አድርገናል።
ከእነዚህም መካከል 8500 የሚሆኑት በራሴ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ደመወዝ የምንከደፍላቸው ሠራተኞች ናቸው።
ሌሎቹ ደግሞ ሥራቸውን እየሰሩ ትምህርታቸውን በመከታተል የመንግሥት ሥራ ሲቀጠሩ፣ ለትምህርት ወደ ውጪ አገር የሄዱ ጭምር ይገኙበታል።
ትላልቅ ጨረታዎች
በአሁኑ ጊዜ ድርጅታችን 29 ፈቃዶች አሉት። ከእነዚህ መካከል 18 ፈቃዶች ከውጪ አገር እቃዎችን የምናስገባበት ሲሆን፣ 11 ፈቃዶች ደግሞ በአገር ውስጥ የተለያዩ ሥራዎች የምንሰራበት ነው።
በአገራችን ውስጥ በክልሎችም ሆነ በፌደራል ደረጃ እንደ ቴሌ፣ መብራት ኃይል እና ውሃና ፍሳሽ ያሉ ተቋማት የሚያወጧቸው ጨረታዎች የከፍተኛ ብር ነው ጨረታ የሚያወጡት።
በእንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ስንጫረት ደግሞ ከብዙ ባለሀብቶች እና ከታዋቂ ሰዎች ጋር ነው የምንወዳደረው።
እንደዚህ አይነት ትላልቅ ጨረታዎች ላይ ደግሞ እንደኛ ዓይነት ብዙ ሰው አይሳተፍም።
ይህ ደግሞ ተጽዕኖም አለ። ይሁን እንጂ እኔ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን መሞከር እወዳለሁ። አንዳንዴ ሰባት ጊዜ ወድቀን በስምንተኛው ይሳካልናል።
ሌሎቹ ደግሞ አትችሉም ይሉናል። እኛም ሰምተን እንደምንችል አሳይተናቸዋል።
እንደ እነዚህ ያሉ ጨረታዎች ደግሞ በቢሊዮኖች በሚተመን ብር የሚካሄድ ጨረታ ነው።
በአብዛኛውም ጊዜ ደጋግመን በመሞከር በመጨረሻም ይሳካልናል።
በዓመትም እንደዚህ ዓይነት ያሉ እስከ 50 ጨረታዎች ላይ እንሳተፋለን።
ጉዞ ወደ ቢሊየነርነት
በአሁኑ ሰዓት ሁለት ትልልቅ ድርጅቶች አሉን። እነርሱም ቲኤፍጂ ጄነራል ትሬዲንግ እና ቶኩማ ጄኔራል ትሬዲንግ ይባላሉ።
እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለያዩ የሕንጻ ግንባታ በማካሄድ ላይ እንገኛለን።
ይህንን ስናደርግ ግን አንዲት ካሬ ሜትር እንኳ ከመንግሥት አልተሰጠንም። ሁሉንም በራሳችን ገንዘብ ገዝተን ነው የምናለማው።
በአሁኑ ሰዓት ያለኝ ሀብት ግንባታዎችን እና በባንክ ያለኝ ገንዘብ ተደማምሮ ቢያንስ 5 ቢሊየን 500 ሚሊየን ይጠጋል።
በቋሚነት ድርጅቴ ውስጥ የሚሰሩ 8500 ሠራተኞችም ደሞዝ እንከፍላለን። ልዩ የሚያደርገን አንዱ ነገር ከባንክ ተበድሬ አለማወቄ ነው።
የምሠራቸውን ማንኛቸውንም ሥራዎች በራሴ አቅጄ ነው የምሰራው።
ሰባራ ሳንቲም የባንክ ዕዳ የለብኝም።
ይህ ያለኝን ሀብት ደግሞ የራሴ ብቻ አይደለም። የሠራተኞቼ እና የሕዝቡም ነው ብዬ አምናለሁ።
በዚህም የተነሳ በዓመት በሚሊየን ብር የሚቆጠር ለተለያዩ ወገኖች ድጋፍ እንዳርጋለን።
ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በባኮ ወረዳ 26 ኪሎ ሜትር መንገድ በራሳችን ወጪ አሰርተናል።
በአሁኑ ጊዜ በባኮ ገጠር የጀመርኩት ሥራ ተስፋፍቶ ዱባይና አሜሪካ ደርሷል።
እቅዴም ይህንኑ ሀብት በትሪሊየን እንዲደርስ ማድረግ ነው።
መንገድ ዳር ያደርኩበት ጊዜ ነበር
በማደግ ላይ ላሉ ወጣቶች የማስተላልፈው ምክር ቢኖር “ሥራ መናቅ የለባችሁም” የሚል ነው።
ሥራን ከትንሽ ነገር መጀመር አለባቸው። ሀብት ማፍራት በሂደት የሚመጣ ስለሆነ “በአንዴ ለምን ሀብታም አልሆንኩም” ብሎ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም።
በትንሽ በመጀመር እርሱኑ በማሻሻል ወደ ተሻለ ነገር በማሳደግ የሀብት ባለቤት ወደ መሆን ይደረሳል።
እኔ ንግድ በጀመርኩበት ሰዓት ከአንቦም ሆነ ከአዲስ አበባ ምንም ዘመድ አልነበረኝም።
አዲስ አበባ መጥቼ ለአልጋ ከፍዬ የማድርበት በማጣት መንገድ ላይ አድሬ አውቃለሁ።
ይሁን እንጂ ተቸግርያለሁ፣ ከስሬያለሁ ብዬ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም።
ይኸው እኔ የገጠር ልጅ ዛሬ በአንቦ እና በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን፣ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በመዘዋወር እቃዎችን ገዝቼ ወደ አገሬ አስገባለሁ።
ለዚህ ደግሞ ያበቃኝ ትዕግስትና ተስፋ አለመቁረጤ ነው ብዬ አስባለሁ።