ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መወያየታቸውን ገለጹ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቅርቡ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ዙሪያ መነጋገራቸውን ገለጹ።
ብሊንከን በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ግጭት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን አመልክተዋል።
ሁለት ዓመት የቆየውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማብቃት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ቁልፍ ሚና እንደነበራት ይነገራል።
ውይይቱን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትም ሆነ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በውጭ ጉዳይ ኃላፊው መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ውይይት መደረጉን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ እንዲሁም ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ በተጨማሪም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ሥራ ብሊንከን እውቅና ሰጥተዋል ብሏል።
በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን “ሁሉም የውጭ ኃይሎች ከአገሪቱ እንዲወጡ እና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት በአንድ ላይ እንዲከናወን” ማድረግን ጨምሮ የተደረሰው ስምምነት በቶሎ ተግባራዊ የመደረግን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል ብሏል።
በተጨማሪም አሜሪካ በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ የሚከናወነውን የቁጥጥር እና የማረጋገጥ ተግባር ጨምሮ በኅብረቱ ጥላ ስር ያለውን የሰላም ሂደት እንደምትደግፍ ብሊንከን ማረጋገጣቸውን መሥሪያ ቤታቸው አመልክቷል።
በትግራይ ውስጥ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ግጭቱ በውይይት መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩት ወገኖች መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሰየሟ ይታወቃል።
ባለፈው ሳምንት አንድ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት አገራቸው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት በሚያደናቅፍ የትኛውም ወገን ላይ አሜሪካ ጠንካራ ማዕቀብ እንደምትጥል ገልጸው ነበር።
በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ግጭቶች መቆማቸውን ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ መሆኑን የረድኤት ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ የበለጠ በሚቀላጠፍበት ሁኔታ፣ በወደሙ መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ ዙሪያ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ ድርድር ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ በሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ለማስፈጸም የሚያግዝ ቀጣይ ውይይት በኬንያ ናይሮቢ ከተደረገ በኋላ የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አዛዦች በስምምነቱ ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደት ላይ ተስማምተው ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. የትግበራ ሰነድ ፈርመዋል።