ባለቤቱን ለ12 ዓመታት በእስር ያስቀመጠው ግለሰብ በፈረንሳይ ተያዘ

ግለሰቦቹ የሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤት (አፓርታማ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ባለቤቱን በቤት ውስጥ እስር ለ12 ዓመታት ያህል ያስቀመጠው ጀርመናዊ ግለሰብ በፈረንሳይ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ግለሰቡ ጀርመናዊት የሆነችው ባለቤቱን ፈረንሳይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መኝታ ክፍል ውስጥ እንዳትወጣ በማድረግ በብረትና በሽቦም አጥሮባት ነበር ተብሏል።

ፖሊሶች በሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤት (አፓርታማ) መኝታ ክፍል ውስጥ ሲያገኟት ጸጉሯን ተላጭታ ከፊል እርቃኗን እንደነበረች የፈረንሳይ የፖሊስ ምንጭ ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው የግለሰቦቹ መኖሪያ ከጀርመን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ፎርባች በተሰኘችው ከተማ ነው።

የ55 አመቱ ግለሰብ ባለቤቱን በማገትና እና ሌሎች ወንጀሎችም በሷ ላይ ፈጽሟል በሚል በእስር ላይ ይገኛል።

የ53 ዓመቷ ባለቤቱ ስልክ ስታገኝ ጀርመን ወዳሉ ፖሊሶች እንደደወለችና መረጃውም ለፈረንሳይ እንዲተላለፍ እንደተደረገም ተገልጿል።

ባለቤቱ በተደጋጋሚ ስትጮህ የሰሙ ጎረቤቶች ግለሰቡን በጠየቁበት ወቅት የካንሰር ታማሚ እንደሆነችና በህመሙ ምክንያት እየጮኸች ነው ብሎ እንደነገራቸው የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ጎረቤቶቿን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

አሊሺያ የተባለች ጎረቤት የግለሰቧን ጩኸት በተደጋጋሚ ብትሰማም በህመሟ የተከሰተ እንደመሰላትና ውጭም አይታት እንደማታውቅ ለኤኤፍፒ ተናግራለች።

ሌላኛዋ ኤሪካ የተባለች ጎረቤት ግለሰቧን ካየቻት ምናልባት “ከ10 ዓመታት በላይ እንደሆነና” ሞታለች ወይም ቤት ቀይራለችም ብላ እንዳሰበች ተናግራለች።

ፖሊስ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ለባለቤቱ ምግብ የሰጠበትን ጊዜያት ጨምሮ ሌሎች ያደርጋቸው የነበሩ ነገሮችን ይጽፍበት የነበረውን ማስታወሻ ማግኘቱንም የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ግለሰቧ በተገኘችበትም ወቅት ጤንነቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ የአካባቢው አቃቤ ህግ ኦሊቪየር ግላዲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአፓርታማው ውስጥ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ድመቶች ነበሩ ተብሏል።

በመኖሪያ ቤታቸው ባለቤቱ እንዳትወጣ በሚል በፍርግርግ ብረቶች አጥሮባት እንደነበር የፈረንሳይ ሚዲያ የዘገበ ሲሆን ግለሰቡ በበኩሉ ድመቶቹ እንዳያመልጡ ለማድረግ ነው ሲል ተናግሯል።

በተጨማሪም ፖሊስ ባለቤቱን ሲያገኛት ምንም አይነት ደምም ሆነ አካላዊ የጥቃት ምልክቶች አልነበሩባትም ቢልም ቀደም ሲል የወጡ ዘገባዎች የሚያሳዩት ተቃራኒውን ነው።

ግለሰቡ ስራ እንደሌለውና ከዚህ ቀደም በጀርመን ኢንዱስትሪ ውስጥ ይሰራ እንደነበር ተናግሯል።

ተጠርጣሪው በምስራቅ ፈረንሳይ በምትገኘው ሜትዝ ከተማ ታስሮ እንደሚገኝም ተዘግቧል።