ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በታጠቁ ሃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ተጠየቀ
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠየቀ።
በሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው እንደሆነም ነው ኢሰመጉ መስከረም 17/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
እየደረሱ ያሉ ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሰዋል ያለው ኢሰመጉ በዚህም የበርካቶች ህይወት መቅጠፉን፣ የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል ብሏል።
በተጨማሪም ዜጎች ንብረታቸው እንደተዘረፈና እንደወደመ እንዲሁም ለእገታና መፈናቀል እየተዳረጉ እንደሆነም ነው በትናንትናው መግለጫው የጠቀሰው።
ከሰሞኑ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ባሰፈረው በዚህ መግለጫ በክልሉ ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ወረዳ ኤጀሬ ቀበሌ መስከረም 2/ 2016 ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አራት ሰዎች ተገድለዋል።
በኪራሙ ወረዳም በተመሳሳይ ቀን በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ቆስሏል።
መስከረም 4/ 2016 ዓ.ም ዕለትም ወደ ጊዳ ከተማ ይጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎች በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።
ታጣቂዎች ተሳፋሪዎቹ መንገድ ላይ እንዲወርዱ አድርገው ወንዶቹን ለይተው ‘ጋራ ዲቾ’ በምትባል ስፍራ በርካቶቹን ገድለዋል እንዲሁም አቁስለዋል ሲልም ኢሰመጉ በመግለጫው አካቷል።
ኢሰመጉ ሰላማዊ ዜጎችን እየገደሉ ነው ያላቸውን ታጣቂ ኃይሎች ያላቸውን አካላት በስም አልገለጸም።
የመንግሥት የጸጥታ አካላት በቄለም ወለጋ ዞን አንፍሎ ወረዳ ሱዲ ቀበሌ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 27/ 2015 ዓ.ም በፈጸሙት ጥቃት የሰው ህይወት አልፏል እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ኢሰመጉ የምስራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የአስተዳደርና ጸጥታ እና የሚሊሻ ዘርፍን ስለጉዳዩ የጠየቀ ሲሆን ዞኑ የሰው ህይወት መጥፋቱን እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን በቃል ማረጋገጡን አስፍሯል።
በክልሉ የቀጠሉ ጥሰቶች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣቱን የጠቀሰው ኢሰመጉ መንግስት የዜጎቹን የሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቋል።
በተጨማሪም የፌደራል እና የኦሮምያ ክልል መንግስታት የክልሉ ነዋሪዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የእለት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ እና በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ዜጎችን የመጠበቅ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
እንዲሁም በክልሉ በተደጋጋሚ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና የታጠቁ ኃይሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ውስጥ እጃቸው ያለበት አካላት በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲደረጉም ለመንግሥት ጥሪ ቀርቧል።