የናይጄሪያ ፖሊስ የክርስቶስን ዳግም ምጻት በሚያዚያ ወር ሲጠብቁ የነበሩ ሕጻናትና አዋቂዎችን ታደገ

ታትሟል

የናይጄሪያ ፖሊስ ሕጻናትን ጨምሮ 77 ሰዎች  ከሰሞኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመለስ ነው በሚል በጋራ ተሰብስበው ሲጠብቁበት ከነበረ ቤተ ክርስቲያን ነጻ እንዳወጣቸው ተናገረ።

እነዚህ ሰዎች ተሰብስበው የነበረው በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ኦንዶ ግዛት ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጻት በከፍተኛ ጉጉት ቀን ቆርጠው እየተጠባበቁ ነበር።

የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ከ77ቱ ሰዎች ከፊሎቹ ለወራት በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጥበቃ ቆይተዋል።

ብዙዎቹ ጌታ ኢየሱስ በሚያዝያ ወር ይመጣል በሚል የተነገራቸው ነበሩ።

የጌታ ኢየሱስን መምጣት በአካል ተገኝቶ ለማየት ትምህርታቸውን አቋርጠው በቤተ ክርስቲያኒቱ ለወራት የተቀመጡ ወጣቶችም ነበሩበት።

አንዲት እናት ለፖሊስ የልጆቿን መሰወር ከገለጠች በኋላ ነው ፖሊስ ባደረገው አሰሳ እነዚህ 77 ሰዎች በዚህ ቤተ ክርስቲያን የተገኙት።

ፖሊስ በኦንዱ ከተማ ቫለንቲኖ አካባቢ የሆል ባይብል ቢሊቨርስ ቸርች ከዚህ ክስተት በተያያዘ ምርመራ ከፍቶበታል።

የዚህ የጴንጤቆስጤ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ፓስተር ዴቪድ አኒፎዎሼ እና ምክትላቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በነዚህ አገልጋዮች ተታለዋል የተባሉት ተጎጆዎች በሚመለከታቸው በባለሥልጣናት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።

አንድ የፖሊስ ባልደረባ ስለጉዳዩ እንዳስረዱት ወጣቶቹን በማታለል ለወራት ጥበቃ ውስጥ ያስቀመጣቸው የዋናው ፓስተር ምክትል የሆነ ጆሲያ ፒተር አሱሙሳ የተባለ አገልጋይ ሲሆን ጌታ በሚያዚያ ስለሚመጣ ቤተሰባቸውን ጥለው በዚያ ቁጭ ብለው እንዲጠብቁ አሳምኗቸዋል።

በሚያዚያ ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይመጣ ሲቀር ግን መምጫ ቀኑን ወደ መስከረም ማዛወሩን ገልጦላቸው እየተጠባበቁ ነበር።

በጠቅላላው ፖሊስ በዚህ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ኢየሱስን ለማየት በሚል ከቤተሰባቸው ተሰውረው የተቀመጡ 26 ሕጻናትን፣ 8 አዳጊዎችን እና 43 አዋቂዎችን ነጻ አውጥቷቸዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጻት ቀን በነዚህ አማኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በቀራኒዮ ተራራ የመጀመርያ ምጻቱን ተከትሎ ከሞተ በኋላ ዓለምን በጽድቅ ሊፈርድ በሚያዚያ ዳግም ተመልሶ የሚመጣበት ቀነ ቀጠሮ ነበር።

ይህ ቀነ ቀጠሮ ወደ መስከረም ተዛውሯል ሲሉ ለልጆቹ የተናገሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ምክትል ፓስተር ናቸው።