ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉን አቀፍ ክልላዊ መንግሥት እንዲመሠረት ጠየቁ
በትግራይ ክልል የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል ጋር በተያያዘ ሁሉንም የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ክልላዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ አቀረቡ።
ክልላዊ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆኑት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ውናት (ውድብ ነፃነት ትግራይ) እና ባይቶና ዓባይ ትግራይ የተባሉት ፓርቲዎች ዛሬ አርብ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም. በመቀለ ከተማ በሰጡት የጋራ መግለጫ ነው ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት።
ፓርቲዎቹ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ዋነኛ አደጋ “ሥርዓት የወለደው ስንፍና ነው” በማለት “አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሲታመም የማይታመም መንግሥት ያስፈልገናል። ይህም የሚሆነው ሁሉንም ድርጅቶች ያካተተ እና ሕዝብን ማሰለፍ የሚችል መንግሥት ሲቋቋም ነው” ብለዋል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ትግራይን በብቸኝነት ሲመራ የቆየውን ህወሓትንም “ስንፍናው እየተጠራቀመ መጥቶ ማንነቱ የገለጠ ድርጅት ራሱን በዚህ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በማድረግ ለመቀጠል የሞት ሽረት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ሲሉ ከሰዋል።
ፓርቲዎቹ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት ህወሓት በአመራሮቹ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ 14ተኛውን ጉባኤውን እያካሄደ ባለበት ጊዜ ነው።
ሦስቱ የትግራይ ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በትግራይ መንግሥት ለማቋቋም ከሚጥር ማንኛውም አካል እንደሚሰለፉ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
የአምስት አስርት ዓመታት ዕድሜ ያለው ህወሓት ደም አፋሳሹን ጦርነት ከስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ሰበብ በአመራሮቹ መካከል ክፍፍል ተፈጥሮ ውዝግብ ውጥ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት “ለሥልጣን ሲባል በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ሹክቻ” ሕዝቡን ከባድ ስጋት ላይ እንደጣለው ያመላከቱት ፓርቲዎቹ “ሁለቱም ቡድኖች የጐጠኝነት አጀንዳ በማንሳት ሕዝቡን ጐትተው ለማስገባት እየሞከሩ ነው” በማለት ከሰዋል።
“ጉባኤውን የድርጅቱ አባላት ናቸው እያካሄዱ ያሉት። የትኛውም አካባቢ ከአንደኛው ወገን ጋር እንደቆመ ለማስመሰል እየተደረገ ያለውን አካሄድ እንቃወማለን” በማለት ሕዝቡ በሕብረት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ከመመለስ ጋር ተያይዞ ከምርጫ ቦርድ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የተገለጸውን “በልዩ ሁኔታ” መመዝገቡን እንደማይቀበለው እና ቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት መጠየቁ ይታወቃል።
ህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ጥያቄው ጉዳይ መቋጫ ሳያገኝ በዚህ ሳምንት 14ኛ ጉባኤውን እኣካሄደ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ስብሰባው ሕጋዊውን ሂደት የተከተለ ባለመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረው አሳውቋል።
በጉበኤው መካሄድ ላይ በህወሓት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚገኙበት ከ17 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና አብዛኞቹ የደቡባዊ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ የፓርቲው አመራሮች እና ካድሬዎች ጉባኤው ላይ ላለመሳተፍ ራሳቸውን አግልለዋል።
ከአንድ ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ሳያገኝ ጉባኤ ቢያካሂድ ዳግመኛ ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት እንዳለው አስጠንቅቀው ነበር።
ሦስቱ የትግራይ ክልላዊ ተቃዋሚ በሰጡት መግለጫም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የክልሉ ሕዝብ “በመቀለ እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ ሽኩቻ. . . ለቡድኖች ሥልጣን” ሲባል ወዳልተፈለገ ጦርነት እንዳይገባ ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ገልፀዋል።
ሦስቱ የትግራይ ክልል ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት እየተካሄደ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።