የትራምፕን ጉብኝት የተቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የለንደን ነዋሪዎች አደባባይ ወጡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት በዩናይትድ ኪንግደም የሚያደርጉትን ሁለተኛ ኦፊሴላዊ ጉብኝት የተቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን አሰሙ።

ከ50 በላይ የሚሆኑ ማኅበራት እና የእርዳታ ድርጅቶች በጥምረት ያሰናዱት 'ስቶፕ ትራምፕ ኮአሊዥን' የተባለው ሰልፍ ረቡዕ ከሰዓት ከ9፡00 ጀምሮ በለንደን ተካሂዷል።

'ዘረኝነትን እምቢ እንበል'፤ 'ትራምፕን እምቢ እንበል'፤ እንዲሁም 'እስራኤልን ማስታጠቅ ይብቃ' የሚሉ መፈክሮችን የፃፉ ሰልፈኞች አደባባይ ታይተዋል።

ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2019 በዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያው ጉብኝታቸውን ባደረጉ ወቅትም የተቃውሞ ሰልፍ ገጥሟቸው ነበር።

የለንደን ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ቢያንስ 5 ሺህ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፉን እንደታደሙ አስታውቋል።

ፖሊስ አክሎ 1500 የፖሊስ መኮንኖች ሰልፉን ለመቆጣጠር ተመድበው እንደነበር ገልጿል።

ዩናይት ዘ ኪንግደም የተሰኘው በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ በለንደን ከተማ ከተካሄደ ከቀናት በኋላ ነው የትራምፕ ጉብኝት ተቃውሞ የተሰናዳው።

ስቶፕ ትራምፕ ኮአሊዥን ከአየር ንብረት ለውጥ አቀንቃኞች እንዲሁም የፍልስጤም ድጋፍ እና የፀረ-ዘረኝነት ድርጅቶች ጥምረት ነው።

ከሰልፉ በፊት የጥምረቱ ቃል አቀባይ "ለትራምፕ እና ለዘረኝነት የሚያጎበድድ መንግሥት ለፋሺዝም በሩን የሚከፍት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ምንም እንኳ ትራምፕ በሁለት ቀናት ጉብኝታቸው ፓርላማውን ለመጎበኝት ባያቅዱም ሰልፈኞቹ ለንደን ውስጥ ፖርትላንድ ፕሌስ በተሰኘውና የሀገሪቱ ፓርላማ በሚገኝበት ስፍራ ነው ተቃውሟቸውን ያሰሙት።

በተጨማሪ ቢቢሲ ብሮድካስቲንግ ሀውስ አካባቢ ተሰባስበው የአሜሪካውን ፕሬዝደንት ጉብኝት አጥብቀው እንደሚቃወሙ በድምፅ ሲያሰሙ ነበር።

ፓርላማ አካባቢው በተሰናዳው ተቃውሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት እንደራሴዎቹ ጀረሚ ኮርቢን እና ዛራህ ሱልታና እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የትራምፕ እና ሕፃናትን ለወሲብ ብዝበዛ በማጋለጥ የሚታወቀው ጀፈሪ ኤፕስቲን ፎቶ ያለበትን ምስል ዊንድሶር ካስል ላይ በፕሮጀክተር ያስመለከቱ አራት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።