ህጻን ልጃቸውን ለ7 ዓመታት የቆለፉባት ጀርመናውያን ቤተሰቦች ምርመራ ተከፈተባቸው

የግለሰቦቹ ቤት

የፎቶው ባለመብት, ARD

ታትሟል

በጀርመን የስምንት ዓመት ህፃን ልጅ ላይ ለአመታት ከቤት እንዳትወጣ የቆለፉት እናት እና አያቶች ምርመራ ተከፈተባቸው።

የጀርመን አቃቤ ህግ ህጻኗ ለሰባት ዓመታት ያህል በቤት ውስጥ ተዘግቶባት እንደነበር አስታውቋል።

በመጨረሻም በያዝነው ዓመት መስከረም መገባደጃ ላይ ነፃ እንደወጣችና ለማደጎም ተሰጥታለች ተብሏል።

በህጻናት ደህንነት ላይ የሚሰሩ ባለስልጣናት ቀላል የሚባሉ እንደ ደረጃም መውጣትም ሆነ የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለማከናወን እንደምትቸገር ተናግረዋል።

የጀርመን ሚዲያዎች ውጭ ወጥታ እንደማታውቅና ጫካም ሆነ ሜዳ አይታም ሆነ ምንነቱንም እንደማታውቅ ዘግበዋል።

እናቷ ኑሯችንን በጣሊያን አድርገናል በሚል ለባለስልጣናቱ እንደዋሸች አስታውቀዋል ።

ቤተሰቦቿ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጀርመን ሳውየርላንድ አካባቢ ነው።

በዚህ ቤት ውስጥ እናት እና አያቷቿ አንዲትን ህፃን ለሰባት ዓመታት ያህል ከአለም እንድትነጠል ማድረጋቸውን አቃብያነ ህግ ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም ይህች ህፃን ከማንም ሰው ጋር ግንኙት እንዳይኖራት፣ ትምህርት ቤት እንዳትሄድና ውጭም እንዳትወጣ ተከልክላለች ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስካሁን ባለው አካላዊ ጥቃት ደርሶባታል ወይም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ስለመግጠሙ ምንም አይነት መረጃ የለም ብለዋል።

የአካባቢው የህጻናት ደህንነት ክፍል ኃላፊ ሚካኤል ፋርበር ማንበብ እና አንዳንድ ቀላል ሂሳቦችን መስራት እንደምትችል ተናግረዋል።

ሆኖም በእለት ተእለት ያሉ ቀላል ተግባራት ለማከናወን እንደምትፈተን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ህጻኗ በልጆች የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንክብካቤ ውስጥ ትገኛለች።

የጀርመን ብሔራዊ የሕፃናት ጥበቃ ማኅበር ባለሙያ ለጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት “ በአሁኑ ወቅት ለህጻኗ ዓለም ተገለባብጣባታለች። በሌላ ፕላኔት ላይ የመሆን ያህል ነው የሚሰማት” ብለዋል።

አቃብያነ ህግ እናትና አያቶች ለምን ህጻኗን ከአለም መነጠል እንዳስፈለጋቸው ምክንያታቸውን ለማወቅ እየሞከሩ ነው።

ነገር ግን እናቷ ህፃኗን ከአባቷ ለማራቅ በሚል እንደሆነ ተገምቷል። ልጅቷ ከመወለዷ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው ግለሰቧ ከልጇ አባት ጋር የተለያየችው።

ልጁን እንዳያይ በመከልከሏም አባትየው ጉዳዩን ወደ ቤተሰብ ፍርድ ቤት ወስዶት ነበር። ፍርድ ቤቱም በአውሮፓውያኑ 2012 በጋራ እንዲያሳድጉ ብያኔ አስተላለፈ።

ነገር ግን የጀርመን ባለስልጣናትም ሆነ አባትየው ያምኑ የነበረው እናት ልጇን ይዛ አገር ለቃ እንደወጣች ነበር።

እሷም በአውሮፓውያኑ 2015 ወደ ጣሊያን እንደሄደች ለባለስልጣናቱ አሳውቃ ነበር። አገር ለቃ እንዳልወጣችና ልጇንም ይዛ ወላጆቿ ቤት እንደገባችና እነሱም በዚህ ተባባሪ እንደሆኑ ተገልጿል።

በዚህች 24 ሺህ ነዋሪዎች ባሉባት ትንሽ ከተማ ውስጥ አንዲት ህጻን ለረጅም ጊዜ ተደብቃ መቆየቷ በአካባቢው ግርምታን ፈጥሯል።

 ባለስልጣናቱ በቅርብ ዓመታት ጥቆማ ስለደረሳቸውም ነበር ምርመራ የከፈቱት፤ ሆኖም በወቅቱ ተጨባጭ መረጃ ማግኘት አልቻሉም ነበር።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ አንድ ባልና ሚስት ህፃኗን እንዳዩዋት ለመርማሪዎች ማሳወቃቸውንም ተከትሎ በተከፈተ ምርመራ እናቲቱ ጣሊያን ኖራ እንደማታውቅ ደረሱበት።

የህጻኗ እናት እና አያቶች በህገወጥ እስር እና ግፍ በማድረስ ወንጀል ተጠርጥረው እየተመረመሩ ይገኛሉ። አቃቤ ህግ እናት እስከ 10 አመት እስራት ልትቀጣ እንደምትችል ቢያሳውቅም እስካሁን ግን ምንም አይነት ክስ አልተመሰረተም።