ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋዛን ለቀው እየወጡ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት የምናውቀው
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ምን አልባት አንዳንዶችን ሊረብሽ የሚችል ዝርዝር ይዘት ይዟል።
አርብ ምሽት ላይ ሰላማዊ ሰዎችን አሳፍረው ወደ ደቡባዊ ጋዛ እየተጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን የሚያሳዩ ዘገባዎች ወጥተዋል።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች አሳፍረው የነበረው የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ሰሜናዊ ጋዛን ለቀው የሚወጡ ሰላማዊ ሰዎችን ነው።
ከአየር ድብደባው በኋላ በአካባቢው የደረሰውን እልቂት የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም ብዙም ሳይቆዩ ነበር የወጡት።
ቢቢሲም የወጡትን ቪዲዮዎች በመተንተን ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ ጋዛ ከሚወስዱት ሁለት መንገዶች አንደኛው በሆነው ሳላህ አል ዲን ጎዳና ላይ ድብደባ መፈፀሙን አረጋግጧል።
ቪዲዮው የሚያሳየው ምንድን ነው?
በቢቢሲ የተረጋገጠው ረዘም ያለው ቪዲዮ በጣም አሰቃቂ ነው። የሚያሳየው በአጠቃላይ በሥፍራው የደረሰውን እልቂት ነው። ወንዶች ጸሎት እያደረጉ እና እያለቀሱ በጭስ በተሸፈነው አየር ውስጥ ሲሮጡ ታይተዋል። ሳይረን እና የመኪና ጦሩምባዎች ይሰማሉ።
የቪዲዮ ካሜራው ወደ ተሽከርካሪው ሲቀርብ ደግሞ የደረሰውን የጉዳት መጠን በግልጽ አሳይቷል። የተጠማዘዙ እና የተጣመሙ አስክሬኖች በየቦታው ወድቀዋል።
በኋላ ላይ ቲ ሸርት እና ቁምጣ የለበሰ ታዳጊ አስክሬን ተሽከርካሪው ላይ ወድቆ ይታያል። ጭንቅላቱ ወደ ካሜራው የዞረ ነበር። በዚህም ቪዲዮ ላይ ቢቢሲ ቢያንስ የ12 ሰዎች አስክሬንን መለየት ችሏል።አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። የተወሰኑት ሕጻናት ከሁለት እስከ አምስት በሚደርስ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ይመስላሉ።
ሌላ ምስል ላይ ደግሞ የሰዎች አስክሬን በጎዳና ላይ ወድቆ ይታያል።ተሽከርካሪዎቹ፣ ምን አልባትም አሽከርካሪዎቹ እና መንገደኞቹ ውስጥ ባሉበት ሲቃጠሉ ያሳያሉ።
ከድብደባው በኋላ የወጡ የተረጋገጡ ምስሎች
ከድብደባ በኋላ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርተዋል።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱ የተፈፀመው ሰሜንን ከደቡብ በሚያገናኘውና የፍጥነት መንገድ በሆነው ሳላህ አል ዲን ጎዳና ላይ መሆኑን ዘግበዋል። ይህ መንገድ በሰሜን ጋዛ የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ወደ ደቡብ ጋዛ ለመጓዝ የሚጠቀሙበት አንደኛው መስመር ነው።
የእስራኤልን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው እየወጡ ስለነበር አርብ ዕለት መንገዱ የተጨናነቀ ነበር።
በቢቢሲ የተረጋገጠው የመጀመሪያው ቪዲዮ ከጥቃቱ በኋላ የነበረውን አስከፊ ሁኔታ ያሳያል። ቪዲዮውን ለማረጋገጥም ከሰሜን ጋዛ ጀምሮ 45 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በቦታው የነበረውን ሞት እና ውድመት ቢቢሲ የተመለከተ ሲሆን ቪዲዮው ሕንጻዎችና የመንገድ ምልክቶችን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ዝርዝሮችን ያሳያል።ይህም ቦታው የት እንደሆነ ፍንጭ ሰጥቷል።
ከዚያም የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም፣ ጎዳናውን በመመልከትና በቪዲዮው ላይ ከታየው ዝርዝር መረጃ ጋር ተዛማጅነት ያለውን መረጃ መርምሯል።
በዚህም አደጋው የተከሰተው ከደቡባዊ የጋዛ ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን ለይቷል።'ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች' በመጠቀምም ምስሉ አዲስ ስለመሆኑና ከዚህ ቀደም በማኅበራዊ ሚዲያ ያልተጋራ ስለመሆኑ አረጋግጧል።
በመጨረሻም የኦንላይን ዘዴ በመጠቀም የጸሐይን አንግል እና የጥላ ርዝመት በመለየት ምስሉ እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 13፣ 8፡30 ላይ እንደተቀረጸ ማረጋገጥ ተችሏል።
እነዚህን መረጃዎች በመያዝም ክስተቱን ያሳያል ከተባለ ሌላ ምስል ጋር አመሳክሯል።
ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት
ሌላ ቪዲዮ በቀድሞው ትዊተር አሁን ደግሞ ኤክስ በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቅዳሜ ጠዋት ሲዘዋወር ታይቷል።
በዚህ ቪዲዮ ላይ ከሰሜን ጋዛ የተነሳ ተሽከርካሪ ከድብደባው በኋላ ያለውን ክስተት በሚያሳየው ቦታ አቅራቢያ ላይ ሆኖ ይታያል።በተሽከርካሪው ላይ ከ30 በላይ ሰዎች እንደተሳፈሩ ይገመታል። ይሁን እንጂ ጥቃት የተፈፀመበት ተሽከርካሪ ይህ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
በዚህ ቪዲዮ ላይ የኦንላይን ሶፍትዌር በመጠቀም የጥላውን እንግል መተንተን የተቻለ ሲሆን ቪዲዮው የተቀረጸው ከ9፡30 እስከ 11 ፡20 መካከል ባሉት ሰዓታት ነው።
የመንገዱ ስፋት እና አካፋይም መንገዱ ዋና መንገድ መሆኑን ያሳያል።
የሳተላይት ምስሎችም በአቅራቢያው ባሉ ሕንጻዎች እና ዛፎች አቀማመጥን በመጠቀም የተሽከርካሪውን መገኛ ትክክለኛ ቦታ ማረጋገጥ ተችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ጥቃቱ የተፈፀመው በዚህ ቦታ በደቡብ አቅጣጫ ነው። ምስሉ የተቀረፀው ደግሞ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ነው። ይህም ተሽከርካሪው ከመመታቱ ከሰዓታት በፊት ሊገኝበት የሚችለውን ሥፍራ የሚያሳይ ነው።