አንዲት ሱዳናዊት ወጣት፣ ወንድ ስማለች ተብላ በመከሰሷ እስር ተፈረደባት

ታትሟል

አንዲት ሱዳናዊት ወጣት አንድን ወንድ መሳሟን ካመነች በኋላ ፍርድ ቤት በአመንዝራ ጥፋተኛ ናት ብሎ እስር ተፈረደባት።

በዚህ ድርጊት የተከሰሰችው የ20 ዓመቷ ወጣት በመጀመሪያ ላይ በድንጋይ ተወግራ እንድትገደል ነበር የተፈረደባት።

ይሁን እንጂ ቅጣቱ ዓለም አቀፍ ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ ቅጣቱ ተቀንሶ ስድስት ወራትን በእስር እንደታሳልፍ ተወስኗል።

ዘ አፍሪካን ሴንተር ፎር ጀስቲስ ኤንደ ፒስ ስተዲስ (ኤሲጄፒኤስ) የተባለው ድርጅት ቀደም ሲል ወጣቷ ላይ ተላልፎባት የነበረውን ፍርድ “ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ የሕግ ጥሰት ነው” ብሎ አውግዞት ነበር።

ወጣቷ አመንዝራለች በማለት ጥቃተኛ ናት ብሎ የሞት ቅጣት አስተላልፎ የነበረው በሱዳኗ ዋይት ናይል ግዛት፤ ኮስቲ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት ነው።

ይሁን እንጂ ብይኑ ቁጣን ከቀሰቀስ በኋላ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ዳግም ተመልክቶታል። ጉዳዩን የያዙት ዳኛ የወጣቷን ድርጊት ከ“ማመንዘር” ወደ “አስነዋሪ ተግባር” መፈጸም በሚለው በመቀየራቸው ሕይወቷ ተርፏል።

ጠበቃዋ ኢንቲሳር አብዱላህ ወጣቷ በፍርድ ቤት ወንድን መሳሟን ማመኗ ዳኛው “ጥፋተኛ ናት ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ልጅቷ ለፍርድ ቤቱ ከወንድ ጋር እንደነበረች አምናለች፤ በዕድሜ ትንሽ በመሆኗ፣ የቀረበባትን ክስ ስታምን ሊያስከትል ስለሚችለው መዘዝ አላወቀችም” ብለዋል።

ኤሲጄፒኤስ ወጣቷ በፍርድ ሂደቱ መጀመሪያ ላይ ጠበቃ የማቆም ዕድል አልተሰጣትም ነበር ብሏል።

ሱዳን አሁንም ድረስ በቁራን ላይ በአላህ ወንጀሎች ተብለው የተጠቀሱትን ተግባራት የፈጸሙትን በሞት ትቀጣለች። በሞት ከሚያስቀጡ ወንጀሎች መካከል ስርቆት እና በትዳር ላይ ማመንዘርን ይጨምራል።

በዚህም በሱዳን ሕግ መሠረት ሰዎች ሰዎች እንደሚፈጽሟቸው ጥፋቶች በግርፋት፣ እጅ ወይም እግርን በመቁረጥ፣ በስቅላት ወይም በድንጋይ በመወገር ሊቀጡ ይችላሉ።

በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሱዳን በተለይ በድንጋይ በመወገር የእንዲገደሉ የሚፈረድባቸው በአብዛኛው ሴቶች ናቸው። እነዚህ የፍርድ ውሳኔዎች ግን ብዙ ጊዜ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ይደረጋሉ።

ከዚህ ቀደም አንድ የሱዳን መንግሥት ሚኒስትር እነዚህን ቅጣቶች “ቀልድ” ሲሉ የገለጿቸው ቢሆንም፣ የትኛውም የመንግሥት ሚኒስትር ግን ጣልቃ መግባት እንደማይችል አምነዋል።

ከወራት በፊት በሱዳን መፈንቅለ መንግሥተ ከተካሄደ በኋላ አገሪቱ በወታደራዊው መኮንኖች እየተመራች ትገኛለች።