ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፈው ሰኔ በጋምቤላ የፀጥታ ኃይሎች የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ 50 ሰላማዊ ሰዎች መግደላቸው ተገለጸ
በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
በጋምቤላ ክልል ያጋጠመውን ቀውስ በተመለከተ ኢሰመኮ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 18/2014 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በጋምቤላ ከተማ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ የፈጸሙ ኃላፊዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት እንዲኖርም ጠይቋል።
በከተማዋ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ እና በአማጺያኑ ታጣቂዎች መካከል የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችን እና ዘረፋዎችን በተመለከተ ኢሰመኮ ምርመራ ማድረጉን ገልጿል።
ይህንንም በተመለከተ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው 13 ገፅ ሪፖርት ከሰኔ 07 እስከ 09 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ዘረፋ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎች መፈጸሙን አመልክቷል።
እነዚህን አካላት ይፋ ያደረገው ኢሰመኮ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች ድርጊቱን በመፈጸም፣ በመምራት እና በማስፈፀም ተሳትፈዋል ብሏል።
በሦስቱ ቀናት ውስጥ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሴቶችና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎችን በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መግደላቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
ታጣቂዎቹ ከተማዋን ለቀው ከወጡ እና ከተማው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ከገባም በኋላ ግድያዎቹ የተፈፀሙ ሲሆን ለዚህ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ተጠያቂ መሆናቸው ሰፍሯል።
ኮሚሽኑ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ብሎ የጠራቸው የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች ሲሆኑ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር የተባበሩ የተወሰኑ ወጣቶች መኖራቸው ተጠቅሷል።
የጸጥታ ኃይሎቹ ባደረጉት አሰሳ ቢያንስ 50 ሰዎችን በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ እና ውጪ፣በመንገድ ላይ እና በህግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ ሰዎችን ጭምር ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን ኮሚሽኑ በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በተጨማሪ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት፣ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ በርካቶች ላይ ደግሞ ድብደባ እና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን የኢሰመኮ ሪፖርት ያስረዳል።
ለዚህም የፀጥታ ኃይሎቹ “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሳሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ” የሚል ምክንያትም እየሰጡ ነበር ብሏል።
በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰላማዊ ነዋሪዎች አስከሬን በክልሉ ልዩ ኃይሎች እና ፖሊሶች አማካይነት በጭነት መኪና ተሰብስበው ወዳልታወቀ ቦታ እንደተወሰደና በጅምላ እንዲቀበሩ መደረጉን ኮሚሽኑ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችና የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
በተጨማሪም አስከሬን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ የሟች ቤተሰቦችም መከልከላቸውን አረጋግጧል።
የሟቾች አስከሬን ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተሰጠና የተቀበሩበት ቦታ ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተገለጸ ኢሰመኮ የክልሉን ፖሊስ ጠይቆ፣ አስከሬን እንዲሰጠው ያመለከተ የከተማው ነዋሪ የለም የሚል መልስ ማግኘቱን ገልጿል።
የከተማው ማዘጋጃ በበኩሉ ፌደራል ፖሊስን እንዲያነጋግሩ ለኢሰመኮ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ አስከሬኖች ተሰብስበው የተቀበሩት በማዘጋጃ ቤቱ መሆኑን መግለጹ ተጠቅሷል።
ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሌላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎችም ውጊያው በተካሄደበት ዕለት “ተኩሳችሁብናል” በሚል ምክንያት በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ ሰባት ሰዎች መግደላቸውን ያትታል።
ከግድያው በተጨማሪ በበርካታ ነዋሪዎች ላይ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ማድረሳቸውንም ተገልጿል።
የፀጥታ ኃይሎቹና ታጣቂ ኃይሎቹ ከገደሏቸው በተጨማሪ በተኩስ ልውውጡ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቁ ስድስት ሰዎች ሕይወታችው ማለፉንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም በበኩሉ ከውጊያው በኋላ ባደረገው ማጣራት የክልሉ ልዩ ኃይሎች ሰኔ 8 እና ሰኔ 9/2014 ዓ.ም. በከተማዋ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጾ፣ በተጨማሪ መወሰድ ያለባቸውን ሕጋዊ እርምጃዎችም መጠቆማቸውን ገልጸዋል።
“የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳ እና መልሶ የመቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙና” ተፈጻሚነቱንም እንደሚከታተል ኢሰመኮ አሳስቧል።
ሰኔ 07 ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መንግሥት በሽብርተኛነት የሰየመው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በጋራ ወደ ጋምቤላ ከተማ ገብተው ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ከክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ፌደራል ፖሊስ ጋር ውጊያ ተደርጓል።
ታጣቂዎቹ የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን ውጊያውንም ተከትሎ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የጋምቤላን ከተማ መልሰው መቆጣጠራቸው ይታወሳል።